ርዕስ አንቀፅ፡ በግልጽ የሚታዩ የአደጋ ምልክቶች ቢስተዋሉም መንግሰት አዳዲስ ክልሎችን ማዋቀሩን እንደቀጠለ ነው፤ አካሄዱን ገታ በማድረግ ዕቅዶቹን ማጤን ይገባዋል!

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12/ 2015 ዓ.ም፡- በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የተመራ ከፍተኛ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” በሚል ለሚደራጅው አዲስ ክልል አመሰራረት እቅድ ላይ ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ውይይት አድገዋል።

ኃላፊዎቹ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ እንዲጠቃለሉ መወሰኑን ቀድመው ጠቅሰዋል። እነደ እነሱ ገለፃ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጥምባሮ እና ሀላባ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል እንዲደራጁ ነው ውሳኔ ያስተላለፈው፡፡

ነገር ግን እስካሁን ድረስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ‘ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል’ በሚል ስያሜ ክልል እንዲመሰረት ይፋ ያደረገው ዶክመንትም ይሁን ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሄድ ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ የለም።

ከመነሻው ጀምሮ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች መግለጫ ችግር የነበረበት ነው፤ ምክንያቱም የዞኑም ሆነ የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ስለ ውሳኔው ስለማያውቁ፤ ሕገ መንግስቱ እውቅና በሰጠው አሰራር መሰረት አዲስ የክልል ማደራጀት ወይም ዞን እና ወረዳ ማዋቀር የሚቻልበት ህዝበ ውሳኔ እንኳ አልተካሄደም፡፡

ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው የክልሉ ኃላፊዎች ከፌዴራል መንግስት ይሁንታ ተሰጥቶት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወላይታ፣ ጋሞ፣ የጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች በጋራ ተደራጅተው ”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” በሚል ስያሜ አዲስ ክልል ለመመስረት ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ከአንድ አመት በፊት ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም የወሰነውን ውሳኔ በራሳቸው አንደ ጥሩ አጋጣሚ መጠቀማቸው ነው፡፡

ኃላፊዎቹ በራሳቸው የወሰኑት ውሳኔ ግልፅ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ብቻ ሳይሆን የአምስቱ ዞኖችና የአንዱ ልዩ ወረዳ ህዝቦች የሚሹትን የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና የማህበራዊ መረጋጋት መሰረታዊ መርሆችን ያዳከመ ነው።

ራስን በራስ የማስተዳደር የመብት ጥያቄ  በመጠቀም ጉራጌ ክልል እንዲሆን ሙሉ ድምፅ ከሰጡት አስራ አንዱ ብሔሮች ውስጥ ጉራጌ አንዱ ነው፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጉራጌ ህዝብ በመንግስት የተደገፈ ጭካኔ የተሞላበት ጭቆና ጥቃት ደረሶበታል። ለጉራጌ ህዝብ መብት ይሟገቱ የነበሩ የማህበረሰብ መሪዎችና አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ላይ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ እስራት እና መሰወር ያካተተ ተግባር ተፈፅሞባቸዋል። ይህ ሁሉ የተፈፀመበት የጉራጌ ህዝብ ጥያቄው ባለመመለሱ ያለማቋረጥ በተደጋጋሚ ጥያቄውን እያቀረበም ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ለለፉት በርካታ ሳምንታት የሀድያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጥምባሮ እና ሃላባ ዞኖች ህዝቦች በታቀደው የተቋማት መቀመጫ እና የቢሮ ክፍፍልን እቅድን በመቃወም የተቃዉሞ ድምፅ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳ እነዚህ በግልጽ የሚታዩ የአደጋ ምልክቶች ቢኖሩም፣ “የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል” ም/ቤት ምስረታ ጉባዔ ዝግጅት ተጠናቆ ኃላፊዎቹ ዛሬ ዓርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡

በጉባኤው የክልሉን ማዕከላዊ መዋቅርና በከተሞች የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶችን ድልድልን በሚመለከት ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች ወደፊት ግጭቶችን የመፍጠር አቅም አለው።

አንደኛ፤ በሕዝብ ይሁንታ ያልተቋቋመ ክልላዊ መንግሥት ሕጋዊነት ይጎድለዋል። በመንግስት ላይ እምነት ማጣትንም ያመጣል፤ ይህም አለመረጋጋት እና የስልጣን ፈተናዎችን ያስከትላል፡፡

ሁለተኛ፤ ከላይ እስከ ታች ያለው የአንድ ወገን ውሳኔ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጡትን መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መርሆችን መጣስ ነው። በዚህ መንገድ የሚዋቀሩ የመንግስት መዋቅሮች ለሕዝብ ተጠያቂ ባለመሆናቸው ለዜጎች መብትና ነፃነት ቅድሚያ መስጠት የሚሳናቸው ሲሆን ይህም አምባገነናዊ አገዛዝ፣ ሳንሱር፣ አድሎና ሌሎች የስልጣን በደሎች የሚያስከትል መሆኑ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው።

ሶስተኛ፤ ይህ በዞኖቹ ውስጥ ላለው ህዝብ ፍላጎት ክብር አለመስጠትን የሚያሳይ ሲሆን ይህም የማህበረሰቦቹን ስጋት እና ምኞቶች ወደማይፈቱ ፖሊሲዎች በማምራት በመጨረሻም መነጣጠልን እና ማህበራዊ መከፋፈልን ይፈጥራል፡፡

ባጠቃላይ ከህዝቡ ሙሉ ፍላጎት ውጭ የክልል መንግስት ለመመስረት መወሰን በተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ ያለውን የጋራ የሀይማኖት እና የባህል ውጥረት ያባብሳል። በክልሉ ውስጥ ያሉ ቡድኖች መገለል እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፉ በማድረግ አሳሳቢ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ውጥረቶች እና ግጭቶች እንዲከሰቱ ያደርጋል።

ፍላጎት ለፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ የቡድን እና የግለሰብ መብቶች መሰረታዊ መርህ ሆኖ በኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ማዕቀፍ ስር ተካቷል፡፡

የፌደራልም ሆነ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መስተዳድሮች በሕገ መንግሥቱ መሰረት ራስን በራስ ከማስተዳደር በቀር ሌላ ጥያቄ ባላቀረቡ ማኅበረሰቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር ቀስቃሽ ምክንያት ከመሆን ይልቅ አዲስ ክልላዊ መንግስት መመስረቱ ወደ ፍትሃዊ፣ የተረጋጋ እና ሰላማዊ ክልል እንዲመራ ለማረጋገጥ መለስ ብለው ውሳኔውን እንደገና ማጤን አስፈላጊ ነው።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.