በማህሌት ፋሲል
አዲስ አበባ መጋቢት 12/2014 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ቅርንጫፍ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ዳኞች በዛሬው እለት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የቀርበውን ለቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ለቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የምስክርነት ቃላቸውን በበይነ መረብ እንዲሰጡ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ ፈቀደ።
በሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው የክስ መዝገብ አራት ተከሳሾች በ319.4 ሚሊዮን ብር የትራክተር ግዥ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በአሁኑ የኢጋድ ዋና ዳይሬክተር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፤ የቀድሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር እና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ድሪባ ኩማ (አምባሳደር) እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በመከላከያ ምስክነት ተቆጠሩ ሲሆን ሁሉም ምስክሮች ቀርበው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ጠይቋል።
ሜቴክ ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ገዝቷል የተባሉትን ሁለት መርከቦችን በሚመለከት በመከላከያ ቡድኑ ምስክርነታቸው የሚፈለግ ሲሆን አቃቤ ህግ እንደሚለው መርከቦቹ አገልግሎት ላይ ከዋሉ ከ28 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ በመሆናቸው በ60 ሚሊዮን ብር በተጭበረበረ መንገድ መገዛት ያልነበረባቸው ሲሆኑ በዚህም መንግስት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል በማለት ይከሳል።
የተጭበረበረ ነው ከተባለው የትራክተሮች ግዢ ጋር በተያያዘ የምስክርነት ቃላቸውን የተጠየቁት የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ከሀገር ውጪ በመሆናቸው ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳልቻሉ ለፍርድ ቤቱ ደብዳቤ አስገብተዋል።
ዳኞች ጥያቄውን ተመልክተው ከፍርድ ቤቱ አመራሮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ዛሬ ጥያቄውን ተቀብለው በሂደቱ ላይ ከአቃቤ ህግ እና ከተከሳሽ ጠበቆች ጋር እንዲመክሩ ወስነዋል። ዳኞቹ ከቀድሞው ጠ/ሚ ኃይለማርያም በተጨማሪ በቀድሞው አሁን በአሜሪካ የሚኖሩትን አምባሳደር ፍስሃ አስገዶም የበይነ መረብ የምስክርነት ጥያቄ ተቀብለዋል።
ከተዘረዘሩት የመከላከያ ምስክሮች መካከል የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በዋለው ችሎት ፍርድ ቤት ቀርበው የትራክተሮቹ ግዥ ሂደት ላይ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ባለፈው አመት በሚያዝያ ወር በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ሜጀር ጀነራል ክንፈ የትራክተሮቹ ግዥ በቀድሞው ጠ/ሚ ኃይለማርያም ይመራ ነበር ሲሉ መከራከራቸው ይታወሳል።
በዚሁ መዝገብ የቀረቡት ሌላው የመከላከያ ምስክር የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ሲሆኑ፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ለፍርድ ቤቱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የችሎቱ ሂደት ዳራ
የሜ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ክስ ከአራት አመት በፊት የጀመረው ከ60 በላይባብዛኛው ከኢትዮጵያ መረጃ እና ወታደራዊ መዋቅር የተውጣጡ ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር በማዋል ሲሆን 40ዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት አርብ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ᎐ም መሆኑ ይታወሳል።
የወቅቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበሩት ብርሃኑ ፀጋዬ ቁጥጥር ስር የዋሉትን ተጠርጣሪዎችን ተፈጽሟል በተባሉ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና በኢህአዴግ ዘመን በሠራዊቱ ይመራ በነበረው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ውስጥ ነበራቸው በተባለ የሙስና ትስስር ወንጀል መክሰሳቸውም ይታወሳል።ጠቅላይ አቃቤ ህጉም በሦስት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምርመራ እየተካሄደ እንደነበር በመጥቀስ ሲዘረዝሩም፥ አዲስ አበባ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ᎐ም በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦምብ ጥቃት ምርመራ፤ በቅድመ-አብይ አህመድ የኢህአዴግ መር የደህንነት፣ የመረጃ እና የፖሊስ ክፍሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ ላይ የተደረገ ምርመራ፤ እንዲሁም በሜቴክ ውስጥ አሉ የተባሉ የሙስና አውታሮች ላይ ምርመራዎች መሆናቸውንም ጠቁመው እንደነበር አይዘነጋም። አስ