ዜና፡ በትግራይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ፣ በአማራ ከ580 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19 /2015 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ 1 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ትላንት ሓምሌ 18፣ 2015 ባወጣው ሪፖርቱ  ዘላቂ ጦርነት የማቆም ስምምነቱ ከተደረሰበት ህዳር ወር  ጀምሮ 700ሺህ ተፈናቃዮች ያለ ድጋፍ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል ሲል ገልጧል፡፡

አሁን ላይ ለተፈናቃዮች የሚውል ገንዘብ፣ ምግብ፣ አስቸኳይ መጠለያና ምግብ ነክ ያለሆኑ ቁሳቁስ ድጋፍ እጥረት ሳቢያ ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው የመመለሱ ስራ መቆሙን ገልጧል፡፡

በአማራ ክልል ደግሞ እስከ ሰኔ ወር ድረስ በ15 ወረዳዎች 580 ሺህ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ሪፖርቱ ገልጧል፡፡ ወደ ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ህመራና ኦሮሞ ልዩ ዞን፤ 360 ሺህ ዜጎች መመለሳቸውን የገለፀው ድርጅቱ መሰረታዊ የሆኑ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የህክምና፣ የትምህርት፣ የውሃ፣ እና የንፅህና መጠበቂያዎች እጥረት የተመላሾችን ችግር እንዳባበሰው አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብና ቄሌም ወለጋ ዞኖች ውስጥ በግጭትና ፀጥታ ችግር የተነሳ የተፈናቀሉ ሰዎች ያለ ሰብዓዊ ድጋፍ ሳያገኙ መቅረታቸውን ገልፆ ከ 13 ሺህ በላይ ሰዎች በ2021 እና 2022 ተፈናቅለው ከተመለሱ በኋላ በምስራት ወለጋ ዞን ጎቡ ሳዮ እና ዋዩ ቱካ ወረዳ በተፈፀረ የፀጥታ ችግር  ተፈናቅለው በማህበረሰቡ መካከል ተጠልለው ይገኛሉ ብሏል፡፡

የድርጅቱ ሪፖርት ተፈናቃዮች የእለት ተእለት መሰረታዊ አገልግሎት እንደማያገኙና ለመተዳደሪያቸው የሚረጋቸውን ክንዋኔዎችን እንደማያደርጉ ገልፆ የታጠቁ ቡድኖች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው በካምፖች እና በከተሞች ውስጥ ተገድቧል ብሏል። በሰኔ ወር የክልሉ መንግስት በምስራቅ ወለጋ ዞን ለስድስት ወረዳዎች ከ45 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች የስንዴ ዱቄት ድጋፍ ማድረጉን የገለፀው ሪፖርቱ የምግብ እርዳታ፣ የህክምና አገልግሎት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብሏል፡፡

አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያን ጨምሮ በዘጠኝ ክልሎች ከ 480 ሺህ የሚሆኑ ሰዎ በክረምት ጎርፍ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በክረምቱ ጎርፍና በወንዞች መሙላት ሳቢያ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ተብሎ አንደሚገመትም አክሎ አስታውቋል፡፡ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለመከላከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

እስከ ሓምሌ 21 በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በርሜል ቅዱስ ጊዮርጊስ ፀበል አካባቢ የተነሳ የኮሌራ በሽታ ከዘጠን ዞኖች ውስጥ በ 13 ወረዳዎች ላይ ከ 2150 በላይ ሰዎች ላይ መከሰቱን የገለፀው ሪፖርቱ ክልሉ በራካታ ስደተኞች ከሱዳን የሚገቡበት በመሆኑ እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚጠለሉበት በመሆኑ ለኮሌራ በሽታ ተጋላጭ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

በዚህ አመት በኩፍኝ በሽታ ከተያዙ 22 ሺህ 400 ሰዎች ውስጥ ከ420 በላይ የሚሆነው በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው ወይንሸት የተፈናቃይ ጣቢያ የተከሰተ ነው ብሏል፡፡

በተጨማሪም በአማራ 137,298፣ በትግራይ 454,688 ሰዎች ላይ የወባ በሽታ መከሰቱን ገልፆ ቁጥሩ ባሳለፍነው ሳምንት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ ነበር ብሏል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.