በማህሌት ፋሲል @MahletFasil
ግንቦት 23፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦ ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥራቸው ከግማሽ ደርዘን እንደሚበልጥ እስካሁን ከምናውቀው ለመረዳት ችለናል። ተከታዩ የዜና ትንታኔ የጋዜጠኞቹ ስም እና የት እንደሚሠሩ ፣ የመታሰራቸውን ዳራ እና የፍርድ ቤት ሂደት ፣ እንዲሁም የታሰሩበትን ሁኔታዎችን ይመለከታል ።
ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ – “ገበያኑ”
አርብ ግንቦት 13 እረፋድ ላይ በፖሊስ የተያዘው የቀድሞው “ሻይ ቡና” አዘጋጅ እና አቅራቢ ፣ በአሁኑ ጊዜ የራሱን “ገበያኑ” የተሰኘው የመገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነው ሰለሞን ሹምዬ ፣ ግንቦት 13 ቅዳሜ ጠዋት የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ቀን ጠይቆበታል።
መርማሪ ፖሊስ ሰለሞንን “ሁከትና ብጥብጥ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ለማስነሳት በመሞከር” ጠርጥሬዋለው ሲል ምርመራዬን ለማጠናከር 14 የምርምራ ቀን ይሰጠኝ ሲልም ጥይቋል።
የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው የቀረበበት መዝገብ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ትውውቅ እንደሌላቸው እና የደንበኛቸው መዝገብ ተለይቶ ለብቻው እንዲታይ ችሎቱን የጠየቁ ሲሆን ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀን ውድቅ ተደርጎ ደንበኛቸው ዋስትና እንዲፈቀድለትና ከውጭ ሆኖ እንዲከታተል ችሎቱን ጠይቀዋል።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት ለፖሊስ 9 የምርመራ ቀን በመፍቀድ ለግንቦት 22 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ፖሊስ አራት ተከሳሾች ያሉበትን መዝገብ ነጥሎ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰቷል።
ሰሎሞን ግንቦት 22 ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቦ የመጀመርያው ፍርድ ቤት የሰለሞንን ጠበቆች የዋስትና ጥያቄ ከመስማቱ በፊት፡ መርማሪ ፖሊስ ባለፈው ችሎት ለዘጠኝ ቀናት ያደረጋቸውን ድርጊቶች አድምጧል። ፖሊስ ለፍርድ ቤት በእጁ ያለውን ኤሌክትሮኒክስ ወደ “መርማሪው አካል” ልኮ ውጤቱን እየጠበቀ መሆኑን ተናግሯል።
ከአስተያየቶቹ መካከል “መንግስት ህገ መንግስቱን ማስከበር ስላልቻለ እያንዳንዱ ግለሰብ ህጉን ማስከበር አለበት” የሚል ያካትታል በማለት ፖሊስ ለችሎቱ ተናግሯል።
መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪው በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ማግኘቱን ለማወቅ ለባንኮች ደብዳቤ መላኩንም አብራርተዋል። ፖሊስ ለቀረበበት ክስ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
“ገበያኑ” እየተባለ የሚጠራው የዩቲዩብ ሚዲያ በኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን ፍቃድ የተሰጠው መሆኑን ለማጣራት ደብዳቤ መፃፉንም መርማሪ ፖሊስ ተናግሯል። በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ሰሎሞን ከዚህ ቀደም በሰጠው አስተያየት እየመረመርኩት ነው ብሏል። ከአስተያየቶቹ መካከል “መንግስት ህገ መንግስቱን ማስከበር ስላልቻለ እያንዳንዱ ግለሰብ ህጉን ማስከበር አለበት” የሚል ያካትታል በማለት ፖሊስ ለችሎቱ ተናግሯል። ለእነዚህ መልሶች እና ተጨማሪ ምርመራ ለማካሄድ 14 ቀናት እንዲፈቀድለትም ችሎቱን ጠይቋል።
የሰሎሞን ጠበቆች የደንበኛቸው ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መታየት እንዳለበት ተከራክረዋል። በተጨማሪም “ገበያኑ” እየተባለ የሚጠራው የዩቲዩብ ሚዲያ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ ሚዲያ ነው ሲሉ ተከራክረዋል። ይህንን በመረዳት ፍርድ ቤቱ ደንበኛቸውን በዋስ እንዲለቀቅላቸውም ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ የጠበቆቹን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ሰባት ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን ለፖሊስ ፈቅዷል። ችሎቱ ለመጪው ግንቦት 29 ቀጠሮ ይዟል።
ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ – “ኢትዮ ፎረም”
‘ኢትዮ ፎረም’ የተሰኘው የዩትዩብ መገናኛ ብዙኀን አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን ሃሙስ ግንቦት 18፣ 2014 ዓ. ም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ያዋለው ሲሆን ግንቦት 19 ቀን ጋዜጠኛውን ፍርድ ቤት አቅርቦ 14 የምርመራ ቀን ጠይቆበታል። ፖሊስ ጋዜጠኛው “ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት” ጠርጥሬዋልሁ ሲል ለፍርድ ቤት ገልጿል።
ፖሊስ ተከሳሹ ”ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት” ጠርጥሬዋለሁ ያለ ሲሆን በቀጣይ ግብረ አበሮቹን ለመያዝ፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባስብ እንዲሁም ምርመራውን ለማጠናከር 14 ተጨማሪ የምርምራ ቀን ይሰጠኝ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ፖሊስ አክሎም ጋዜጠኛው ”ኢትዩ ፎረም” በተባለ እና ሌሎች ሚዲያን በመጠቀም ሁከትና ብጥብጥ ሲያስነሳ ነበር ያለ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ‘በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄደውን ጦርነት’ የሚመራው እሱ ነው ሲል ክስ አቅርቧል። ፖሊስ ጋዜጠኛ ያየሰው በስውር የተደራጀ ሀይል ውስጥ እንዳለበት እንደሚያምን እና በተደጋጋሚ መታሰሩ ለዚህ ማሳያ እንደሆነ ለችሎት ተናግሯል።
“በመንግስት ጫና እና ማስፈራሪያ ምክንያት ስራ ካቆምኩ 2 አመት ሆኖኛል”
ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ
የተከሳሽ ጠበቃ ታደለ ገብረ መድህን በበኩሉ ደንበኛቸው ላይ የቀረበው ምርመራ ግልፅነት የጎደለው መሆኑን፣ ፖሊስ የተከሳሽን ግብረ-አበሮች ለማያዝ ሲል ደንበኛቸውን ማሰር እንደሌለበት አንስተው ፍርድ ቤቱ ደንበኛቸውን በዋስትና እንዲለቀው ጠይቀዋል። ክርክሩን ጋዜጠኛ ያየሰው በአካል ተገኝቶ የተከታተለ ሲሆን፣ ”በመንግስት ጫና እና ማስፈራሪያ ምክንያት ስራ ካቆምኩ 2 አመት ሆኖኛል። የተያዝኩት በህገውጥ መንገድ ነው፣ በዚህ ሁለት አመት ያለ ፍርድ ስድስት ጊዜ ታስሪያለሁ”ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎት መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀናት በመከለስ 10 የምርመራ ቀናትን የፈቀደ ሲሆን ለግንቦት 29 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ – “ፍትህ” መጽሄት
ሀሙስ ግንቦት 18 ረፋዱ ላይ ሲቪል የለበሱ ጸጥታ ኃይሎች የተያዘው በየሳምንቱ በአማርኛ የምታተመው “ፍትህ” መጽሄት ባለቤት እና ማኔጅንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አርብ ግንቦት 19 ከሰአት በኋላ ቀርቦ ፖሊስ ”ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት፣ህዝቡ በመከላከያ ሰራዊት ላይ እንዲሁም በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ እና እንዲያምፅ በመንቀሰቀስ” ጠርጥሬዋለው ብሏል።
የተመስገን ደሳለኝ ጠበቆች ደንበኛቸው ጋዜጠኛ በመሆኑ መከሰስ ያለበት በመገናኛ ብዙሀን አዋጅ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው ደንበኛቸው በዋስ ወጥቶ ጉዳዩን እንዲከታተል ችሎቱን ጠይቀዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኛቸው ጋዜጠኛ በመሆኑ መከሰስ ያለበት በመገናኛ ብዙሀን አዋጅ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው ደንበኛቸው በዋስ ወጥቶ ጉዳዩን እንዲከታተል ችሎቱን ጠይቀዋል።
ችሎቱም የሁለቱን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ተጠርጣሪው ”በምን አዋጅ መታየት አለበት” የሚለውን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 22 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በእለቱም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ 10 ተጨማሪ የምርመራ ቀን በመፍቀድ ለግንቦት 29 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ – “ሮሃ ቲቪ”
ቅዳሜ ግንቦት 20 ጧት የሮሃ ቲቪ የዩትዩብ መገናኛ ብዙኀን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ የሆነችውን ጋዜጠኛ መዓዛ ሞሐመድን ከጓደኛዋ ቤት በፖሊስ ታስራለች።
መዓዛን “ለጥያቄ እንፈልግሻለን” በማለት አዲስ አበባ ከሚገኘው ከጓደኛዋ መኖሪያ ቤት ይዘዋት የሄዱት ሁለት የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች እንደሆኑ ባለቤቷ ሮቤል ተስፋዬ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
ሰኞ ግንቦት 22 ጠዋት ከጠበቆቿ ጋር ችሎት የቀረበችው መአዛ ፖሊስ ”ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ገንዘብ በመቀበል፣ የሀይማኖትና የብሄር ግጭት እንዲነሳ በማድረግ፣ህዝብ መንግስት ላይ እንዲነሳሳ በማድርግ” ጠርጥሬያታለሁ ያለ ሲሆን ግብረአበሮቿን ለመያዝ እና ከተጠርጣሪዋ እጅ የተያዙየኤሌክትሮኒክስ ቀሳቁሶች ለመመርመር 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።
መዓዛ ከሳምንታት በፊትም ሮሃ ሜዲያ ላይ እየሰራች ሳለች ታስራ ክስ ሳይመሰረትባት መፈታቷ ይታወሳል
የተጠርጣሪዋ ጠበቆች ደንበኛችን የተያዘችው በሚዲያ በግልፅ መንግስትን በመተቸቷል እንደሆነ፣ ደንበኛቸው ከቅዳሜ ጀምሮ በእስር ብትቆይም ፖሊስ የሰራው ምንም ስራ እንደሌለ እና የተጠርጣሪዋን ቃል እንኩዋን እንዳልተቀበለ አንስተው የተከራከሩ ሲሆን ፖሊስ ግብረአበሮቿን ለመያዝ ደንበኛቸውን በእስር ማቆየት ተገቢ አይደለም ብለዋል ።
ፍርድ ቤቱ የግራና ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ለውሳኔ የ 7 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ለግ ንቦት 29 ቀን፣ 2014 ዓ.ም አስተላልፏል።
መዓዛ ከሳምንታት በፊትም ሮሃ ሜዲያ ላይ እየሰራች ሳለች ታስራ ክስ ሳይመሰረትባት መፈታቷ ይታወሳል።
ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው – “አልፋ ቲቪ”
የአልፋ ቲቪ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ግንቦት 27 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ከሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ተጠርጥሮ ቅዳሜ ግንቦት 20፤ 2014 ፍርድ ቤት ቀረቦ ፖሊስ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ጠርጥሬዋለሁ ሲል ለየፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ክስ አቅርቦ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
በቃሉ በችሎቱ ላይ “ጉዳዩ መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ነው” ሲል የተከራከረ ሲሆን የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለትም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ አክሎም፤ በቃሉ “በተለያዩ በመንግስት ሚዲያ ቀርቦ ቃለ መጠይቅ በማድረግ መንግስት እንዲጠላ እና ሀይማኖታዊ ግጭት እንዲፈጠር ተንቀሳቅሷል” ብሏል።
ፍርድ ቤት ያለ ጠበቃ የቀረበው ጋዜጠኛ በቃሉ በበኩሉ “ስራ እንዳልሰራ ተደርጌያለሁ በመንግስት ሚዲያም ቀርቤ አላውቅም” ብሏል። በቃሉ በችሎቱ ላይ “ጉዳዩ መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ነው” ሲል የተከራከረ ሲሆን የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለትም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የጋዜጠኛውን ጉዳይ መርማሪ ፖሊስ “ጋዜጠኛው በዋስትና ከወጣ ይጠፋል። ግብረ አበሮቹንም ያባብላል” በሚል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀናት በሁለት ቀንሶ 12 ቀናትን ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገን ክርክር ካዳመጠ በኋል በመጪው ሰኔ 2፤ 2014 በሚኖረው ቀጣይ ቀጠሮ ፖሊስ በተሰጡት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት አንዲያቀርብ ትእዛዝ አስተላልፏል።
ጋዜጠኛ መስከረም አበራ – “ኢትዮ ንቃት”
“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዮቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው ቅዳሜ ግንቦት 12 ከቀኑ 6ሰአት ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመለሰችበት ወቅት በፀጥታ ሀይሎች የታሰረችው ጋዜጠኛ እና መምህርት መስከረም ሰኞ እረፋድ ላይ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አንደኛ የግዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርባ ከመርማሪ ፖሊስ ጋር ክርክር አድርጋ መርማሪ ፖሊስ 14 የምርመራ ቀን ይሰጠኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል።
መርማሪ ፖሊስ መስከረምን “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት እና የፌደራል መንግስት እና የአማራ ክልል ለመነጠል ገንዘብ ተከፍሏት እንደምትሰራ” ጠርጥሬያታለሁ ያለ ሲሆን፣ የምርመራ መዝገቡን ለማጠናከር እና የሰነድ ማስረጃን ለማሰባሰብ የተጠርጣሪዋን ግብረ አበሮች ለመያዝ፣ ከጋዜጠኛዋ የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን የምርመራ ውጤት ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ለመጠባበቅ ፣ እንዲሁም የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ በሚል ተጨማሪ 14 ቀን እንደሚያስፈልገው ችሎቱን ጥይቋል።
“ሁለቱም እናታቸውን ናፍቀዋል በተለይ ትንሹ ጡት የሚጠባ በመሆኑና ስሜቱን አውጥቶ መናገር ባለመቻሉ ከባድ ግዜ ነው እያሳለፍን ያለነው”
የመስከረም አበራ ባለቤት ፍፁም ገብረ ሚካኤል
የተጠርጣሪዋ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኛቸው ላይ የተጠየቀው 14 ቀን አግባብ እንዳልሆነ እና ስራዋን በግልፅ በሚዲያ ስራዋን የምትሰራ መሆኗን አንስተው የተከራከሩ ሲሆን ፖሊስ የጠየቀው የሚዲያ ህጉን የሚጣረስ በመሆኑ ደንበኛቸው መከሰስም መከሰስ ካለባት ቀጥታ በአቃቤ ህግ መሆን እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ጠበቆቹ አክለውም ደንበኛቸው የ7 ወር ህፃን ልጅ እንዳላትና ጡት የምታጠባ ስለሆነ ቋሚ አድራሻ ስላላት ከእስር ተለቃ በውጪ ሆና ትከራከር ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል ።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት የተጠርጣሪዋ ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ፖሊስ የ13ቀን የምርመራ ቀን በመፍቀድ ለግንቦት 29/2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
መስከረም አበራ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ስትሆን የመጀመሪያ ልጇ የሰባት አመት ሁለተኛው ደግሞ የሰባት ወር ናቸው። “ሁለቱም እናታቸውን ናፍቀዋል በተለይ ትንሹ ጡት የሚጠባ በመሆኑና ስሜቱን አውጥቶ መናገር ባለመቻሉ ከባድ ግዜ ነው እያሳለፍን ያለነው” ያለው የመስከረም አበራ ባለቤት ፍፁም ገብረ ሚካኤል፣ ”በአሁኑ ሰአት ልክ እንደእርሷ ባንሆንለትም [የሰባት ወሩ ህፃን] የመስከረም እናት እና እኔ እየተንከባከብነው ነው” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ – “ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” (ከእስር ተፈታለች)
ሐሙስ ግንቦት 18፤ 2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ከስራ ቦታዋ ስትወጣ በፀጥታ ሀይሎች የተያዘችው የ“ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ ፍርድ ቤት ሳትቀርብ ግንቦት 22 ቀን ከእስር ተፈታለች ።
የኦሮሚያ ፖሊስ “ስንፈልግሽ ተመጫልሽ” በሚል እንደፈታች የጣቢያው ዋና ዳይሬክተር ለሚ ታዬ ተናግረዋል
የ“ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ ከእስር መለቀቋን የጣቢያው ዋና ዳይሬክተር ለሚ ታዬ ጋዜጠኛ ሶቦንቱ የተለቀቀችው ቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል ። ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ የኦሮሚያ ፖሊስ “ስንፈልግሽ ተመጫልሽ” በሚል እንደፈታች እንደነገረቻቸው ለዚሁ የዜና አውታር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በበኩሉ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች “በተቀናጀ መንገድ የሕግ በላይነትን ማስከበር” በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት በወሰዱት እርምጃ ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል።
“የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በስራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ ይገባል”
ዶ/ር ዳንኤል በቀለ
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሊወስድ የሚችላቸውን እርምጃዎች ኢሰመኮ እንደሚገነዘብ ካሳወቀ በኋላ፣ “የዚህ አይነት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን” የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል።
“በተለይም የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በስራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ ይገባል፣ እንዲሁም በማናቸውም አይነት ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ወዲያውኑ እንዲያውቁ እንዲደረግና ወደ ፍርድ ቤትም ሊቀርቡ ይገባል” ብለዋል፡፡ አስ