ዜና፡ በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ሰራተኞች በአስቸካይ እንዲፈቱ አመነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በአዲስ አበባ ዙሪያ እየተካሄደ የነበረው ቤት የማፍረስ እንቅስቃሴን ለማጣራት በመሄዳቸው ለእስር የተዳረጉትን አራት የሰብአዊ መብት መርማሪዎች “በአስቸኳይ” እና “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” በመፍታት እና በእነርሱ ላይ የተመሰረተው ክስ እንዲነሳ ማድረግ አለባቸው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

የኢሰመጉ ሰራተኛ የሆኑት ዳንኤል ተስፋዬ፣ብዙአየሁ ወንድሙ፣ በረከት ዳንኤል እና ናሆም ሁሴን ታህሳስ 27 ቀን አለም ባንክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እየተካሄደ ባለው ቤት የማፍረስ እንቅስቃሴን ለማጣራት በሄዱበት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣወ መግለጫ ገልጧል፡፡ ፖሊስ ስራቸውን ለማካሄድ አስፈላጊው ፍቃድ የላቸውም ሲል ከሷል ብሏል፡፡

የኢሰመጉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ታህሳስ 28 በሰራተኞቹ እስር ጉዳይ ላይ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ በበላይ አካላት እናንተ የመመርመር መብት የላችሁም ተብለናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አክለውም ይህ ህጋዊ መብታችንን መጋፋት ነው ብለዋል፡፡

“እነዚህ አራት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አንድም ወንጀል አልፈጸሙም። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን በግድ ማፈናቀል ተግባር ላይ መረጃ የማሰባሰብ ስራ ብቻ እያከናወኑ ነበር። መጀመሪያውኑ በፍፁም መታሰር አልነበረባቸውም ፤ በአስቸኳይ እና ያለ ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። ማንም ሰው ወሳኝ የሆነ የሰብአዊ መብት ስራ በመስራቱ  ወንጀለኛ መባል የለበትም ”ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ታይግሪ ቻጉታህ ተናግረዋል።

“አራቱም ሰራተኞች ታህሳስ 27 ቀን የተከሰሱት ከፖሊስ ፈቃድ ውጪ የሰብአዊ መብት ክትትል አድርገዋል በሚል ሲሆን ይህም  በኢትዮጵያ ህግ ወንጀል አይደለም። የድርጅቱንም ተሽከርካሪ ያሰረው ፖሊስ  ከድርጅታቸው የድጋፍ ደብዳቤ ሳይዙ በግዳጅ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ተጎጂዎችን እያነጋገሩ ነበር ሲል ገልጿል። በአሁኑ ወቅትም በገላን ጉዳ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዋል” ሲል አምነስቲ ገልጧል።

“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ማስፈራራት በአስቸኳይ በማቆም እና በአስተማማኝ እና ምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነው  እንዲሰሩ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል ታይግሪ ቻጉታህ።

ኢሰመጉ በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ በሚሰራው የሰብዓው መብት ስራዎች  ምክንያት በሰራተኞቹ እና በአባላቶቹ ላይ በጫና ሀገር ለቆ እንዲሄዱ ማድረግ እንዲሁም ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንደ ግድያ፣ እስራትና ማሰቃየት ሲደርስባቸው ቆይቷል ሲል ጠቅሶ በእስር ላይ የሚገኙት ባለሙያዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ  ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በመንግስት የሚፈጸሙ ስልታዊ የሆኑ በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ ተገቢውን ኃላፊነታቸውን በመወጣት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳይችሉ መጠነ ሰፊ ጫናዎች እየተደረጉባቸው ይገኛሉ ብሏል የኢሰመጎ መግለጫ፡፡

ለእዚህም ማሳያነት በኢሰመጉ ጋምቤላ ቅርንጫፍ አባላት እና ሰራተኞች ላይ የደረሱ ዛቻዎች እና ማስፈራራቶች፣ በ24/03/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ በሚገኘው የኢሰመጉ ማዕከላዊ ቀጠና ጽ/ቤት አቤቱታ ለማቅረብ የመጡ 22 ሰዎችን አቤቱታ አቅርበው ሲወጡ መታሰራቸው በመንግስት በኩል በኢሰመጉ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጫናዎችን የሚያሳዩ ድርጊቶች ናቸው ሲል አክሎ ገልጧል፡፡

ኢሰመጉ በሰራተኞች ላይ የተፈጸመው እስር በየትኘውም መስፈርት ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ ድርጊት በመሆኑ ሰራተኞቹ ከእስር እንዲለቀቁ እና ይህንን ሕጋዊ ያልሆነ እስራት እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡ አካላትና ትዕዛዙን የፈጸሙ አባላት ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና ውጤቱንም ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.