የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የህውሀት ከፍተኛ አመራሮችን መፈታት ተቃወሙ

በጌታሁን ፀጋዬ እና ማህሌት ፋሲል

አዲስ አበባ ጥር 02 2014፣ መንግስት ታህሳስ 29 2014 ማታ የቀድሞ የህውሀት አመራሮችን ከእስር ለቋል። ከተለቀቁት ውስጥ አቶ ስብሀት ነጋ፣ ቅዱሳን  ነጋ ፣ሙሉ ገብረ እግዚአብሄር ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ እንዲሁም አባይ ወልዱ የሚገኙ ሲሆን የነሱን መፈታት የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውመውታል። 

እናት ፓርቲ በፌስቡክ ገልፁ ባወጣው መግለጫ  መንግስት ታሕሳሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም የወሰነው ውሳኔ የፓርቲውን አምባገነንነት የሚያሳይ፣ ለስልጣኑ ማስጠበቂያ እንጂ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ደህንነት ስሜት የማይሰጠው የመሆኑ ማሳያ ነው ብሏል። በመቀጠልም ከብዙ ታሳሪዎች መካከል “በእድሜ የገፉ ስለሆነ” በሚል ማታለያ እና ውሀ በማይቋጥር ምክንያት ሀገር ለሕልውና እያደረገች ያለውን ጦርነት ዓላማ የሳተ፣ የሕግ አሠራር ሂደትን የጣሰ፣ በግለሰቦችና ገዢው ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ዜጎች የሚታሠሩበትና የሚፈቱበት መሆኑን ማሳያ ነው። ስለሆነም ለፓለቲካ ትርፍ እና ለስልጣን ማስጠበቂያ ሲባል የሕግ አሠራርን ወደጎን በመተው በስሜትና በማንአለብኝነት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ሀገራችንን አሁን ካለችበት ሁኔታ ወደከፋ አዘቅት ይዟት እንዳይጓዝ ፓርቲያችን ሥጋቱን አበክሮ ይገልጻል ብለዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ የፌዴራል መንግሥቱ በታህሣሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በሀገር ላይ ይቅር የማይባል ክህደት የፈፀሙና ህዝብ ቀስቅሰው ፣ ጦር አደራጅተው በመምራት ለዚህ ሁሉ ሀገራዊ ውድመት የዳረጉንን ፣ በሀገሪቱ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው ድርጅት ቁንጮ አመራሮችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ማብራሪያ ከእስር በመፍታት የሀገርና የህዝብን ጥቅምና ክብር በፅኑ የሚጎዳ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል ብሏል በመግለጫው፡፡ ለሀገር ህልውናና ለህዝባችን ሰላምና ደህንነት በመላው ኢትዮጵያውያን የተከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጣ ፤ በይቅርታና በሰብአዊነት ስም የተፈፀመ ኢሰብአዊና ኢፍትሃዊ ውሳኔ ነው ሲል ተቃውመውታል። 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) “በአጥፊነት ተጠርጥረው እና በጦር ግንባር ተይዘው በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎችን ክስ ማቋረጥ እና ምህረት ብሎ በዳይን መካስ እጅግ የሚያስቆጭ እና የሚያንገበግብ እውነት ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ መቆጠብ ብቻ ሳይሆን በይፋም ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል” ያለ ሲሆን  “በሀገራዊ ምክከሩ ላይ ተሳታፊዎችን እና አጀንዳዎችን የሚወስነው ተብሎ ሥልጣን የተሰጠው ሊቋቋም ያለው ኮሚሽን ሆኖ ሳለ መንግሥት በቅርቡ ከእስር የፈታዋቸውን ሰዎች የፈታዋቸው በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ነው በማለት ከወዲሁ ተሳታፊዎቹን እየመለመለ ይገኛል” ሲል ገዢውን ፓርቲ ተችቷል። 

እንደ ፍትህ ሚኒስቴር ገለፃ መንግስት የተወሰኑ እስረኞችን ክስ በማቋረጥ ከእስር መፍታቱ ለአገራዊ ምክክሩ አካታችነት ጉልህ ፋይዳ አለው ብሏል። መንግስት የተወሰኑ እስረኞችን ክስ በማቋረጥ ከእስር መፍታቱ የአገራዊ ምክክሩን አካታችነት፣ ሰብአዊነትና ርህራሄን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ መሆኑን የገለፁት  የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በመሆኑም በትናንትናው እለት መንግስት ይፋ ያደረገው እስረኞችን የመፍታት እርምጃ ምህረትም ሆነ ይቅርታ ሳይሆን በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ላይ ያለን ጉዳይ ክስ የማቋረጥ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ መከላከያ ሚኒስቴር አዲሱ ህንፃን በሚመረቅበት  ወቅት እንዳሉት “ትናንት ክስ የተቋረጠላቸው ‘የተሸነፉ ሃይሎች’ ክሳቸው ተቋርጦ ከአስር ቤት አንዲውጡ ሲደረግ ከፍተኛ ቁጣ ከስቅሷል” ያሉ ሲሆን “በውስጥም በውጭም ያሉ ያንዳንዶችን ከኛን ይቅር ማለት አምርረው የጠሉና የደነገጡ ወንድምና እህቶቻችን እንዲገነዘቡልን የምንፈልገው ይህንን ጉዳይ እኛም መጀመሪያ ስንሰማው ያስደነገጠ መሆኑ ነው። ነገር ግን ደጋግመን ሲናመነዥከው፣ ግራ ቀኙን ስንትፈሽ ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለዘላቂ ጥቅም የሚያገዝ፣ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ጠላቶች የሚቀንስና በአውድ ውጊያ ያገኘነውን ድል በሰላሙ መድረክ እንድንደግም የሚያደርግ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ በመሆኑ እየመረረን የዋጥነው እውነት ነውና እናተም ለሃገራችሁ ዘላቂ ድል ሲትሉ ይህን ውሳኔ እንድትቀበሉት እጠይቃለሁ” በማለት አስረድተዋል ። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.