ዜና፡ ትላንት በመርካቶ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል፤ 114 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል- የአዲስ አበባ ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2015 ዓ.ም፡- ትላንት ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ/ም ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች መስጂዶች ፈርሰዋል በሚል ምክንያት በመርካቶ ዙሪያ በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ህግ በማስከበር መደበኛ ሥራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሸገር ከተማ የመስጅድ ፈረሳ እንዲቆም በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ በወጣ ህዝብ ሙስሊም ላይ በተወሰደው እርምጃ ሂይወት ማለፉንና ብዙሃን መቁሰላቸውን ገልፆ ድርጊቱ  ፍፅም ተቀባይነት የሌለው ፣ኢ-ፍትሃዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው ሲል አወግዟል፡፡

ፖሊስ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ በተለምዶ ጋዝ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተፈጥሮ በነበረ ግርግር ሁለት ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ሆስፒታል ከተላኩ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል ብሏል፡፡ እንዲሁም አራት ግለሰቦች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ህግን ለማስከበር በተሰማሩ 37 የፖሊስ አመራርና አባላት እንዲሁም 15 የሚሆኑ የተለያዩ የፖሊስ አጋዥ ሀይሎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና የተላኩ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በሆኑ ሁለት አውቶቡሶች ላይም ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው ፖሊስ ብጥብጡን በመምራትና በማስተባበር እንዲሁም ዋነኛ ተሳትፎ የነበራቸው ያላቸውን 114 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በህግ አግባብ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አሰታውቋል፡፡

የነበረው ብጥብጥ በቁጥጥር ስር ውሎ አካባቢው ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጾ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አቅደው በተንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ የፀጥታ አካላት እየወሰዱት ያለውን እርምጃ አጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል ብሏል፡፡ የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስቧል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ህይወት እንዲጠፋና ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ የፅጥታ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል። በተጨማሪም የሚመለከተው አካል በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ እየተከናወነ ያለውን ድርጊት እንዲያስቆምና ወደ ውይይት በመምጣት ስር ነቀል የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ እንዲተገበር ጥሪ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱ በሸገር ከተማ መስጅድን በተመለከተ እየተከናወነ ያለው ድርጊት ሀላፊነት የጎደለው፤የህዝበ ሙስሊሙን ክብር ያዋረደ፤ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፤ የመንግስት የለውጥ ሪፎርምን ወደ ኃላ የሚመልስ በመሆኑ ጉዳዩ እንደ ሀገር ሊታሰብበት ይገባል ብሏል።

ለመላው ህዝበ ሙስሊም ፈጣሪ መፅናናትን እንዲሰጣቸው የተመኘው ምክር ቤቱ የከተማው ህዝበ ሙስሊም ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል አደራ ብሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.