ዜና: የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል

በሲዳማ ብሔር ዘንድ ትልቁን ቦታ የሚሰጠው ፊቼ ጫምባላላ በዓል በደማቅ ሁኔታ በመከበር ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ: የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ የፊቼ ጫምባላላ በዓል ዛሬ በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል። በሲዳማ ብሔር ዘንድ ትልቁን ቦታ የሚሰጠው ፊቼ ጫምባላላ በዓል በደማቅ ሁኔታ ከሁለት ዓመት በኃላ ዛሬ በጠዋት በርካታ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ክፍል በተገኙበት በታላቁ ጉዱማሌ እየተከበረ ይገኛል።

የዘንድሮው በዓል ሲዳማ ክልል በህዳር 2011 የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ተከትሎ ክልሉ ራሱን የቻለ ክልላዊ መንግስት ከሆነ በኋላ የመጀመርያው ነው። በተጨማሪ ም በኮቪድ 19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ የሚከበር የመጀመሪያው ህዝባዊ በዓል ነው።

በበዓሉ ላይ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የተለያዩ ሚንስትሮች፣ ሚንስትር ዴኤታዎች፣ የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ክልል የምክር ቤት አፌ ጉባኤዎች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኦሮሞ አባገዳዎችና ሀራ ስንቄዎች፣ ከተለያዩ ብሔረሰብ የመጡ እንግዶች፣ ከሁሉም ሲዳማ አካባቢ የተወጣጡ ማህበረሰብ በሶሬሳ ጉዱማሌ ተገኝተዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ትናንት እንደተናገሩት ፊቼ ጫምባላላ ለሲዳማ ልዪ በዓል እንዲሁም የአለም ቅርስ የሆነውን በዓል ማበልፀግ እንጂ መሸርሸር እንደማይገባ ገልጾ በፊቼ ጫምባላላ በዓል ያኮረፈ አኩርፎ ስለማያልፍ ሁሉንም ነገር በመተው ቅሬታን በመተው አንድነታችን እንጠንክር ብለዋል።

ምንጭ: የሲዳማ ብ/ክ/መ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እና አዲስ ስታንዳርድ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.