ትንታኔ፡ በደመወዝ እና ሌሎች የመብት ጥያቄዎች እየተናጠ የሚገኘዉ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የቅጥር እና የሰራተኞች አስተዳደር ስርዓት

በአይሰን ኤክፕሪያንስ ተቀጥረው የሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል አገልግሎት ስራን በመስራት ላይ ያሉ ሰራተኞች በሚያነሱት የመብት ጥያቄዎች ላይ ውይይት እያደረጉ፤ ፎቶ- ከሰራተኞቹ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አባባ፣ ሐምሌ 19/ 2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለበርካታ አመታት በብቸኝነት ሲንቀሳቀስ ከነበረው ኢትዮ ቴልኮም በተጫማሪ በቅርቡ የአገሪቱን የቴልኮም ዘርፍ በመቀላቀል አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከሰራተኞች ቅጥር እና አስተዳደር ጋር በተገናኘ ከጅምሩ ፈተናዎች ገጥመዉታል።

ከወራት በፊት በተለይም በኦሮምያ ክልል ከሰራተኞች ቅጥር እንዲሁም ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በድርጅቱ ዉስጥ መድሎዓዊ አሰራር አለ በሚል “ቦይኮት ሳፋሪኮም” የተሰኘ የድርጅቱን ምርትና አገልግሎቶች ከመጠቀም የመታቀብ ዘመቻ በማህበራዊ ሚዲያ መደረጉን ተከትሎ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች የዘመቻዉን አስተባባሪዎች ጠርተዉ ማነጋገራቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪ አይሰን ኤክፕሪያንስ ኢትዮኮል ኃ/የተ/ግ/ማ በሚባል ድርጅት በኩል ተቀጥረዉ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የጥሪ ማዕከል በመስራት ላይ ያሉ ሠራተኞች ረዘም ላለ ጊዜ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎች እና ቅሬታዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ።

በሃገሪቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አስረኛ ወሩን ሊደፍን ጥቂት ቀናት የቀሩት እና በቅርቡ ታዋቂዉን የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቱን (M-Pesa) ሃገር ዉስጥ እንዲጀምር ከብሄራዊ ባንክ ፍቃድ የተቸረዉ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እስከለፈዉ ግንቦት ወር ከ3 ሚሊየን ባላይ ተጠቃሚዎችን በመመዝገብ ስኬታማ ሊባል የሚችል ጅማሮን ያሳየ ቢሆንም ዉጤታማ የሰራተኞች ቅጥር እና አስተዳደር በመዘርጋት ረገድ ግን አሁንም ቅሬታውች ይሰማሉ።

በተለይም በአይሰን ኤክፕሪያንስ በኩል ተቀጥረው ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የጥሪ ማዕከል በመስራት ላይ የሚገኙ ሠራተኞች በርካታ የመብት ጥያቄዎች እንዳሉዋቸዉ እና እነዚህ ጥያቄዎቻቸዉ እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሰራተኞች ያለ አግባብ ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡

ሰራተኞቹ ከሚያነሷቸዉ ጥያቄዎች የደመወዝ ጥያቄ አንዱ ሲሆን ስሜ ቢገለፅ ተፅዕኖ ያደርስብኛል በሚል ስጋት ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ አንድ ሠራተኛ፣ “ሰፋሪኮም ለሠራተኛው የሚመድበው ክፍያ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የቀጠራቸው ድርጅት አይሰን ኤክስፕሪያንስ ለራሱ ይቆርጥብናል” ሲል ገልጧል፡፡ 

በአሁኑ ሰዓት ለሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል በመስራት ላይ እንደሚገኝ የገለፀው ይህ ሰው ሳፋሪኮም ለሰራተኞቹ የሚከፍለውን 70 በመቶውን አይሰን ኤክስፕሪያንስ ለራሱ በመቁረጥ ለሰራተኛው 30 በመቶውን ብቻ ነው የሚከፍለው ሲል ገልጧል፡፡ ይህንንም በአሃዝ ሲያስረዳ ሳፋሪኮም ለአንድ የስልክ ኦፕሬተር የሚከፍለው ደመወዝ 20ሺህ እስክ 24 ሺህ ሆኖ ሳለ አይሰን ኤክስፕሪያንስ ግን ለሰራተኛው የሚከፍለው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 6500 ብር ብቻ ነበር ብሏል፡፡

ይህንንም በመቃወም ከዚህ በፊት ባደረግነው ስራ የማቆም አድማ ስድስት ወር ለሞለቸው ሰራተኞች ብቻ ደሞዛቸዉ ከ6500 ወደ 7800 ብር ከፍ እንደተደረገላቸው የገለፀው ሰራተኛዉ የተጨመረው ክፍያ ለሙያው ከሚገባው እና ካለብን የሥራ ጫና አንጻር ተገቢ ያልሆነ በዘርፉ ከተሰማሩ ድርጅቶች የክፍያ ስኬል መሰረት እና ከወቅታዊ ኑሮ ውድነት ጋር ሲነፃፀር በቂ አለመሆኑን ገልጧል፡፡

“በቅርቡ ሰባት ወር ለሆናቸውና የደሞዝ እድገት ደረጃ ላይ ለደረሱ ሰራተኞች ክፍያ ላለመጨመር ነባር ሰራተኞችን ከህግ አግባብ ውጭ ውላቸው እንዲቋረጥ በማድረግ አዳዲስ ሰራተኞችን ባነሰ ክፍያ በመቅጠር ላይ ነው” ሲል የድርጅቱ ሰራተኛ ይከሳል፡፡

ሌላ በተመሳሳይ መልኩ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የጥሪ ማዕከሉ ሰራተኛ ከደምዝ ጥያቄ በተጨማሪ ድርጅቱ የሰራተኛ የስራ አፈፃፀም ምዘና (KPI) ብሎ ያስቀመጠው መመሪያ ከሕግ አንፃር የማያስኬድ ነው ይላል። “አንድ ሰራተኛ ለአንድ ቀን በህመም ምክንያት ከስራ ቢቀር እና ህጋዊ ህክምና ማስረጃ ይዞ ቢቀርብም በወር ውስጥ ያለው የስራ ብቃት አፈፃፀም ምዘናው በግማሽ ተቀናሽ የሚደረግበት ይሆናል” የሚለዉ ሰራተኛዉ “አንድ ሰራተኛ በስራ ገበታ ላይ ተገኝቶ በሰራበት ቀን እንጂ ሳይፈልግ አስገዳጅ በሆነ ምክንያትና ማስረጃም አቅርቦ ከስራ በቀረበት ቀን አፈፃፀሙ መመዘን የለበትም” በማለት ያስረዳል፡፡

ከዚህ ዉጭ በማታ ሺፍት ለሚሰሩ ሰራተኞች ሌሊት ድርጅቱ ማቅረብ የሚጠበቅበትን የትራንስፖርት አገልግሎት በአግባቡ አያቀረበ ባለመሆኑ ሰራተኞቹ ለሌብነትና ለእንግልት እየተጋለጡ መሆኑን ሰራተኛዉ ቅሬታ ያቀርባል፡፡ በተደጋጋሚ ለዚህ ችግር መፍትሄ እንዲሰጠን ብንጠይቅም ከፈለጋቹ ስሩ ካልፈለጋችሁ ልቀቁ የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን ሲልም ያክላል፡፡

የጥሪ ማዕከሉ ሠራተኞች ረጅም ሰዓት ሄድሴት ጆሮዋቸዉ ላይ አድርገዉ የሚውሉ በመሆኑ በጆሮዋቸው ላይ ለሚደርሰው  ጉዳት ድርጅቱ የጤና ኢንሹራንስ እንዲገባ ተጠይቆ በአንድም ሰራተኛ ላይ ተግባራዊ አለማድረጉ በሰራተኞች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱንም አክሎ ገልጧል፡፡

ፍትሃዊ የስራ እድገት አለመስጠት ሰራተኞቹ የሚያነሱት ሌላኛው ጥያቄ ሲሆን የስራ እድገት የሚገባውን ሰው ትተው ለአመራሩ ቅርብ ለሆነ ሰራተኛ ብቻ እድገት እንደሚሰጥ፤ ሰራተኞች በተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ይዘው ስለሚጠይቁ ብቻ እድገት እንደሚከለከሉ፤ በዚህም ምክንያት የቡድን መሪ የሆኑ ልጆች ስልክ ወደ ማንሳት ደረጃ ዝቅ እንዲሉ ተደርገው እንዲሰሩ እንደሚደረጉ ገልፀዋል፡፡

“ርካሽ የሰው ሃይል እንዳለና በቀላሉ ሌላ ሰራተኛ መቅጠር እንደሚችሉ” ስለሚያምኑ ለሰራተኞች ጥያቄዎች ምላሽ አለመስጠትን ይመርጣሉ ብሏል ሁለተኛዉ ሃሳቡን ለአዲስ ስታንዳርድ የሰጠዉ ሰራተኛ፡፡

የድርጅቱ ሰራተኞች እንደሚገልፁት ከሆነ በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱላቸዉ በግልም ሆነ በቡድን የጠየቁ ቢሆንም ማንኛውንም ጥያቄ እና ቅሬታ በቡድን እንዳይጠይቁ የቃላትና የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው እንደነበር ገልፀዋል። በተጨማሪም የሰራተኞችን ጥያቄ በመያዝ የሚታገሉ ሰራተኞች ከስራ ተባረዋል እንዲሁም ተማረው ስራውን እንዲለቁ ተደርገዋል ይላሉ።

ሰራተኞቹ ከበርካታ ትግል በኋላ ግንቦት 8 2015 ዓ.ም አይሰን ኤክፕሪያንስ ኢትዮኮል ኃ/የተ/ግ/ማ የሠራተኞች ማህበርን ያቋቋሙ ሲሆን ማህበሩ በተቋቋበት እለት የማህበሩ ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠውና ከፊት ሆኖ የሰራተኞቹን ጥያቄዎች ይዞ ሲታገል የነበረው ቸርአምላክ ታምሩ የሰራተኞቹን ቅሬታዎችን ይዞ ድርጅቱን ኃላፊዎች በመጠየቁ ከስራ እንዲሰናበት መደረጉን የድርጅቱ ሠራተኞች ማህበር ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጧል፡፡ ድርጊቱ ከህግ አግባብ ውጭ በመሆኑ በድርጅቱ ላይ ክስ ቀርቦበት፣ በህግ ሂደት ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ ከስራ ተባረረ ከተባለዉ የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ቸርአምላክ ታምሩ ጋር ባደረገዉ ቆይታ ጉዳዩ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የኮልፌ ቀራንዮ ምድብ ችሎት እንደተያዘ እና የክስ መጥሪያ ወረቀትም ለድርጅቱ እንደደረሰው ተረድቷል። በመሆኑም ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ መሆኑን ግምት ዉስጥ በማስገባት የቅሬታ አቅራቢዉ ሃሳብ በዚህ ዘገባ ሳይካተት ቀርቷል።

ነገር ግን የትራንስፖርትና መገናኛ እንዱስትሪ ሠራተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ግንቦት 14 ቀን 2015 ለልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የስራ፣ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ አይሰን ኤክፕሪያንስ የድርጅቱን ሠራተኞች ማህበር ሊቀምንበር “ህግን በጣሰና ተልካሻ ምክንያት” ከስራ አሰናብቶታል ሲል ማስታወቁን አዲስ ስታንዳርድ ተገንዝቧል፡፡ ፌዴሬሽኑ ድርጊቱ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እንቀጽ 14 ተራ ቁጥር 1(ሀ) የጣሰ ነው ሲል በደብዳቤው አክሎ ገልጧል፡፡

ይህንን ተከትሎም የልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ሁለቱ አካላት እንዲግባቡ ቢያወያይም የድርጅቱ ኃላፊዎች ሰራተኛውን ወደ ስራ ገበታው አንመልስም በማለታቸው ጽ/ቤቱ ጉዳዩን ወደ አሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ መምራቱን ግንቦት 25፣ 2015 ዓ.ም ለቦርዱ የተፃፈ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡

በአይሰን ኤክስፒሪያንስ ተቀጥረው ለሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል የሚሰሩ ሠራተኞች እነዚህን እና ሌሎች የመብት ጥያቄዎቻቸዉን በደብዳቤ መልክ ከአይሰን ኤክስፒሪያንስ በተጨማሪ ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ስራና ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢያስገቡም በቂ ምላሽ አልተሰጠንም ይላሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከወራት በፊት በተለይም በኦሮምያ ክልል ከሰራተኞች ቅጥር እንዲሁም ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በድርጅቱ ዉስጥ መድሎዓዊ አሰራር አለ በሚል ከተደረገበት የድርጅቱን ምርትና አገልግሎቶች ከመጠቀም የመታቀብ ዘመቻ በኋላ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች የዘመቻዉን አስተባባሪዎች ጠርተዉ በማነጋገር ችግሩን በአጭር ጊዜ እንደሚፈቱት ቃል ቢገቡም፤ ችግሩ ባለመፈታቱ ከሰሞኑ ተመሳሳይ የማህበራዊ ዘመቻን የማድረግ አዝማሚያ ይታያል።

በሳፋሪኮም ላይ በክልሉ የተነሳውን ጥሬታዎች በመያዝ ጥያቄውን ለድርጅቱ ሲያቀርቡና ከሳፋሪኮም ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሲወያዩበት ከነበሩት ተወካዮች አንዱ የሆነው እና ከሰሞኑ እየተደረጉ የነበሩትን ቅስቀሳዎች በመምራት ረገድ ጉልህ ሚና ያለዉ የአይቲ ባላሙያ አብዲሳ ባንጫሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሲያደርገው የነበረው የቅጥር ሂደት ብልሹ አሰራሮች የሞላበት፣ ለስራው ብቁ የነበሩ ልጆችን በብሔር እና ሃይማኖት ምክንያት ያለመቅጠር አሰራር እንደነበር ይህንንም ከድርጅቱ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጄክቶች፣ የኔትዎርክ ዝርጋታዎችን፣ እንዲሁም የሽያጭ ስራን የሚሰሩ ሰዎች በትውውቅ የሚቀጠሩ እንጂ ሁሉንም አኩል ኣሰታፊ አያደርግም፤ የሚለው አብዲሳ ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል በሚያደርጋቸዉ የስራ እንቅስቃሴዎች የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን መጠቀም አለበት የሚለዉ ሌላኛዉ ቅሬታ መሆኑን እና ይህም አለመስተካከሉን ይናገራል።

“ከቀድሞ የሳፋሪኮም ዋና ስራ አስኪያጅ ባደረግነው ውይይት በጉዳዩ ላይ ገብተው ማስተካከል እንዳልቻሉ ነግረውናል” ያሉት አቶ አብዲሳ ይህ ችግር ኬንያ ለሚገኘው ዋና መስሪያ ቤትም መድረሱን ገልፀዋል፡፡ አሁን የተሾሙት አዲሱ ስራ አስኪያጅ የሠራተኛውን ቅሬታ አለመስማትና ክልሎች በራሳቸው ቋንቋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚከለክለውን የሳፋሪኮም አሰራርን ይቀይራሉ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልፆ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በተለይ በኦሮሚያ ድርጅቱ ፈተናዎች ሊገጥሙት ይችላሉ ይላል።

ሳፋሪኮምና አይሰን ኤክስፒሪያንስ

አይሰን ኤክፕሪያንስ ባሳለፍነው አመት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ በመቀላቀል በጥሪ ማዕከል ስራ ላይ እንደተሰማራ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ በ15 አገራት ላይ እየሰራ እንደሆነ በኢትዮጵያም ቅርንጫፍ ከፍቶ በስሩ ወደ 600 ለሚጠጉ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሮ እየሰራ እንደሚገኝ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታዉቋል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸዉ በአይሰን ኤክስፒሪያንስ ተመልምለው እና ሰልጥነው ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የጥሪ ማዕከል የሚሰሩ ሰራተኞች እንደሚሉት ሰራተኞቹ የሚሰሩት ለሳፋሪኮም ቢሆንም የስራ ቅጥር እና የስምምነት ውሉን የተፈራረሙት ከአይሰን ኤክስፒሪያንስ ጋር ነዉ።

ከሰራተኞቹ አንዱ እንደሚለዉ አይሰን ኤክስፒሪያንስ የሚጠቀምበት ኮምፒውተሮች፣ ሰርቨሮች በሙሉ የሳፋሪኮም ሎጎ ያለባቸው መሆናቸውን ጠቅሶ መጀመሪያ ስንቀጠር የሳፋሪኮም ሰራተኛ ናችሁ ተብለን ነበር ይላል። ብዙ ሰራተኞች ከቀጠሩ በኋላ ግን የአይሰን ኤክስፕሪያንስ ሰራተኞች እንጂ የሳፋሪኮም አይደላችሁም ተብለናል ሲል ተናግሯል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ የአይሰን ኤክስፕሪያንስ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ አቶ እዩኤል ወርቁን ድርጅታቸው ከሳፋሪኮም ጋር ያለዉን የስራ ግንኙነት አስመልክተን ለጠየቃናቸው ጥያቄ “ሳፋሪኮም ደንበኛችን ነው ከዚህ በላይ ከሳፋሪኮም ጋር ያለንን ግንኙነት መግለፅ” አይጠበቅብንም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምንም እንኳ ሃላፊዉ ለሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆኑና አለመሆኑ ለመግለፅ ፍቃደኛ ባይሆኑም አዲስ ስታንዳርድ ባደረገዉ ማጣራት ድርጅቱ ቢዝነስ ፕሮሰስ አዉትሶርሲንግ በሚባል አሰራር መሰረት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያን የጥሪ ማዕከል (ኮል ሴንታር) ስራን ሙሉ በሙሉ ወስዶ በራሱ ሰራተኞች መልምሎ አሰልጥኖና ቀጥሮ እየሰራ መሆኑን መረዳት ተችሎል።

ምላሽ – ለሠራተኞቹ ቅሬታዎች

ሰራተኞቹ በድርጅቱ ላይ ያቀረቡትን ቅሬታዎች የአይሰን ኤክስፕሪያንስ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊዉ አቶ እዩኤል ወርቁ አስተባብለዋል፡፡

ደሞዝን በተመለከተ ድርጅቱ እንደማንኛውም ድርጅት ለሰራተኛው ደመወዝ እንደሚከፍል ጠቅሰው የደሞዝ መብዛትና ማነስ ጉዳይ የአንድ ተቋም ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል፡፡ ጨምረውም አይሰን ኤክስፕሪያንስ ለሰራተኞቹ ደምወዝ የሚከፍለው በራሱ ስኬል መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅቱ ስራ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጃንሲ እንደሆነና ሳፋሪኮም ለሰራተኞች ከመደበዉ ደሞዝ ከ70 በመቶ በላይ ይቆርጣል የሚለውን የሰራተኞች ቅሬታ፤ ድርጅቱ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰዉ በራሱ ስኬል መሰረት ሰራተኛ ቀጥሮ ደሞዝ እንደሚከፊል እና ሰራተኞች ሲቀጠሩ በዚህ ተስማምተዉ እንደሚገቡ፤ ሰራተኞቹም በቀጥታ የራሱ የአይሰን ኤክስፕሪያንስ እንጂ የሰፋሪኮም እንዳልሆኑ አንድ በዚህ ዘገባ ጉዳይ ለአዲስ ስታንዳርድ ተጨማሪ ማብራርያ የሰጡ የድርጅቱ የስራ ሃላፊ ተናግረዋል። በመሆኑም የድርጅቱ የደሞዝ ስኬል ያልተስማማዉ ሰራተኛ የተሻለ ደሞዝ ሊያስገኝ ወደሚችል ስረ ወይም ድርጅት የመሄድ መብት አለው ይላሉ እኝህ ሃላፊ።

የስራ ብቃት ምዘናን በተመለከተ ሰራተኞቹ ባነሱት ጥሬታ ላይ አቶ እዩኤል ወርቁ ሠራተኛው በህመም ምክንያት ቢቀርና ህጋዊ የህክምና ማስረጃ ይዞ ቢቀርብ ከደመወዙ ተቀናሽ እንደማይደረግ ገልፀው የስራ ምዛናው ግን በቀኑ ዜሮ ይደረግበታል ብለዋል፡፡ ሰራተኛው በህመም ምክንያት ለአንድ ቀን በስራ ገበታ ላይ ባይገኝ፣ በስራ ላይ ከተገኘ ሰራተኛ ጋር እኩል ምዘና ውስጥ ተካቶ የስራ አፈፃፀሙ አይሞላም ይህም የሆነው የተሰማሩበት የስራ ዘርፍ የሰራተኛውን መገኘት የሚፈልግ በመሆኑ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ትራንስፖርትን በተመለከተ አቶ እዩኤል ትራንስፖርት ያለተሟላበት ሺፍት የለም በማለት የሰራተኞችን ቅሬታ አስተባብለዋል፡፡ በፖሊሲያችን መሰራት ለሰራተኛው ተገቢ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠን ነው ያሉት ኃላፊው ትራንስፖርት የሚሻሻል ሂደት መሆኑን ጠቅሰው አንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች ግን ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡

ከፍትሃዊ የስራ እድገት አለመኖር ጋር በተያያዘ፣ 10 በመቶ የሚሆኑ ሰራተኞቻችን ከውስጥ ወደ ሱፐርቫይዘር ማደጋቸውን ገልፀው ይህም የምንኮራበት አሰራር ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ቀጥለውም እድገት የሚሰጠው ድርጅቱ ያስቀመጠውን መመዘኛ መስፈርቶችን ላሟላ ሰራተኛ ነው ያሉት ኃላፊው መመዘኛውን ሳያሟሉ እድገት ያላገኙ ሰራተኞች ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ሰራተኞችን የምናሰናብተው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ባስቀመጠው መሰረት ነው ያሉት አቶ እዩኤል የተነሱት ቅሬታዎች የእኛ አሰራር አይደለም ነው ያሉት፡፡ አቶ እዩኤል ሰራተኞችን በዘፈቀደ ከስራ የማባረር እና እንዲለቁ ጫና ማድረግን በተመለከተ የተነሳውን ቅሬታ “አሉባልታና ሀሜት ነው” በማለት አስተባብለዋል፡፡

ድርጅቱ ከስራ ስላሰናበተው የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ቸርአምላክ ታምሩን በተመለከተ ኃላፊዉ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢጠየቁም “ይህ የድርጅቱ ጉዳይ በመሆኑ አይመለከታችሁም” በማለት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ከህግ ውጭ የተሰናበት ሰራተኛ የለንም ሲሉ አክለዋል።

የህይወትና የአካል ጉዳት ኢንሹራንስ ለሰራተኛው ተፈፃሚ እየተደረገ አለመሆኑና የዚህ ተጠቃሚዎች ኃላፊዎች ብቻ ናቸው በሚል ሰራተኞቹ ላነሱት ጥያቄ አቶ እዩኤል በህግ የምንገደድበት ጉዳይ በመሆኑ በድርጅታችን ፖሊሲ መሰረት በርካታ ሰራተኞች አገልግሎቱን እያገኙ ይገኛሉ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሰራተኛው ቅሬታውን ይዞ ወደ ድርጅቱ ሲሄድ ተገቢ የሆነ ምላሽ አይሰጠውም፣ ከፈለጋችሁ ስሩ ካልፈለጋችሁ ለቃችሁ ውጡ የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠን በሚል ለተነሳዉ ቅሬታ አቶ እዩኤል በሰጡት ምላሽ በዚህ ልክ የሚሰጥ ምላሽ የለም ሲሉ ገልፀው “ይህን ቅሬታ ቃላቱን ሳይቀይር የሚያነሳውን ሰው አውቀዋለው” በማለት ጥያቄዉ የአንድ ሰራተኛ እንደሆነ አመላክተዋል። ሆኖም ግን በተባለው ልክ ሰራተኛን የማንቋሸሽ እና የማጥላላት ሁኔታ ድርጅቱ ላይ የለም በማለት ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.