አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7/2015 ዓ.ም – አዲስ አበባ የከተማ አስተዳደሩ ባለሦስት እና አራት እግር (ባጃጅ) አነስተኛ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተሽከርካሪዎች ላይ ያስቀመጠውን ሙሉ እገዳ በማንሳት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊያመቻች ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠይቋል። በሁሉም የከተማዋ ክፍሎች ላልተወሰነ ጊዜ ገደብ መጣሉ ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገላቸው መብቶች አደጋ ላይ የጣለ እርምጃ ነው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
ኢሰመኮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎትን ከየካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማዋ በየትኛውም አካባቢ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይሰጥ እገዳ መጣሉና ያወሳው መግለጫው እገዳውም አለመነሳቱ በተለያዩ ሰብአዊ መብቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ገደብ የሚጥል እርምጃ ነው ሲል ኮንኗል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል እገዳው በከተማዋ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ በመሆኑ የባጃጅ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎቹንና ቤተሰባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በርካታ ተጠቃሚዎችንም ችግር ላይ እንደጣለ መረዳቱን ያመላከተው የኮሚሽኑ መግለጫ መንግሥት ሰዎች ሥራቸውን እና የመረጡትን መተዳደሪያ ያለአግባብ እንዳያጡ ማድረግን ጨምሮ የመረጡትን እና የተቀበሉትን ሥራ እንዲሠሩ የማስቻል ኃላፊነት አለበት ሲል አሳስቧል።
ኮሚሽኑ እገዳውን ተከትሎ የደረሱትን አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችን ማነጋገሩን በመግለጫው አስታውቆ ኃላፊዎቹ በከተማዋ ወደ 10 ሺህ የሚገመቱ “የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ፈቃድ ያልተሰጣቸው መሆኑን፣ እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ በከተማዋ አሠራር ሥርዓት ያልተዘረጋላቸው መሆኑን፣ እንዲሁም ሌሎችም ተዛማጅ ችግሮች” መኖራቸውን እንደገለጹለት አመላክቷል።
በተጨማሪም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ከዋና መንገዶች ውጪ ባሉ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ማስተካከያ እየተወሰደ መቆየቱን፤ ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ባጃጆቹ ከተቀመጠላቸው የእንቅስቃሴ አካባቢ ውጪ በዋና መንገዶች ላይ ሲሠሩ በመታየታቸው እና የከተማው የትራንስፖርት ፍሰት ላይ ጫና መፍጠሩን እንደነገሩት በመግለጫው አካቷል።
እገዳው በሁሉም ቦታ የተደረገው “ልዩነት እና መድሎ ላለመፍጠር” እንደሆነና የባጃጅ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የሚሠሩ በመሆኑ አሠራሩን ስለማሻሻል ከማኅበራቱ ጋር የተደረጉ ውይይቶች እንደነበሩ አስታውቋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከሰብአዊ መብቶች መርሆች አንጻር በባጃጅ የትራንስፖርት ሥራ የተፈጠሩትን ችግሮች በተገቢው ሕጋዊ እርምጃዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በማስተዳደር እና ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዲገቡ ማድረግ ሲገባ፣ በጠቅላላ ከተማው ላልተወሰነ ጊዜ ገደብ መጣሉ ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገላቸው መብቶችን አደጋ ላይ የጣለ እርምጃ ነው ሲሉ መኮነናቸውን መግለጫው አካቷል።
በተለይም በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንን እንዲሁም ሴቶች እና ሕፃናትን ታሳቢ በማድረግ እገዳውን ማንሳትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውቋ። አስ