ዜና፡ ቤተክርስቲያኗ እና የሀገሪቱ ህዝቦች በፈተና ውስጥ እንደሚገኙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2/2015 ዓ.ም፡- በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያናችን እንደ ቤተክርስቲያን፣ ህዝባችንም እንደ ህዝብ በፈተና ውስጥ እያለፍን ያለንበት ግዜ ነው ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስታወቁ። ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ዛሬ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ባሰሙት የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር እንዳስታወቁት በቤተክርስቲያኗ ያጋጠሟትን ችግሮች በጥበብ ካልሆነ በቀር በመሳሳብና እልክ በመጋባት የሚፈቱ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያኗ በአሁኑ ወቅት ካጋጠሟት ፈተናዎች መካከል አበይት የሆኑት በትግራይ እና በኦሮምያበኩል የገጠማት መሆኑን ፓትርያርኩ በመክፈቻ ንግግራቸው አመላክተዋል። በተለይም በትግራይና በኦሮምያ አካባቢዎች ያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎች ከቤተክህነት አልፈው የሕዝብም ጭምር እየሆኑ ስለመጡ የሕዝቡን ጥያቄ በትክክል በማዳመጥ ሃይማኖቱንና ቀኖናውን በጠበቀ መልኩ በጥበብና በፍቅር ጥያቄአቸውን አክብረን መቀበል ያሻል፤ ጉዳታቸውንም መካፈል ይገባናል ብለዋል፡፡

እኛ ያጐደልነው፣የተሳሳትነውና ያስቀየምነው ካለም ይቅርታ ለመጠየቅም ሆነ ንስሐ ለመግባት ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል ሲሉ ያሳሰቡት አቡነ ማትያስ ታረቁ፣ ይቅር በሉ፣ንስሐ ግቡ ብለን የምናስተምር እኛ ይቅርታ ለመጠየቅና ንስሐ ለመግባት ሊከብደን አይገባም ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሀገሪቱ አሁንም ችግር ላይ እንደምትገኝ ሲገልጹም በሀገራችን ያለው የሰላም ሁኔታ በአንድ ወገን የተረጋጋ ሲመስል በሌላ በኩል ደግሞ የመንገጫገጭ ሁኔታ እየተከሠተ እንደሆነ እያየን ነው ሲሉ ገልጸው ይህም ሂዶ ሂዶ ቤተክርስቲያንን እና ሕዝብን እንዲሁም ሀገርን እና ልማትን መጕዳቱ የማይቀር ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያኗ በገለልተኛ አቋምና በሁሉም አቃፊነት ስልት ለሰላም ጠንክረን መስራት እንደሚኖርባትም አሳስበዋል።

በተፈጠረው አላስፈላጊ ከባድ ጦርነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የፈራረሱ አብያተ ክርስቲያናትና የተፈናቀሉ ምእመናን ልጆቻችንን በፍጥነት ደርሰን የምናጽናናበትንና የምንደግፍበትን ሁኔታ በዚህ ጉባኤ ማየት ይኖርብናል ሲሉ የለጉባኤው አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ያሉ በእርስ በርስ ግጭት እየተሳተፉ ያሉ ወገኖች ግጭቱን ኣቁመው በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን ለመፍታት እንዲጥሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.