አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6/ 2015 ዓ.ም – አዲስ አበባ ከተማን የሁከት ማእከል ለማድረግ በተለያየ ግዜ የተደረጉ የተለያዩ ሙከራዎች መክሸፋቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አበቤ አስታወቁ፡፡
ከንቲባዋ በመካሄድ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤው ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት ባለፉት ስድስት ወራት የከተማ አስተዳደሩ ካስመዘገባቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ ከተማይቱ የሁከት አውድማ ከመሆን ለመታደግ የተሰራ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
በህዝብ የተመረጠን መንግስት በመጣል ስልጣንን በሀይል ለመቆጣጠር በሚል መነሻ ከቅርብ ግዜ ወዲህ አዲስ አበባን እና ነዋሪዎቿን ለማወክ ላይ ያነጣጠሩ ተግዳሮቶች ገጥመውናል ያሉት ከንቲባዋ በተለይም ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት የጽንፈኝነት፣ የጥላቻ፣ እና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚደረግ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል።
በከንቲባዋ ‘’ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት’’ በሚል ቢያልፉትም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ማብራሪያ በቁጥር አስደግፈው በመቶኛ አቅርበዋል፤ በዚህም 64 በመቶ የሚሆኑት ከአማራ ክልል አካባቢ ነው የመጡት፤ 21 በመቶ የሚሆኑት ከደቡብ አካባቢ ነው፤ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከኦሮሚያ ነው ብለዋል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ በአድዋ በዓል አከባበር ላይ ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ዙሪያ የከተማዋ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የኦፕሬሽናል ኮሚቴ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ በዕለቱ በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉት 8 መቶ 78 ተጠርጣሪዎች መካከል 5 መቶ 75 የሚሆኑት ከሌሎች ክልሎች የመጡ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
በአብሮነት የኖረውን ህዝብ እርስ በርስ እንዲጠራጠር፣ እንዲለያይ ብሎም ግጭት ውስጥ እንዲገባ ብዙ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መስተዋሉንም ከንቲባ አዳነች አበቤ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ህዝብን ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን እናምናለን ያሉት ከንቲባዋ ከእነዚህ መልካም ስራዎች ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እዳይሆን ለማድረግ እና ሰላምን ለማወክ ከሚነዙ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዎች ራሱን ለመጠበቅ አቅም ያለው ማህበረሰብ እንደሆነም እናምናለን ብለዋል።
ሰላማችንን ለማደፍረስ ህዝቡን በማደናገር እና በማወናበድ በተለይም ወጣቱን በውሸት ፕሮፓጋንዳ በማነሳሳት ሁከት ለመፍጠር ሙከራ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ ከፕሮፓጋንዳው በተጨማሪም ወጣቱን በጥቃቅን መደለያዎችም ወደ ጥፋት ለመማገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩንም ተናግረዋል።
ከንቲባ አዳነች አያይዘውም የከተማዋ ነዋሪ እራሱን በመነጠል ከመንግስት ጋር እንዲያብር ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት ወራት መነሻቸውን ከአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎቸ ያደረጉ ተጓዦች በኦሮምያ ክልል የጸጥታ ሀይሎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከላቸውን የተመለከተ ዘገባ የክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ አሚኮ ማሰራጨቱ ይታወሳል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከንቲባዋ ያቀረቡት ሪፖርት ተቃውሞ መንግስት ከንቲባዋን ከስልጣን እንዲያነሳ እና ለፍርድ እንዲያቀርብ አሳስቧል።
ከሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ መግባት ከአማራ ክልል ነዋሪዎች አስቸጋሪ ሁኗል በሚል ከክልል ምክር ቤት አባላት ለቀረበ ጥያቄ የክልሉ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ሲመልሱ ዜጎች በሀገራቸው በነጻ መንቀሳቀስ አለባቸው ይህም በህገመንግስቱ ተደንግጓል፤ ይህን ማስከበር አለብን ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ሱዳን በነጻ እየገባን አንዳንድ ሀገሮች ላይ ያለቪዛ በቀጥታ እየገባን በሀገራቸው እዚህ ቁሙ ሊንባል አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል። አስ