አዲስ አበባ መጋቢት 12/2014-የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ስህተት መፈጠሩን ገልፆ አጣሪ ቡድን ወደ ፈተናወች ኤጀንሲ መላኩን አስታወቀ፡፡ የክልሉ ትምህር ቢሮ ከሶስት ቀን በፊት በ2013ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ጊዜው እንዲራዘም ጠይቋል፡፡
የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን በሰሜን ወሎ ዞን ከሚገኙ 42 ትምህርት ቤቶች በስድስት ትምህርት ቤቶች ለትምህርት መልቀቂያ ፈተና ከተቀመጡት 679 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት መውደቃቸውን የገለፀ ሲሆን ይህም የውጤት አወሳሰዱን ከመደበኛ ስርዓት ውጭ መሆኑን ዘግቧል።እነዚህ ድርጊቶች የተስተዋሉባቸው ትምህርት ቤቶች ጊራና ካሊም ፣ቁል መሰቅ ፣ጉርጉር ደብረሮሃ ፣ሃናሙቃት ደብረሲና እና ከበበው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በተጨማሪም የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ፈተና እና አስተዳደር ባለሙያ ሙሉ አዳነ እንደገለፁት ዞኑ በጦርነት ውስጥ ከገባ ከ5 ወራት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን አሁንም በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ለፈተና ለመቀመጥ ሙሉ ዝግጁነት እንዳነበራቸው ተናግረዋል። ተማሪዎች በጦርነቱ ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጉዳት ሳያገግሙ ፈተና መውሰዳቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል። ዞኑ ለፈተና ከተቀመጡት 9ሺህ 710 ተማሪዎች መካከል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያስመዘገቡት 3ሺህ 567 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ተናግሯል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በርካታ ተግባራትን ሲፈጽም መቆየቱን ገልፆ በአሁን ሰዓትም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ አመራሮቸና ባለሙያዎች፣ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንና መምህራን የተውጣጣ ቡድን ወደ ፈተናወች ኤጀንሲ መላኩን አስታውቋል፡፡
የክልሉ ትምህር ቢሮ ከሶስት ቀን በፊት በ2013ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ጊዜው እንዲራዘም የጠየቀ ሲሆን የ2013ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤት ከተገለፀበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ በጣም ሰፊ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎቻችን ውጤታቸው እንደገና እንዲፈተሸላቸው እያመለከቱ ከመሆኑም በተጨማሪ በትምህርት አመራሩና በትምህርት ማህበረሰቡ ዘንድም በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ መሆኑን ገልጿል።
ቢሮው የተማሪዎች ውጤት በአግባቡ ተፈትሾላቸው ተገቢው መተማመን እስኪፈጠር ድረስ የተማሪዎች መግቢያ ቀን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ቢሮው በደብዳቤ ትምህርት ሚኒስትርን ጠይቋል፡፡
የፈተና አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ በበኩላቸው ኤጀንሲው ከ20 ሺህ የሚበልጡ ቅሬታዎችን ለግምገማና ለማረም ተቀብሏል ብለዋል። ተፈራ ከፈተና እርማት እና ቅሬታዎች ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ የፈተናው እርማት ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ በጥንቃቄ የተከናወነ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ፈተና እርማት ላይ የቴክኒክ ችግር ማጋጠሙን እና እርማት መደረጉን ገልፀዋል፡፡ በዚህም መሰረት የእርማት ችግሩ የተፈጠረው በ 559 ባልበለጡ ተማሪዎች ላይ እንደሆነ እና ዳግም ምልከታ ተደርጎ ማስተካከያ እንደተደረገም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ከ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ውጤት እና ከዩኒቨርሲቲ መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብረሪያ ሰጥቷል፡፡ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የ12ኛ ክፍል ፈተና በሁለት ዙር እንዲሰጥ መደረጉንና በመጀመሪያው ዙር የስነ-ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ከፈተናው ቀን ቀድሞ በመውጣቱና የውጤት ግሽበት በመምጣቱ እንዲሰረዝ መደረጉን ተናግረዋል።
ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ43 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ 152,144 ተማሪዎች እንዲማሩ የተደረገ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት በ47 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 147,000 ተማሪዎችን ከማስተማር ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ መሆኑን አመልክተዋል። ነገር ግን ሚኒስቴሩ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የፈተና ውጤትን ለመለየት የግዴታ ምዘና ባለማድረጉ ኤጀንሲው ወጥ የውጤት አሰጣጥ ስርዓትን እንዲያስተናግድ መደረጉን አምኗል።