ጤና/ቃለ ምልልስ፡  “የኩላሊት መድከምን ለመከላከል ዋነኛው መፍትሔ ለኩላሊት በሽታ ሊዳርጉ የሚችሉ መንስዔዎችንና አጋላጭ ሁኔታዎቸን አስቀድሞ መከላከል እጅግ ጠቃሚ ነው” – ዶ/ር ለጃ ሐምዛ የዉስጥ ደዌና የኩላሊት ስፔሻሊስት ሐኪም

ዶ/ር ለጃ ሐምዛ_ በቅዱስ ፓውሎስ ሆሰፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የዉስጥ ደዌ ህክምና ትምህርት ከፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኩላሊት ስፔሻሊስት ሐኪም

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7/2015 ዓ.ም፡- የኩላሊት ህመም ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጎላ የመጣ በሽታ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የኩላሊት ህመም ከፍተኛ ወጭን የሚጠይቅ ህመም በመሆኑ ብዙሃኑን ስጋት ውስጥ የሚከት ህመም ነው፡፡በአሁኑ ሰዓትም በአገራችን በዚህ በሽታ እየማቀቁ የሚገኙ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ በቂ ገንዘብ አጥተው በየእለቱ ምገድ ላይ ወጥተው እንዲሁም በየማህበራዊ ሚዲያ ገንዘብ የሚለምኑ በርካቶች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ኩላሊት እጥበት ለማድረግ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ሆነው ህመሙ ለከፋ ችግር የዳረጋቸውም ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡

ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጎላ ከመጣው የኩላሊት በሽታ ራስዎንና ቤተሰቦን እንታደጉይረዳችሁ ዘንድ በቅዱስ ፓውሎስ ሆሰፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የዉስጥ ደዌ ህክምናና ትምህርት ከፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኩላሊት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ለጃ ሐምዛ ጋር ቆይታ አድርገኛል፡፡ ዶ/ር ለጃ ከኩላሊት ህመም እራስንና ቤተሰብን መታደግ በሚቻለበት ጉዳዮች ላይ ከአዲስ ስታንድርዱ ጋዜጠኛ ብሩክ አለሙ ጋር ያጋደረጉት ሙሉ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ፡ የኩላሊት በሽታ ማለት ምን ማለት ?

ዶ/ር ለጃ፡ ስለ ኩላሊት በሽታ ከማብራራቴ በፊት ስለ ኩላሊት ዋና ዋና ተግባራት ማስታወሱ ይበልጥ እንድንግባባ ይረዳናል፡፡ማንኛውም ጤነኛ ሰው ሁለት ኩላሊቶች አሉት፡፡ እርግጥ ነው ከስንት አንዴ በተፈጥሮ አንድ ኩላሊት ብቻ ኖሯቸው የሚወለዱ ሰዎች ቢኖሩም በአንድ ኩላሊት ጤነኛ ሆነው መኖር ይችላሉ፡፡ ኩላሊቶቻችን ጤነኛ ሆነን እንድንኖር ፈጣሪ  ከሰጠን ጸጋዎች ውስጥ በጉልህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የዘወትር ጤናችን ሳይስተጓጎል ጤናማ ህይወት እንድንኖር  ኩላሊቶቻችን ድንቅ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ ዋነኞቹ ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፤

 • የደም ግፊታችን የተስተካከለ እንዲሆንና በሰውነታችን ውስጥ ያለው የፈሳሽ መጠን ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ፤
 • ለዕለት ተዕለት የህዋሶቻችን ጤናማ ተግባራት እጅግ ወሳኝ የሆኑ ንጥረ-ነገሮች (electolytes) እንዳዪዛቡ ሚዛን መጠበቅ፤
 • ለደም ህዋሶች መመረት የሚያስፈልጉ እንዲሁም ለዕለት ተዕለት የህዋሶቻችን ጤናማ ተግባራት እጅግ ወሳኝ የሆኑ ንጥረ-ቅመሞችን  (hormones) ማምረት፤
 • ለአጥንት ጥንካሬና ለጥርስ ጤና እጅግ ወሳኝ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን ማለትም እንደ ቫይታሚን ዲ ፤ ካልሺየም እና ፎስፈረስ የተባሉ ንጥረ-ቅመሞችን ማምረትና ሚዛናቸውን መጠበቅ፤ እና
 • በሰውነታችን ዉስጥ የሚመረቱም ሆኑ ወደሰውነታችን ከምግብና መጠጥ ጋር አሊያም በመድሃኒት መልክ የገቡ ለጥና ጎጂ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን ከሽንት ጋር ማስወገድ፡፡

እንግዲህ ኩላሊቶቻችን እነዚህን ተግባራት በአግባቡ ለማከናወን እንዳይችሉ የሚያስተጓጉሉ ማናቸውም ጉዳቶች ወይም በሽታዎች የኩላሊት በሽታን ወይም መድከምን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

አስ፡ የኩላሊት መድከም ማለት ምን ማለት ነው?

ዶ/ር ለጃ፡ ኩላሊቶቻችንን የሚጎዱ በርካታ በሽታዎችና አጋላጭ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ በሽታዎች ኩላሊቶቻችን ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት እንዳያከናውኑ በማድረግ ለኩላሊት መድከም ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ የኩላሊት መድከም ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው አጣዳፊ ወይም ጊዜያዊ (AKI = Acute Kidney Injury) ሲሆን ሁለተኛው ስር የሰደደ (CKD = Chronic Kidney Disease) የምንለው ነው፡፡

አስ፡ አጣዳፊ ወይም ጊዜያዊ የኩላሊት መድከም (AKI = Acute Kidney Injury) ምን ማለት ነው? መንስዔዎቹስ?

ዶ/ር ለጃ፡ አጣዳፊ ወይም ጊዜያዊ (AKI) የኩላሊት መድከም ማለት ስሙም እንደሚያመለክተው በድንገት የሚከሰቱ የጤና እክሎች ኩላሊትን በከፍተኛ ደረጃ ሲጎዱና የዘወትር ተግባራቱን እንዳያከናውን ሲያደርጉት ነው፡፡ ለዚህም በርካታ መንስዔዎች ቢኖሩም ዋነኞቹ በአደጋም ሆነ በወሊድ ወቅት ከባድ የደም መፍሰስ፡ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት፤ ከባድ የኩላሊት ኢንፌክሽን፤ ድንገተኛና አጣዳፊ የኩላሊተ ማጣሪያ ክፍል መቆጣት ( Acute Glomerulonephritis)፤ የሽንት ትቦና ፊኛ በድንገት መዘጋት (በዕጢ ፤ በጠጠር፤ በአደጋ… ሊሆን ይችላል) ናቸው፡፡ ይህኛው ዓይነት ድክምት በፍጥነትና ባግባቡ ከታከም ሊያገግምና ሊድን የሚችል ነው፡፡

አስ፡የአጣዳፊ/ድንገተኛ ኩላሊት መድከም (Acute Kidney Injury) ዋነኛ መገለጫ ምልክቶች ምንድ ናቸው?

ዶ/ር ለጃ፡ ምልክቶቹ እንደየጉዳቱ ደረጃና መንስዔ ይለያያሉ፡፡ ከአጋላጭ ሁኔታዎቹ ወይም መንስዔዎቹ ምልክቶች በቅድሚያ ይከሰታሉ፡፡ ተከትሎም በጉዳቱ ሳቢያ ኩላሊቶች ተግባራቸውን ባለመወጣታቸው የሚከሰቱ ምልክቶች መከሰት ይጀምራሉ፡፡ ማለትም የሽንት ቀለም መቀየር፡ መጠን መቀነስ ብሎም ጭራሽ መጥፋት፡ የሰውነት ማበጥ፡ የትንፋሽ ማጠር …. በመጨረሻም ራስን እስከመሳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ 

አስ፡ ሥር የሰደደ የኩላሊት መድከም (CKD = Chronic Kidney Disease) ማለት ምን ማለት ነው? መንስዔዎቹስ?

ዶ/ር ለጃ፡ ይሄኛው ዐይነት የኩላሊት ድክምት በድንገት ሳይሆን በረጂም ጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ የሚከሰት ሲሆን አንዴ ከተከሰተ ወደ ሁዋላ የማይመለስና የማያገግም ነው፡፡ ለዚህ የሚዳርጉ በርካታ መንስዔዎች ቢኖሩም በሃገራችንም ሆነ በዓለም-ዓቀፍ ደረጃ ዋነኞቹ የስኳር በሽታ፡ ደምግፊት፤ ልዩ ልዩ የኩላሊተ ማጣሪያ ክፍልን የሚያስቆጡ በሽታዎች (Chronic Glomerulonephritis = CGN)፤ በተፈጥሮ የሚከሰቱ አንዳነድ የኩላሊተ በሽታዎች (Inherited/Genetic Kidney Disorders e.g. Polycystic Kidney disease) ፤ በአግባቡ ያልታከመ ስር የሰደደ/ተዳጋጋሚ የኩላሊት ኢነፌክሽን ፤ ኩላሊትን ሊጎዱ የሚችሉ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ መድሃኒቶችን ያለሀኪም ትዕዛዝ በተደጋጋሚ መውሰድ፤ እና ሥር የሰደደ ተደጋጋሚ የሽንት ትቦና ፊኛ መዘጋት (በዕጢ ፤ በጠጠር፤ በኢንፌክሽን … ሊሆን ይችላል) ናቸው፡፡

እነዚህ በሽታዎች ለኩላሊት ድክመት የሚዳርጉት በረጂም ጊዜ ሂደት (በርካታ ወራትና ዓመታት) በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱት መንስዔዎች ያሉበት ሰው በስፔሻሊስት ሃኪም የታገዘ ተገቢዉን ህክምናና ክትትል የሚያደርግ ሰው ለኩላሊት ድክምት የመዳረጉን ዕድል በእጅጉ መቀነስ ይችላል፡፡

ሥር የሰደደ የኩላሊት መድከም (CKD = Chronic Kidney Disease) አምስት ደረጃዎች አሉት፡፡ ደረጃዎቹ የሚወሰኑት የኩላሊቶቻችን የማጣራት አቅም በምን ያህል መጠን ቀነሰ በሚል ልኬት ነው፡፡

አስ፡ ሥር የሰደደ የኩላሊት መድከም (Chronic Kidney Disease) ዋነኛ መገለጫ ምልክቶች ምንድ ናቸው?

ዶ/ር ለጃ፡ ደረጃ አንድ የኩላሊት መድከም ጉዳቱ መጠነኛ ሲሆን ምንም ምልክት ላይኖረው ይችላል፡፡ ደረጃ ሁለትም እንዲሁ፡፡ በዚህም ሳቢያ ብዙ ታካሚዎች ኩላሊታቸው መድከሙን ሳያውቁ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ ደረጃው እየጨመረ ሲሄድ በተለይም ከደረጃ ሶስት በኋላ የኩላሊት ተጋባራት መዛባትና የሚከሰቱት የጤና ችግሮችም እንደየደረጃው እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ ድካምና አቅም ማጣት፤ የጨጓራ ህመምና የምግብ ፍላጎት መቀነስ፡ ማሳከክ፤ የሽንት መጠን መቀነስ፤ የሰውነት ማበጥ፤ ሳል፤ ትንፋሽ ማጠር፤ እና የመሳሰሉት ምልክቶች እየጎሉ ይመጣሉ፡፡ ደረጃ አምስት የመጨረሻው ደረጃ (ESRD = End Stage Renal Disease) ሲሆን የኩላት የማጣራት ዓቅም እጀግ ስለሚቀንስ የሚከሰቱት የጤና ችግሮችና የሚታዩት የበሽታ ምልክቶችም እየጨመሩና እየከበዱ ይመጣሉ፡፡ በመጨረሻም በጤናና በህይወት ለመቆየት የኩላሊት ዕጥበት ህክምና መጀመር ወይም የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ማድረግ ብቸኛው መፍትሄ ይሆናል፡፡  

አስ፡ የኩላሊት መድከምን እንዴት መከላከል ይቻላል፤ ህክምናውስ?

ዶ/ር ለጃ፡ ዋነኛው መፍትሔ ለኩላሊት በሽታ ሊዳርጉ የሚችሉ መንስዔዎችንና አጋላጭ ሁኔታዎቸን አስቀድሞ መከላከል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይም እንደ ደም ግፊትና ስኳር ያሉ የታወቁ መንስዔዎችንና አጋላጭ ሁኔታዎች ያሉበት ሰው ተገቢውን ቋሚ ህክምናና ክትትል በተገቢው ስፔሻሊስት ሃኪም ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህም ወቀት ሊከናወኑ የሚችሉ ዋነኛ የህክምና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፤

 • ሥኩዋርና ደም ግፊትን በአግባቡ መቆጣተር፤
 • ተያይዘው ሚከሰቱ የጤና እክሎችን መከላከልና ማከም ( የደም ማነስ፤ ድካም፤ የቆዳ ድርቀትና ማሳከክ፤ የምግብ ፍላጎት ማጣትና ማቅለሽለሽ፤ የሰውነት ዕብጠት፤ የሽንት መጠን መቀነስ….)
 • የመድሃኒት አወሳሰድን ማስተካከልና ኩላሊትን ሊጎዱ የሚችሉ መድሃኒቶችን አለመውሰድ፤
 • ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ማስወገድ፤ ከደባል ሱሶች መታቀብ፡
 • አመጋገብን ማስተካከል፤ በተቻለ መጠን ንጽህናው የተጠበቀ፤ የተመጣጠነ፤ ቤት ውስጥ የተዘጋጀ ምግም መመገብ የመከራል፡፡ ጨው ፤ ቀባት፤ የስጋ ውጤቶች፤ የወተት ተዋጽኦ ፤ ፍራፍሬና የታሸጉ ምግቦችን በጣም መቀነስ ጠቃሚ ነው፡፡ በአጠቃላይ አመጋገብን በባለሙያ የታገዘ ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ እና
 • በየመሃሉ የሚከሰቱ ተጓዳኝ በሽታዎችን ባፋጣኝና ባግባቡ መታከም… ኩላሊትን ሊታደጉ ከሚችሉ ተግባራት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

አስ፡ በየመንገዱ እና በማህበራዊ ሚዲያ ለኩላሊት ህመምተኞች ገንዘብ ሲለመን በስፋት ይስተዋልል። ከሌሎች ህመምተኞች በተለየ የኩላሊት ህመምተኞች በስፋት ሲለምኑ የሚስተዋለው በምን ምክኒያት ነው? የህክምና ወጭው ይህን ያክል ወድ የሆነበት ምክኒያትስ ምንድነው?

ዶ/ር ለጃ፡ እውነት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኩላሊት መድከም በሽታ ሰለባ ሆነው፤ የህክምናውን ወጪ መሸፈን ተስኗቸው፤ የአድኑኝ የዕርዳታ ጥሪ በየመንገዱና በየሚዲያው የሚያሰሙ ድምጾችን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህም የበሽታው ስርጭትና አሳሳቢነት እየጨመረ መምጣት ብቻ ሳይሆን የህክምናው ወጪ ፈታኝነትም ያሳያል፡፡ ይህም የሆነው የኩላሊት መድከም በሽታ ከሌሎች መሰል በሽታዎች የተለየ ሆኖ ሳይሆን የሚሰጡት ህክምናዎች ዉድ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የረጅም ጊዜ ክትትልና ቋሚ ወጪ ስለሚሹ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የቅድመ ጥንቃቄና የመከላከል ህክምናዎች ተደርገውም ቢሆን በጊዜ ሂደት የኩላሊት ድከመቱ ተባብሰሶ የመጨረሻው ደረጃ ሲደርስ የኩላሊት ዕጥበት ህክምና (Hemodialysis) ወይም የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ህክምና ማድረግ በህይወትና በጤና ለመቆየት የግድ ይሆናል፡፡ እነዚህ ህክምናዎች ደግሞ እጅግ ውድ ናቸው፡፡ በርካታ የህክምና መሳሪያዎችን፤ ግብዓቶችንና፡ የሰለጠን የሰው ሃይል ይፈልጋሉ፡፡

 የኩላሊት ዕጥበት ህክምና (Dialysis)

የኩላሊት መድከም የመጨረሻ ደረጃ ሲደርስ ለህይወት አሰጊ የሆኑ በርካታ የጤና ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ታካሚውን ከስቃይ ለመታደግና በህይወት ለማቆየት የተዛቡትን የኩላሊት ተግባራትን ማስተካከል የግድ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው የኩላለትን ተግባራት ተክቶ በሚሰራው ማሽን አማካይነት የኩላሊት ዕጥበት ህክምና በማረግ (Hemodialysis) ነው፡፡ የኩላሊት ዕጥበት ህይወት አድን ህክምና ነው፡፡ በከፍተኛ ስቃይና በሞት አፋፍ ላይ የነበሩ በርካታ ታካሚዎች በዲያሊሲስ ህክምና አማካይነት ድነው ጤናማ ህይወት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኩላሊት መድከሙ ጊዜያዊ ወይም አጣዳፊ ከሆነ ዲያሊሲሱ የሚያስፈልገው ጊዜያዊ ጉዳቱ እስኪያገግም ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የኩላሊት ድክመቱ ስር የሰደደ ከሆነ ግን ጤናማ ሆኖ በህይወት ለመቆየት ሕክምናው በሳምንት ሶስቴ ለአራት ሰዓታት በቋሚነት መቀጠል አለበት፡፡

ዲያሊሲስ ውጤታማ ህይወት አድን ህክምና ቢሆንም ወጪው ቋሚና ወድ ከመሆኑ አንጻር የቤተሰብን የኢኮኖሚ አቅም በእጅጉ ይፈትናል፤ የኑሮንም ሁኔታ ያናጋል፡፡ ለዚህም ነው በርካቶች ለአደባባይ ልመና የተዳረጉት፡፡ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት መንግስት፤ የዕርዳታ ድርጅቶች፤ ባለሃብቶችና አቅሙ ያላቸው ወገኖች በሙሉ የነዚህን ታካሚዎቻችን ህይወት ለመታደግ የተለመደውን ትብብራቸውን ይበልት አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡

አስ፡ ስለ የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ህክምና (Kidney Transplant) ማብራሪያ ይስጡን?

ዶ/ር ለጃ፡ ሌላው አማራጭ ህክምና የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ነው፡፡ ኩላሊትን መለገስ አንድ ሰው ለሚወደው ሰው ሊሰጣቸው ከሚችላቸው ውድ ስጦታዎች ዋናው ነው! ይህ ውድ ስጦታ እንዳይባክን የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ወስብስብ ሂደት ያለው ውድ ህክምና ነው፡፡ ንቅለ-ተከላው የተሳካ ይሆን ዘንድ ኩላሊተ ለጋሸና ተቀባይ የሚያለፉባቸው ሁለንተናዊ የምርመራ ሁደቶች አሉ፡፡ በዚህ የምርመራ ሂደት መሟላት ያለባቸው ዋናዋና ቅድመሁኔታዎች/ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፤

 • የኩላሊት ለጋሹ ያለምንም ጫና በራሱ ተነሳሽነትና ሙሉ ፈቃድ መሆን አለበት፡፡ በማንኛውም ዓይነት ጥቅም፤ መደለያም ሆነ ጫና ተደርጎበት ላለመሆኑ በተለያየ የምርመራ ሂደት እንዲረጋገጥ የህክምና ሥነ-ምገባርም ሆነ ህጉ ያስገድዳል፤
 • የኩላሊት ለጋሹ ሁለንተናዊ ጤንነት በምርመራ ሂደት መረጋገጥ አለበት፡፡ በወቅቱ ያለው ጤና ብቻም ሳይሆን ለወደፊቱም አጠቃላይ ጤናው በተለይም የኩላሊት ጤናው ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች ያለበት ሰው (ለምሳሌ ደም ግፊት፤ ስኳር …) ያለበት ሰው እንዲለግስ አይፈቀድለትም፤ ምክንያቱም የታመመን ሰው ለማዳን ጤነኛን ሰው ማሳመም የህክምናው ስነ-ምግባር አይፈቅድምና፤
 • የኩላሊት ለጋሹና የኩላሊት ተለጋሹ የደም ዓይነት አንድ ዓይት ወይም ተስማሚ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪ የተለገሰው ኩላሊት በተቀባዩ የበሽታ ተከላካይ ሥርዓት እንደጎጂ ነገር ተቆጥሮ እንደማይከሽፍ (Immune Rejection)  በምርመራ ሂደት መረጋገጥ አለበት፡፡ ለጋሹና ተቀባዩ የቅርብ ዝምድና ያላቸው መሆናቸው ለዚህ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው፤
 • ከኩላሊት ለጋሹ ወደ ተለጋሹ ሊተላለፉ የሚችሉ ከባድ በሽታዎች (ለምሳሌ ኢንፌክሽኖች ወይም ካንሰር) አለመኖሩ መረጋገጥ፤ ካለም በቅድሚያ ታክሞ መዳን አለበት፤ እና
 • የኩላሊት ተለጋሹ የኩላሊት ንቅለ-ተከላውን ተቃቁሞ እናም በቀጣይ የሚሰጡ መድሃኒቶችን ባግባቡ እየወሰደ ጤናማ ሆኖ ለመኖር የሚያስችል የጤና ሁኔታ ላይ መሆኑ በምርመራ መረጋገጥ አለበት፡፡

በቅድመ-ምርመራው እነዚህ ሁሉ ቅድመ-ሁኔታዎች ከተሟሉ ንቅለ-ተከላው ይደረጋል፡፡ ይህም ታካሚው ዲያሊሲሰ ከመጀመሩ በፊት አሊያም ከተጀመረ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ ቀድሞ ከተጀመረናከተሳካ ከዲያሊሲስ በፊት መሆኑ ተመራጭ ነው፡፡ የኩላሊት እጥበትም ሆነ ንቅለ-ተከላ ህይወት አድን የህክምና አማራጮች ቢሆኑም ተስማሚ ለጋሽ ከተገኘና ከተሳካ የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ከዲያሊሲሰ የተሸለ አማራጭ ነው፡፡

አስ፡ ችግሩን ለመቅረፍና ህክምናውን ለማስፋፋት ምን እየተሰራ ነው፤ እንደ ባለሙያ ችግሩ ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ለጃ፡ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደሀገር ብዙ ጥረቶች እተደረጉ ነው፡፡ በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች በአጠቃላይ፤ ለኩላሊት መድከም በተለይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ህክምናውን የማስፋት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይቷል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስታል አሁን እየሰጠ ያለውን የተቀናጀ የኩላሊት ህክምና አገልገሎት ነው፡፡ በሆስፒታላችን እየተሰጠ ካለው የዲያሊሲስና የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ህክምናዎች በተጨማሪ በሌሎች ሆሰፒታሎችና ከተሞችም አዳዲስ የዲሊሲስ ማዕከላት እንዲገነቡ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እገዛ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይሁንና ካለው የታካሚ ብዛትና ከችግሩ ስፋት አንጻር ካየነው ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ህክምናውን ማስፋፋቱና ተደራሽ ማድረጉ አሁንም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ለዚህም ከጤና ሚኒስቴር በተጨማሪ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም (ሙያተኞች፡ ባለሀብቶች፡ የሙያ ማህበራት…) ጉልህ አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

አስ፡ዶ/ር ውድ ጊዜዎትን መስዋዕት አድርገው ለሰጡን ሰፊ ሙያዊ ማብራሪ በጣም እናመሰግናለን፡፡ መጨመር የሚፈልጉት ሀሳብ ካለ እድሉን ልስጦት?

ዶ/ር ለጃ፡ ይህ ጠቃሚ መረጃ ለአንባቢን ይደርስ ዘንድ ይህን ቃለ-መጠይቅ ስላደረጋችሁ እኔም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ ‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!› እንዲሉ አበው ዋነኛው መፍትሔ ለኩላሊት በሽታ ሊዳርጉ የሚችሉ መንስዔዎችንና አጋላጭ ሁኔታዎቸን አስቀድሞ መከላከል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ለኩላሊታችን ጤና ዋጋ እንስጥ! ጤና ይስጥልኝ!፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.