ትንታኔ: በሽግግር ፍትህ ሰነዱ የሚታዩ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ተግራባራዊ እንቅፋቶች

በአብዲ ቢያንሳ@ABiyenssa

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30/2015 ዓ.ም፡- የትግራይ ጦርነት መቆም በኋላ የፌደራሉ መንግስት አካታች የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነድ ይፋ አድርጓል። ባለፈ ታሪኮቿ ሳቢያ በፈተና ለምትናወጠው ኢትዮጵያ የፖሊሲው መዘጋጀት መፍትሔ ለማስገኘት በምታደርገው ጥረት ወሳኝ መዕራፍ እንደሆነ በመገለጽ ላይ ይገኛል። ነገር ግን ሰነዱ ወሳኝ ነገሮች መያዙ እንደተጠበቀ ሁኖ ጥያቄዎች ግን ተነስተውበታል። በመነሳት ላይ ያሉት ጥያቄዎቹም በዋነኝነት የሚያጠነጥኑት በተግባራዊነቱ ላይ እና በድህረ ግጭት ፍትህ እንዲሁም ተጠያቂነትን በማስፈን ዙሪያ ነው።

ከጥር ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ አስፈላጊነት በሚል መጠሪያ የቀረበው ረቂቅ ሰነድ ለባለ ድርሻ አካላት ለውይይት ቀርቧል። ሰነዱ ሰፊ ጉዳዮችን እንዲያካትት ተደርጓል። ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በሀሪቱ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በማየት እና ተጠያቂነትን በማስፈን እንዲሁም እርቅ ማውረድ የሚል ተካቶበታል። ሰነዱ ውዳሴ የማግኘቱን ያክል በባለሞያዎች ዘንድ ደግሞ በተግባራዊነቱ እና በአቀራረቡ ረገድ ጥያቄዎችን ቀስቅሷል።

በቅርቡ አዲስ ስታንዳርድ የሰብአዊ መብት እና ሽግግር ፍትህ ሙሁራንን አነጋግሮ ነበር። ሁሉም ባለሞያዎች በሰነዱ ላይ ያላቸውን ስጋት አጋርተውናል። የስጋታቸው ምንጭም ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ሲገባ የሚያጋጥመው መሰናክሎች እና ለሰነዱ መዘጋጀተ አስገዳጅ የሆኑ መክንያቶች ናቸው።

የህግ ባለሞያ እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃ/ማሪያም ሰነዱ ሀገሪቱ የገባቸበትን የተወሳሰበ የፖለቲካ ቀውስ እና የሰብአዊ መብት ጥሰትን ለመጋፈጥ ወሳኝ የሆነውን አንጻራዊ ተሞከሮ ይጎድለዋል ሲሉ ይተቻሉ።

የሰነዱን ችግር አቶ ያሬድ በተጨማሪ ሲያስረዱ ሰነዱ ይበልጥ ትኩረት ለብሔራዊ ሉአላዊነት መስጠቱ አለም አቀፍ ተዋናዮችን እና ሂደትን ለማግነል ነው ሲሉ ይገልጻሉ። ሰነዱ ለሽግግር ፍትህ ወሳኝ የሆኑትን አለም አቀፍ ተዋናዮችን እና ሂደትን ማግለሉን ተችተዋል። በተለያዩ አለማችን ክፍሎች የሽግግር ፍትህን በማሳለጥ ረገድ ልምድ ያካበቱ አለም አቀፍ ተዋናዮች ይህንን የሽግግር ፍትህ ለማሳለጥ አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ይህንን ሀሳብ የሰብአዊ መብት ጠበቃ እና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት መርጋ ፈቃዱ እንደሚጋሩት ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ሰነዱ የሉአላዊነትን ጽንሰ ሀሳብ ከመንግስት ውጭ የሆኑ ተዋናዮችን ለመገደብ ተጠቅሞበታል ሲሉ በመግለጽ እንደ አፍሪ ህብረት ያሉ ለትግራዩ ጦርነት መቆም አስተዋጽኦ ያደረጉት ገለል ሊደረጉ አይገባም ብለዋል።

በተጨማሪም የሲቪል ማህበራት ለሂደቱ አስፈላጊ መሆናቸውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት መርጋ ፈቃዱ ህዝባዊ ምክክሮችን ለማመቻቸት፣ እርቀ ሰላም ለማስፈን እና በመሰረታዊ ደረጃ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ከሁለቱ ሙሁራን በተጨማሪ በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የህግ ክፍል የሰብአዊ መብት ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት አባድር ኢብራሂም በበኩላቸው የፖሊሲው ረቂቅ ሰነድ ጽንፍ የያዘ ብሔራዊ አቋም በመላበሰ ለሉአላዊነት እና ለብሔራዊ ክብር ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው ይህም በመንግስት በኩል ለድርድር የማይቀርበውን የአለም አቀፍ ተዋናዮችን እና ሂደትን የማግለል ተግባር ለማስረገጥ መዋሉን ገልጸዋል።

በመንግስት ዘንድ ጉዳዩ ለድርድር እንደማያቀርበው ለማሳየት በተጠናከረ መልኩ የተባበሩት መንግስታት ያቋቋመው መርማሪን ጨምሮ ገለልተኛ ምርመራ እንዳይካሄድ ሲያደርግ እና ሲከላከል መቆየቱን በማሳያነት አስቀምጠዋል።

አባድር ኢብራሂም በተጨማሪ እንዳመላከቱት ሰነዱ በውስጡ እንዲይዝ የተደረገው ፍሬ ሀሳብ የተቃኘው እና የተዘጋጀው በፍትህ ሚኒስቴር መሆኑን በመጥቀስ ችግሩን ለማሳየት ጥረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለፉ/የቆዩ ችግሮችን እንዲካተቱ ማድረጉ በተአማኒነቱ እና ገለልተኝነቱ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጉን አመላክተዋል።

በተጨማሪም ከሰነዱ በመነሳት እንዲሁም ይፋ ከተደረገው መረጃ መሰረት ሂደቱ የሚከናወነው በፖለቲካ ተዋናዮች እና ባለድርሻ አካለት ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱ ግልጽነት የለውም፤ ይህም በፍትህ ሚኒስቴር ባለቤትነት ቢካሄድ እንኳን ለቀጣይ የፖለቲካ መረጋጋት እና ለሽግግር ፍትሁ የሚኖረው አስተዋጽኦ ግልጽ አይደለም ብለዋል።

ከሽግግር ፍትህ በፊት መቅደም ያለበት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ሽግግር ነው ሲሉ የገለጹት አባዲር የኦሮምያ እና አማራ ክልሎች ጨምሮ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠኝ በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ ዝግጁ አይደለችም ሲሉ ገልጸዋል። ሀገሪቱ በግጭት ውስጥ ነች የምትገኘው ያሉት አባዲር የሽግግር ፍትህ በባህሪው ከግጭት ጋር አይሔድም፤ ስለዚህም ሂደቱን የበለጠ የተወሳሰበ ያደርገዋል ብለዋል።

አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ጦርነት ወይንም ጦርነቶች ለጉዳዮች ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ሲሳን የሚፈጠሩ መሆናቸውን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን ያሉተ ሙሁሩ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መረጋጋትን የማታገኝ ከሆነ ጦርነቶቹ ቀጣይ እንደሚሆኑ ልናምን እንደሚገባ አስታውቀዋል። ይህም የሽግግር ፍትህ እርባና ቢስ እንዲሆን ያደርገዋል፤ የሽግግር ፍትህ የሚያስፈልገው አንድን ሀገር ከአንባገነናዊነት ወደ ዲሞክራሲ ወይንም ከጦርነት ወደ ሰላም ለማሸጋገር ነውና ብለዋል።

የሀገሪቱ የፖለቲካ ተዋናዮች ንግግራቸው በጦርሜዳ ላይ ከሆነ በሰላማዊ ሁኔታ ለመወያየት እስኪወስኑ ድረስ የሽግግር ፍትህ ሀሳብ መቆየት አለበት፤ ያ ሰላም ለዲሞክራሲያዊ ሂደት የራሱ አስተዋጽኦ ይኑረው አይኑረው እንደተጠበቀ ሁኖ ማዘግየቱ ይሻላል ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ አባድር ሁሉ መርጊያ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሽግግር ፍትህ ለማካሄድ አመች ነው ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ። በግልጽ ሲያስቀምጡትም ለሽግግር ፍትህ መኖር ወሳኙ የፖለቲካ ሽግግርን እንደ መንስኤ ስንጠቀምበት መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም አሁናዊው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በግጭት እና ክፍፍል የተመሰረተ በመሆኑ የሽግግር ፍትሁን ያደናቅፈዋል ሲሉ አመላክተዋል።

ለሰነዱ ተጨማሪ ችግር እንደ መርጋ ገለጻ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ከ1983 በኋላ ያለውን ብቻ እንዲያካትት መደረጉ ነው፤ ታሪካዊ የፍትህ መዛባቶች እና ቁርሾወች በሀገሪቱ አሉ፤ ይህም በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ተጭኖታል፤ ጽንፍ የያዘ የፖለቲካ አመለካከት እና ግጭት እንዲሰፍንም አስተዋጽኦ አለው ሲሉ አብራርተዋል።

ሌላኛው በሰነዱ የታየው ትልቅ ችግር ጦርነቱ በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮምያ እና ሌሎች ክልሎች ያስከተለው ውድመት በስርአት አለመቅረቡ ነው ሲሉ ያሬድ እና መርጋ ይገልጻሉ።

የውድመቱ መጠን፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ፣ ጦርነቱ በህጻናት እና ሴቶች ያስከተለው ተጽእኖ፣ የተጎጂዎችን እና አጥፊዎች ልየታ የመሳሰሉት በሰነዱ በግልጽ ተለይተው አልተቀመጡም ሲሉ መርጋ ገልጸዋል።

በተጨማሪ ያነጋገርናቸው ባለሞያዎቹ በተቋማቱ በተለይም መከላከያ፣ ፖሊስ፣ አና ፍትህ አካላት ላይ የሽግግር ፍትሁን ለማስፈጸም ያላቸውን ገለልተኝነት እና ብቃት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። እነዚህ ተቋማት በግጭቱ ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ሲፈጸም እና ጭቆናው ሲደረግ መሳሪያ ሁነው ያገለገሉ ናቸው፤ የሽግግር ፍትሁ እንዲሳካ እነዚህ ተቋማት እንደገና ሊደራጁ ይገባል ሲሉ አቶ ያሬድ ይገልጻሉ።

ወታደራዊ ክፍሉ፣ የፍትህ ስርአቱ እና በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሁለት ምክንያቶች ለሽግግር ፍትሁ ዝግጁ አይደሉም የሚል ምክንያት አለኝ ያሉት አባድር የመጀመሪያው የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ለዚህ ግዙፍ ተልዕኮ የሚመጥን ብቃት፣ ክህሎት እንዲሁም መሰረታዊ የሰው ሀይል አላቸው የሚል እምነት የለኝም፤ ሁለተኛ ደግሞ እነዚህን ተቋማት የተቆጣጠሯቸው እና የሚመሯቸው አምባገነኖች በመሆናቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

እነዚህ ትችቶች እንደተጠበቁ ሁነው ሰነዱ መዘጋጀቱ ብቻ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ ሙሁራኑ ይገልጻሉ። ረቂቅ ሰነዱ የሚሰራ ነው ሲሉ የገለጹት ያሬድ ይህ የሚሆነው ግን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ አባድር የሰነዱን ቴክኒካል ክፍል ያላቸው አድናቆት ገልጸው ለሽግግር ፍትህ አስፈላጊ የሆኑት ግብአቶች እና አማራጮችን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል። አሳሳቢው ነገር መንግስት በእውነት የሽግግር ፍትህ ሂደት እንዲኖር ይፈልጋል ወይ የሚለው ነው ያሉት አባድር በተጨማሪም መንግስት በራሱ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ እና ፍትህ እንዲሰፍን ቁርጠኛ ነው ወይ የሚለው እንደሚያሳስባቸው አመላክተዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.