በጌታሁን ለገሰ @Birmaduu2
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2015 ዓ.ም፡- አብርሃም አበበ የስምንት አመት ታዳጊ ልጅ ሲሆን ፒያሳ፣ ልዩ ስሙ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የክብደት መለኪያ ሚዛን አጠገብ ተቀምጧል።
አብረሃም ከወላይታ ወደ አዲስ አበባ ስራ ለመፈለግ በደላላዎች ከሚመጡት ህፃናት መካከል አንዱ ነው፡፡ ህፃናቱን ሲያዘዋውሯቸው ጉዞኣቸው የተሸለ ህይወት ፍለጋ እንደሆነ እንዲምኑ ይደረጋሉ፡፡ ግን አዲስ አበባ እንደገባ ልክ እንደሌሎቹ አብርሃም በመንገዶች ዳር የክብደት መለኪያ ሰርቶ ገንዘብ እንዲያስገኝ አዋቂ ሰው አለማምዶታል።
“አዲስ አበባ የመጣሁት ከአንድ ወር በፊት ነው። ጓደኞቼ ጥሩ ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ እንደማገኝ ነግረውኝ ነበር የመጣሁት” ሲል አብርሃም ወደ አዲስ አበባ የመጣበትን አጋጣሚ ይናገራል።
ሌላኛው በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማራው የ12 ዓመቱ ቴዲ ተስፋዬ፣ የትውልድ ስፍራው ያለው ህይወት ከባድ በመሆኑ ጥሏት ለመሄድ መወሰኑን ይገልፃል፡፡ “እዛ ስራ ማግኘት እጅጉን ከባድ ነው፣ ምንም የእርሻ ቦታ የለንም” ሲል ገልፆ ቤተሰቦቹ አቅመ ደካማ በመሆናቸው ወደ ትምህርት ቤት ሊልኩት እንዳልቻሉ ገልጧል፡፡
እንደ አአብርሃም እና ቴዲ ለአቅመ አካል ያልደረሱ ህፃናት በተለያዩ የከተማዋ ሰፈሮች በተለያየ የስራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ አዲስ ስታንዳርድ እነዚህን ህፃናት በፒያሳ፣ መገናኛ፣ ሲኤምሲ ሚካኤል፣ ቦሌ እና በሌሎች አካባቢዎች ተመልክታለች፡፡ አብዛኞቹ ህፃናት ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለይም ከወላይታ ዞን የመጡ ናቸው፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን፣ የግብርና ኮሌጅ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ይስሃቅ ጌቾ እና አስራት ወርቁ በ2011 ዓ/ም በወላይታ ዞን የህጻናት ህገ-ወጥ ዝውውር በተመለከተ ባደረጉት ጥናት መሰረት “በወላይታ ዞን የህገ-ወጥ የህጻናት ዝውውወር ከሌላው አከባቢ የከፋ ያለ ነው፤ አዘዋዋሪዎቹ ህጻናትን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በተለይም ወደ ከተማ ለማጓጓዝ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ፡፡”
የይስሃቅና እስራት ጥናት እንደሚያመላክተው ከሆነ በጥናቱ ከተካተቱት ህጻናት መካከል ክፍተኛ መጠን ያላቸው ህጻናት ማለትም (57.8 በመቶ) የሚሆኑ ህጻናት በቤተሰቦቻቸው ውስጥ የኢኮኖሚ ችግር በመኖሩ ችግሩ እንዲስፋፋ የደረገው ዋነኛ ምክኒያት መሆኑን ነው፡፡ “ድህነት ህጻናቱ ከገጠተር ማህበረሰብ ተልይቶ ወደ ከተማው ጎዳና እንዲወደወቁ እድርጋቸዋል፤ ይህም በቀላሉ ርህራሄ በሌላቸው ህገ-ወጥ የህጻናት እዘዋዋሪ እጅ እንዲገቡ እድርጓቸዋል።”
አዲስ ስታንዳርድ በጥሩ ክፍያ ስራ ለመጀመር በማሰብ ቤተሰቦቻቸውን ትተው ወደ አዲስ አበባ የመጡ በርካታ ህፃናትን አነጋግራለች፡፡ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም የተለያዩ ስራዎች ይሰጣቸውና ለሌላ ሰው በትንሽ ክፍያ መስራት ይጀምራሉ፡፡ ርህራሄ በሌላቸው የህጻናት እዘዋዋሪ እጅ ይገባሉ።”
አብርሃም ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፀው በመንገድ ላይ ሰዎችን የመመዘን ስራን የሚሰራው ለባለሚዛኑ ነው፡፡ የሚዛኑ ባለቤት ስራው በቀን ከሚያስገኘው 30 ብር ገቢ ትንሽ ክፍያ ይከፍለዋል፡፡ “ከሬስሮራንቶች የተራረፈ ምግብ ተቀብለን ምሳችንን እንበላለን፣ አንዳንዴ ደግሞ ምግብ ስለማናገኝ ሳንበላ እንተኛለን” ሲል ገልጧል፡፡
አክሎም እሱ እና ጓደኞቹ በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር በአንድ ክፍል ውስጥ ታጭቀው እንደሚያድሩ ይናገራል፡፡ አብርሃም እና ጓደኞቹ በአዲስ አበባ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ነው። ትምህርታቸውን መከታታል ባለባቸው ዕድሜ በንግድ ስራ ላይ በመሰማራታቸውና ገና ህፃናት በመሆናቸው ለብዝበዛ እና ለጥቃት ተጋልጠዋል።
በፒያሳ በሱቅ ስራ ላይ የተሰማተራችው እመቤት ግርማ አብርሃም እና ሌሎች ህፃናት በሱቋ ስፍራ ስለሚውሉ በየቀኑ ይገናኛሉ፡፡ ህፃናት በዚህ ደረጃ ጥቃት ሲደርስባቸው ማየት ያሳዝናል፡፡ ከጉልበት ብዝበዛ ባሻገር ህፃናቱ ለወሲባዊ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው፡፡ በእነዚህ ልጆች ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል መንገር በጣም ከባድ ነው” ስትል እመቤት ትናገራለች።
“ብዙውን ጊዜ በሆቴሎች ፊት ቆመው የተረፈ ምግብ ለመቀበል በጅምላ ሲጠባበቁ አያቸዋለሁ የት እንደሚያድሩ ግን እርግጠኛ እይደለሁም፤ አንዳንድ ህጻናት ግን መንገድ ላይ ተኝተው አያለሁ” ስትል እመቤት አክላ ገልፃለች።
አብዛኞቹ ልጆች ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ከወላጆቻቸው አባላት ጋር ያላቸው ግኑኝነት የተቋረጠ ሲሆን ከቤተሰባቸው አባላት ጋርም አያወሩም፡፡
የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኛ በመዲናዋ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ ሚካኤል አካባቢ የክብደት ሚዛን ይዞ የተቀመጠውን ቢኒያም የተባለ የስምንት አመት ህፃን ያነጋገረ ሲሆን ነገር ግን የልጁን እንቅስቃሴ ከሩቅ የሚከታተል ሰው ስለነበር በመፍራት ጋዜጠኛው ለሚጠይቀው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አልቻለም
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የወላይታ ዞን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ከልታ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት የዞኑ አስተዳደር የህጻናትን ስደት አስመልክቶ ባደረገው ምርመራ ህፃናቱ በአዲስ አበባ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚችሉ ቃል በሚገቡላቸው ደላላዎች ነው የሚታለሉት።
“የተያዙና ፍርድ ቤት የቀረቡ ደላላዎች ያሉ ሲሆን ህጋዊ እርምጃም እየተወሰደባቸው ነው። በተጨማሪም ከዞኑ ውጭ የህጻናትን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መመሪያዎችን ጥብቅ አድርገናል” ሲሉ አቶ ፀጋዬ ጨምረው ገልፀዋል።
እንደ አቶ ፀጋዬ ገለጻ፣ አብዛኞቹ ህጻናት የሚፈልሱት በአዘዋዋሪዎች ስልታዊ በሆነ ምንገድ ተታለው ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ ከችግር ለማምለጥ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሰደደ ይገደዳሉ፡፡ አንዳንድ ህጻናት ከወላጆቻቸው ፍቃድ ውጭ በጓደኞቻቸው እና በቤተሰባቸው አባላት በድብቅ ይዘዋወራሉ። “ህጻናቶቹም ሆኑ ወላጆች የስደትን ጥቅምና ጉዳት ጠንቅቀው አያውቁም” ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ የዞኑ አስተዳደር ለትርፍ ካልተቋቋሙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ህብረተሰቡን ስለ ስደት የማስተማር ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
ሆኖም “ሁሉም ወደ የአዲስ አበባ የፈለሱ ልጆች የወላይታ ተወላጆች እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ስህተት ነው፡፡ ስደት በአገሪቱ ውስጥ ሁሉም ቦታ አለ የወላይታ የተለየ አይደለም” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው የሶዶ ከተማ የሚገኘው የሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ቅስቀሳ ሲሰራ የቆየ ሲሆን በከተማዋ በሚገኙ 11 ቀበሌዎች የህፃናት መብት ኮሚቴዎችንም አቋቁሟል። ነገር ግን ከተለዩት ችግሮች አንዱ “የህብረተሰቡ አባላት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አይደሉም” መባሉ ሲሆን ይህም የችግሩን ቀጣይነት እና በዙሪያው ያለውን ውስብስብ ሁኔታ ያመለክታል፡፡
ባሳለፍነው አመት ግንቦት ወር ላይ የስልጤ ዞን ፖሊስ፣ ከሶዶ ከተማ ወደ አዲስ አበባ 19 ህጻናትን ሲያዘዋውሩ የተያዙ ዘጠኝ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ተጠርጣሪዎቭን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል የቻለው በወራቤ ከተማ ነዋሪዎች ጥቆማ መሰረት መሆኑ ተገልጧል፡፡ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠሩት ሰዎች ሁሉም ሴቶች ሲሆኑ በሳኖ ቀበሌ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ውለዋል።
አዲስ ስታንዳርድ በጉዳይ ላይ መረጃ ላማግኘት የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ህጻናት ቢሮ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስን ለማነጋገር በተደጋጋሚ የሞከረች ቢሆንም መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡አስ