ዜና፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ታጣቂዎች በመፈፀሙት ጥቃት 8 ነዋሪዎች ሲሞቱ 16 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7/ 2015 ዓ.ም፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ግልገል በለስ ከተማ በተለምዶ “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራ ሰፈር በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት፣ 3 የአካባቢውን ሚሊሻ አባላት ጨምሮ 8 ነዋሪዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ጥቃቱ የተፈፀመው በግልገል በለስ ከተማ፣ በተለምዶ “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራ ሰፈር ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ መሆን ኮሚስኑ ትላንት ሰኔ6 ቀን ባወጣው መግለጫ ገልጧል፡፡

በጥቃቱ ከሞትቱ ስምንት ሰዎች በተጨማሪ በ16 ሲቪል ሰዎች ላይ  ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ የሕክምና እርዳታ እያገኙ መሆኑንና በርካታ ሌሎች ነዋሪዎች ቻይና ካምፕን ለቀው ወደ ሌላ ሰፈር መሸሻቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አመላክቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና የአካባቢው አስተዳደር ኃላፊዎች የጥቃቱ ፈጻሚዎች በግልገል በለስ ከተማ አቅራቢያ ከመንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ትጥቅ ለማስፈታት በሚል አንድ ካምፕ ውስጥ እንዲሰፍሩ የተደረጉ የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት መሆናቸውን  እና በጥቃቱም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአካባቢው የሚኖሩ በተለምዶ “ቀዮች” ተብለው የሚታወቁ ነዋሪዎች/ከጉሙዝ ብሔር ውጪ ያሉ ሌሎች ብሔሮች መሆናቸውን አስረድተዋል ተብሏል።

ታጣቂዎቹም ለጥቃቱ ምክንያት ያሉት “ከመንግሥት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት አልተተገበረም” የሚል መሆኑን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ማወቅ ተችሏል።

የጉሕዴን ታጣቂዎች ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከግልገል በለስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በመሄድ አንድ እረኛ የገደሉ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዳሉ። በከተማዋ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ከተማዋ በመሠማራቱ ለጊዜው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ማወቅ ተችሏል።

በደረሰው ጥቃት ሳቢያ አካባቢውን ለቀው ወደ ሌላ ሰፈር ለሸሹ  ነዋሪዎች አስፈላጊው ሰብአዊ ድጋፍ  ማድረስ፣ ለነዋሪዎች አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ እንዲችሉ ማድረግ፣ እንዲሁም አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል ሲል ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

ታጣቂ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት እና መልሶ የማቋቋም ሥራ ሰላም እና ደኅንነት የማረጋገጡ ዋነኛ አካል እንደሆነና ሂደቱም ሊከተላቸው የሚገቡ መስፈርቶች እና መርሖች እንዳሉት ያስታወሱት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ “ይህንን የማድረጉን ሂደት የሚያስፈጽሙ የመንግሥት አካላት በተለይም የተጎዱ አካባቢ ነዋሪዎች እና ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ እንዲሁም የዚህን መሰል ሂደቶች አፈጻጸም እና በተጎጂ አካባቢዎች ላይ ያለውን ተጽዕኖ በቅርበት መከታተልን እኩል ትኩረት መስጠት ውጤታማ በሆነ መንገድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ለመከላከል ያስችላል” ብለዋል።

በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰባት አባላት ያሉትና በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ኮሚቴ፣ በመተከል ዞን ያለውን ሁኔታ ጎብኝቶ፣ ከሦስት ሺህ በላይ ታጣቂዎች እና በእነርሱ አማካኝነት “ጫካ ገብተው” የነበሩ ከ68 ሺህ በላይ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.