በምህረት ገ/ክርስቶስ @Mercy
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30/ 2015 ዓ/ም፦ ዛሬ ጠዋት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግብያ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲዉን ሁለት ካምፓሶች የሚያገናኝ ድልድይ በመደርመሱ ምክንያት የተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ለህዝብ እንዳስታወቁት አዲስ መረጃ እስከአሁን በጉዳቱ የአንድ ተማሪ ህይወት ሲያልፍ፣ ሁለት ከባድ ጉዳት እና ሌሎች መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸዉ ይገኛል፡፡
አደጋው የደረሰው ከዋናው ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለመሄድ ድልድዩን ሲሻገሩ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ነው::
ሁለቱን ግቢዎች የሚያገናኘው ድልድይ ላይ ድልድዩ መሸከም ከሚችለው አቅም በላይ ተማሪዎች ሲወጡበት በመውደቁ አደጋው ማጋጠሙን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጹ ያወጣው መረጃ ያመላክታል።
“በዚህ አደጋ ምክንያት ጥቂት ተማሪዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል” ያለው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል።
“ሁኔታቸዉን መላዉ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ እና የትምህርት ሚኒስቴር ግብረሀይል በቅርበት እየተከታተለ” ነው ያለው ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ “ወላጆች እንዳይደናገጡ እንጠይቃለን” በማለት በጋጠመው አደጋ ማዘኑንም ገልጸዋል።
ጉዳት የደረሰባቸዉ ተማሪዎች በቀጣይ በሚሰጠዉ ፈተና የሚፈተኑ መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ ሌሎች ተማሪዎች በአጋጣሚዉ ሳይረበሹ ተረጋግተዉ እንዲፈተኑ አሳስቧል።
የዛሬውን ፈተና መፈተን ያልቻሉ ተማሪዎች ሌላ ዕድል ከት/ት ሚኒስቴርና የፈተናዎች ድርጅት ጋር በመነጋገር እንደሚመቻችላቸውም አሳውቋል።አስ