ዜና፡ በሱዳን ግጭት ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር አንድ ነጥብ አራት ሚሊየን መድረሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2015 ዓ.ም፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ በሱዳን በሁለቱ ጀነራሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር አንድ ነጥብ አራት ሚሊየን ተጠግቷል።

ሰባተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው የሱዳን ግጭት ሳቢያ በሱዳን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ሀገራት የተሰደዱ መኖራቸው እንደተጠበቀ ሁኖ በርካቶች ደግሞ በዚያው በሱዳን አንጻራዊ ሰላም ወዳለበት ቦታ በመሰደስ ተጠልለው እንደሚገኙ ሪፖርቱ አስታውቋል።

በሱዳን ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን በላይ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ተጠልለው ይኖሩ እንደነበር ሪፖርቱ አውስቷል።

ጾታዊ ጥቃት በተለይም ወሲባዊ ጥቃት በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት አመላክቷል። በሱዳን የተሰማሩ ሰብአዊ ረድኤት ድርጅቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የምግበ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ያስታወቀው ተመድ የጸጥታ እና የትራንስፖርት ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁሟል።  

እስከ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ቀናት ድረስ ከ345ሺ በላይ ሱዳናውያን ወደ አጎራባች ሀገራት በተለይም ወደ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ቻድ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ሪፖርት አመላክቷል።  

በምስራቅ ዳርፉር በሚገኝ አድ ዱአይን በተባለ ሆስፒታል ከሰላሳ በላይ ህጻናት በህክምና እጥረት በተለይም በኦክስጂን እጥረት መሞታቸውን ሲኤንኤን በዘገባው አስታውቋል። ከሞቱት ህጻናት መካከል ስድስቱ አዲስ የተወለዱ መሆናቸውንም ጠቁሟል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የሱዳን ስደተኞች በቀጥታ ወደ መጠለያ ካምፖች የሚገቡ ከሆነ ምንም አይነት ሰነድ እንደማይጠየቁ በሳለፍነው ሳምንት ማብቂያ በማህበራዊ ትስስር ትዊተር ገጹ አስታውቋል። ከመጠለያ ካምፕ ውጪ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለመንቀሳቀስም ሆነ ወደ ሶስተኛ ሀገር ለመሻገር የሚፈልጉ ማንኛውም ዜጋ የመግቢያ ቪዛ እንደሚጠየቅ አመላክቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.