ምንድነው የሆነው?
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን (ኢመብባ) የፈቃድ እና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ሐምሌ 08 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ ስታንዳርድ አሳታሚ የሆነውን ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃ.የተ.የግ.ማ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአዲስ ስታንዳርድ አባላትን አዲስ ስታንዳርድ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተቀበለውን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ዋና ቅጂውን ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጽህፈት ቤት ይዘው እንዲመጡ ጠየቀ ፡፡
በዚህ መሠረት ጥያቄው አስተዳደራዊ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ሶስት ግለሰቦች ማለትም የፋይናንስና አስተዳደር እና ማርኬቲንግ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም አንድ የፋይናንስና አስተዳደር ረዳት የተጠቀሰውን የምስክር ወረቀት ይዘው ወደ ቢሮው ሄደዋል ፡፡
የዳይሬክቶሬቱ ኃላፊም በኢመብባ ይዘት ክትትል ቡድን በኩል የተለያዩ ቅሬታዎች እንደደረሳቸው ተናግረው ባለስልጣኑ የአዲስ ስታንዳርድን የምዝገባ የምስክር ወረቀቱን እንደወሰደ እና አዲስ ስታንዳርድ የህትመት ስራውን ማቆም እንዳለበት ተናግረዋል ፡፡
በዛኑ ቀን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አዲስ ስታንዳርድ በኢትዮጵያ ፓርላማ “ሽብርተኛ” ተብሎ የተፈረጀውን ህወሓት “የትግራይ መከላከያ ሰራዊት” የሚለውን ቃል በመጠቀም የህወሓትን አጀንዳ የሚያራምድ መሆኑን ገልጿል ።
ከዳይሬክቶሬቱ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃ.የተ.የግ. ማ የአዲስ ስታንዳርድ ይዘት ህትመት በጊዜያዊነት መታገዱን የሚገልጽ ማስታወቂያ አውጥቷል ፡፡
ውሳኔው የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ሕግ የጣሰበት ሁኔታ
አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2013 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለብሮድካስት አገልግሎት ማለትም ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ የፈቃድ አሰጣጥ ሁኔታዎችን የሚወስን ሲሆን ለበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን የእውቅና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠት ብቻ ይሰጣል ፡፡
* በአዋጁ አንቀፅ 26 ላይ እንደተገለጸው የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ማመልከቻ ከቀረቡ በኋላ ባለስልጣኑ ለአመልካች ህጋዊ እውቅና ካልሰጠ አመልካቹ ህጋዊ እውቅና እንዳገኘ ይቆጠራል ፡፡
* በአዋጁ አንቀፅ 22 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ምዝገባ ስርአት ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የይዘት ገደብ ሊያደርግ እንደማይገባ ይደነግጋል ፡፡
* በአዋጁ አንቀፅ 48 ላይ መገናኛ ብዙሃን ሀሳባቸውን የመግለፅ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትችት የማቅረብ መብትን ያረጋግጣል ፡፡
* አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በተመለከተ በአዋጁ አንቀፅ 73 ላይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንደ አስፈላጊነቱ እርምጃዎችን የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ መውሰድ ይችላል ። የአዋጁን ድንጋጌዎች የተላለፉ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚከተሉትን አስተዳደራዊ እርምጃዎች በየደረጃ ይወሰዳል ።
ሀ) የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት
ለ) እስከ 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ ብር) የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት
ሐ) ጥሰት የተፈጠረበትን ህጉን ፕሮግራም ማገድ ወይም መሰረዝ
መ) ጥሰት የፈጸመውን የብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃድን ፈቃድ ማገድ ወይም መሰረዝ
ከላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ ለብሮድካስት አገልግሎት ሰጭዎች እንጂ ለበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ሚዲያ የሚተገበር አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ፡፡
የእውቅና የምስክር ወረቀትን የማገድ ወይም መሠረዝ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመወሠን ስልጣን ውጪ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ድርጊቶች የይዘት ህትመትን ወደ ማገድ እንደማይወሰዱ ልብ ይሏል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ቦርድ ወሳኝ ሚና
* በተሻሻለው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሾም ዘጠኝ አባላት ያሉት ቦርድ የሚኖረው ሲሆን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሥራ አመራር ሆኖ ያገለግላል ፡፡
*በአዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ቦርዱ የአዋጁን አፈጻጸምና የባለስልጣኑን ሥራዎች በበላይነት ይቆጣጠራል ።
* በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ 5 ቦርዱ ከህዝብ የቀረቡ ቅሬታዎችን በሚመለከት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን መርምሮ እንደሚወስን ይገልጻል ።
* በአዋጁ አንቀፅ 12 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ቦርዱ በብሮድካስት አገልግሎት ባለፍቃዶች የሚቀርብለትን የክትትል ውጤት በመመርመር ለቦርድ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ገለልተኛ የሆነ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በማደራጀት በውሳኔ ሀሳቡ መነሻ በማድረግ ውሳኔ ይሰጣል ።
ሆኖም ምንም እንኳን አዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2021 ቦርድ መቋቋም እንዳለበት የሚደነግግ ቢሆንም ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በአዋጁ ላይ የተደነገገውን ስልጣን ያለው ቦርድ አልተዋቀረም ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረኩት ክትትል እና በደረሱኝ ቅሬታዎች ላይ በመመርኮዝ ነው የአዲስ ስታንዳርድን ህትመት በጊዜያዊነት ያገድኩት በማለት የውሳኔውን ምክንያት ይፋ ያደረገው እነዚህ የሕግና አካሄድ ጉድለቶች በነበሩበት ሁኔታ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በሰጠው አስተያየት አዲስ ስታንዳርድ የሽብር ቡድንን አጀንዳ ያራምዳል እና የሽብር ቡድኑን “የትግራይ መከላከያ ሰራዊት” ብሎ ይጠራል በማለት የወነጀለ ሲሆን በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የእግድ ውሳኔውን ካስተላለፈ በኋላ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ይህንን ስያሜ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ማሳሰቡ ይታወቃል ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአዲስ ስታንዳርድን ህትመት በድንገት ማገድ እና በምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እና ድርጅቶች ባደረጉት ቃለመጠይቆች ላይ የሰጡት አስተያየት የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን የሚያስተጓጉል አሠራር፣ አስተዳደራዊ ተግባር እና እና እርምጃ የሚከለክለውን የሚዲያ አዋጁን አንቀጽ 72 ይጻረራል ።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአዲስ ስታንዳርድ ይዘት ህትመት እንዲታገድ ከማዘዙ በፊት አስጠንቅቄያለሁ ቢልም ፣ በአዋጁ መሠረት በቦርዱ የሚወሰኑት ጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ፣ ቅጣት ፣ ፈቃድ መታገድ ወይም መሠረዝ እና መሠል አስተዳደራዊ እርምጃዎች አዲስ ስታንዳርድ የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን በመሆኑ ተፈፃሚ አይደሉም ።
በኢመብባ ዋና ዳይሬክተር ፣ በምክትል ዋና ዳይሬክተር እና በአዲስ ስታንዳርድ የዜና ክፍል አርታኢዎች መካከል የተደረገ ስብሰባ
ሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓም፣ የአዲስ ስታንዳርድ የዜና ክፍል ሁለት ሲኒየር የዜና ክፍል አባላት ማለትም ዋና አዘጋጅና ኤዲተር ከኢመብባ ዋና ዳይሬክተር ከአቶ መሃመድ ኢድሪስ እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጋር ስኬታማ እና ገንቢ ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ በስብሰባው ላይ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ መስማማት ላይ ተደርሷል
የአዲስ ስታንዳርድ አባላት፡-
* የአዲስ ስታንዳርድ አባላት ከላይ የተጠቀሱትን በውሳኔው ላይ የተከሰቱ ግድፈቶች ለኢመብባ አመራሮች አስረድተዋል ፡፡
* የአዲስ ስታንዳርድ አባላት ቀደም ሲል የኢመብባ ከፍተኛ አመራር አባል በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የሰነዘሩዋቸው ከበድ ያሉ ውንጀላዎች እና መግለጫዎች ሚና ላይ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል ፡፡
* የአዲስ ስታንዳርድ አባላት ገለልተኛ ቁጥጥር ያለውን አስፈላጊነትና ለዚህም አዲስ ስታንዳርድ ህትመቱ ያልተገደበ ትብብር እንደሚያደርግ በመግፅ ይህን የመሰለ ቅሬታ ሲያጋጥምም ሆነ ኢመብባ ባለፉት ጥቂት ቀናት “ህትመቱ በፓርላማ በአሸባሪነት የተሰየመውን ድርጅት አጀንዳ ለማራመድ ይሠራል” በማለት ያወጣው ተደጋጋሚ መግለጫ የተሳሳተ መሆኑን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡
* የአዲስ ስታንዳርድ እንደዚህ ያሉትን ክሶችን በቀላሉ የማይመለከት መሆኑን በመግለጽ እነዚህ የመጡት ክሶች የተሳሳቱ መሆኑን ለማረጋገጥ መወሰኑን አስታውቋል ።
ለዚህም የአዲስ ስታንዳርድ አባላት እንደዚህ ያሉ ክሶች ሙሉ በሙሉ መሠረተ ቢስ መሆናቸውን ለማሳየት የኢመብባ ተቆጣጣሪ ቡድን የተመረጡ ህትመቶችን በተመለከተ ገለልተኛ ክትትል ለማድረግ ሲጠየቅ ስለህትመቱ ገለፃ በመስጠት ለመተባበር በጣም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የኢመብባ አመራር
* የአዲስ ስታንዳርድ የበይነመረብ ይዘት ህትመት እንዲታገድ የተወሰደው እርምጃ የህግ ስርዓቱን የጣሰ መሆኑን አምኗል ፡፡ አመራሩ ለድርጊቱ እንደ ምክንያት ያቀረበው የመገናኛ ብዙሃን ህትመቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት እና ሉዓላዊነትን አይተኩም የሚል ነው ፡፡ ወደ ድንገተኛ ውሳኔ የወሰደው ልዩ ይዘት እየተመረመረ መሆኑንና ውጤቱም በተገቢው ጊዜ እንደሚገለፅ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራር ገለጿል ።
* የኢመብባ አመራር “የትግራይ መከላከያ ሰራዊት” የሚለውን አጠራር ጨምሮ የቃላትን አጠቃቀም ማረም አስፈላጊነት ለአዲስ ስታንዳርድ አሳውቋል ፡፡
* የኢመብባ አመራር መገናኛ ብዙሃን እንደነዚህ ያሉትን ቃላት ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ያስጠነቀቀው የጽሑፍ ማሳወቂያ በአዲስ ስታንዳርድ ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ መሆኑን ተገንዘቧል ፡፡
* የኢመብባ አመራር ወደፊት ለሚኖሩ ቅሬታዎች አዲስ ስታንዳርድን ለማሳወቅ ተገቢውን አካሄድ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ህግ መሰረት እንደሚከተል ገልጿል ፡፡
* የኢመብባ አመራር ለአዲስ ስታንዳርድ ረቡዕ ሐምሌ 21 ቀን 2021 ዓ.ም የእውቅና ምስክር ወረቀት ዋናውን ቅጂ እንደሚመለስለት አረጋግጧል ፡፡
* የኢመብባ አመራር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመግለጫ አዲስ ስታንዳርድ በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለው እና አጀንዳውን ያራምዳል በሚል የቀረቡትን ክሶች ላይ እርምት እንደሚወስድ ገልጿል ፡፡
ማጠቃለያ አስተያየት
ስብሰባው የተካሄደው የጉዳዩን አሳሳቢነት ኢመብባ እና አዲስ ስታንዳርድ በመከባበር ላይ በመሰረቱት የጋራ መግባባት ነው፡፡ አዲስ ስታንዳርድ የሚታወቅበትን የጋዜጠኝነት ሥነምግባር አስጠብቆ ለመቀጠል እና ዴሞክራሲና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመሩ ጥረቶችን ለማገዝ እንደ ገለልተኛ ሚዲያ ያለውን ወሳኝ ሚና ለመጫወት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል ፡፡