በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
አዲስ አበባ፣መስከረም 23/2015 ዓ.ም፡– የፌዴራል ዐቃቤ ህግ የሃሰት ወሬን ነዝተዋል ፣ በውጊያ ውስጥ የወገን ጦር አሰላልፍና ቦታን ለጠላት እና ለህዝብ አሳውቀዋል በሚል እና በሌሎች ወንጀሎች ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ መዐዛ መሃመድ እና ከመስከረም ወር መጀመሪያ ቀናት ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ደራሲና አክቲቪስት አሳዬ ደርቤ ላይ መስከረም 20/2015 ዓ.ም. ክስ አንደተመሰረተባቸው ፍትህ ሚኒስቴር አስተወቀ፡፡
በዚህ መሰረትም አንደኛ ተከሳሽ በሆነው ጎበዜ ሲሳይ፤ Amhara Perspective ተብሎ የተከፈተ የቲዉትር አካዉንት ላይ በቀን 26/12/2014 ቀርቦ ባደረገዉ ንግግር “ጠቅላላ ህዝቡ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የማይደግፍ ይልቁንም ህወሃት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የሚፈልግ እና የሚደግፍ እና ወጣቱ ከመንግስት ጎን መሰለፍ የማይፈልግ” አድርጎ በማቅረብ ሰራዊቱ በአካባቢዉ ያለ ህዝብ አይደግፈኝም ብሎ እንዲያስብ በማነሳሳት በህዝብና እና በሰራዊት መካከል ያለዉን መልካም ግንኙነት የሚጎዳ እሳቤ እንዲኖር የሰራ፣ የመንግስት የመከላከል አቅም ላይ ህዝቡ ያለዉን አቋም የሚያፈርስ መረጃ እስተላፏል ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡
በተጨማሪም በራሱ ስም በከፈተዉ በፌስቡክ ገፅ ላይ በቀን 30/12/2014 ዓ.ም ‹‹አሁን በተከፈተው ጦርነት ውስጥም ሕወሓትን ፊት ለፊት እየተዋጉ የሚገኙት የፋኖ መሪዎችን ምሬ ወዳጆን እና ደምሌ አራጋውን ለመግደል በተደጋጋሚ ከኋላ እየተተኮሰባቸው ህይዎታቸው ተርፏል። በዚህ ሁኔታ እንዴት መንግስትን ተማምኜ ጦርነት እገባለሁ የሚል ወጣትም አለ።›› በማለት የሃሰት ወሬ በመናገረ እንዲሁም ነሃሴ 30/1014 ዓ.ም በፌስቡክ ገፁ “የሃገር መከላከያ ሰራዊቱ እና ጥምር ጦሩ የት አካባቢ እንዳለ እና የት አካባቢ ሳይዝ እንደቀረ” በፅሁፉ በመግለፅ በዉጊያ እንቅስቃሴ ዉስጥ የወገን ጦር አሰላለፍ እና ቦታ ከፍተኛ ቁምነገር ሆኖ መያዝ የሚገባዉን ለጠላት እና ለህዝቡ በማጋራት ወንጀል በአጠቃላይ ሶስት ተደራራቢ ክሶች እንደተመሰረተበት ተገልጿል፡፡
ሁለተኛ ተከሳሽ አሳዬ ደርቤ እና 3ኛ ተከሳሽ መዐዛ መሃመድ በተመለከተም 2ኛ ተከሳሽ አሳዬ ደርቤ የሃሰት ወሬዎችን 3ኛ ተከሳሽ መዐዛ መሃመድ በምታስተዳድረዉ በሮሃ ሚዲያ ለማህበረሰብ በማድረስ እና የሃሰት ወሬዎች እንዲሰራጩ በማድረግ ወንጀል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ በሮሃ ሚዲያ አማካኝነት ነሃሴ 19/2014 ዓ.ም ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የነበረዉን ጦርነት ማጠናቀቅ ይቻል ነበር፡፡ ችግሩ ምንድን ነዉ ለመሸነፍ ዝግጁ ያልሆነ ጠላት ስላጋጠመን ሳይሆን ፍላጎት የሌለዉ መንግስት ስለነበረን ነዉ፡፡ ህወሃት ሲዳከም እፎይታ ጊዜ እየሰጠ ወደ ደቡብ ጎንደር ሲያመራ አፈግፍግ የሚል ትዕዛዝ እየሰጠ በሀብት የሚጠናከርበትን፣የህዝብ ስነልቦና የሚንኮታኮትበትን መንገድ ሲጠርግ ነበር፣ ህዝቡ ተጠናክሮ ከደቡብ ጎንደር ሲያወጣዉ ደግሞ በዛዉ ግለት ከማስቀጠል አንፃር የእፎይታ ጊዜ እየሰጠ እንደገና ወደ ወሎ የሚሄዱበትን መንገድ ሲያመቻች ነበር፡፡ የወንበር ስጋት ሲሆኑ ቀጥቅጦ ያባርራቸዋል፤ ከወንበሩ የሆነ ኪሎሜትር እርቀት ላይ ሲሆኑ ትቷቸዉ ይመጣል ማለት ነዉ” ብሎ በመናገራቸው ክስ እንደተመሰረተባቸው የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡
በንግግራቸውም በወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አቅም እና ስልቶች ምክንያት የሚወሰኑ ዉሳኔዎችን ፍፁም ሃሰት በሆነ መንገድ በመቀየር መንግስት ሆነ ብሎ ህወሃት ሲዳከም ጥቃት የሚያቆም እና እንዲጠናከር እድል የሚሰጥ፣ ለማሸነፍ ፍፁም ፍላጎት የሌለዉ አድርጎ በማቅረብ የሃሰት ወሬዎችን ነዝተዋል በሏል፡፡
ይህ የዐቃቤ ሕግ ክስ በዛሬው እለት መስከረም 23 ቀን 2015 ዓ.ም ክሱ ለተከሳሽ እና የችሎት ታዳሚ ተነቦ ክርክሩ እነደሚደረግም ተገልጿል፡፡
“ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዛ መታሰሯን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወሳል።
የመአዛ እስር የጸጥታ ሃይሎች “የአማራ ድምጽ” የተባለውን ሌላኛውን የዩቲዩብ ሚዲያ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በድጋሚ ካሰሩት ከሰዓታት በኋላ ነው። መአዛ ለሶስተኛ ጊዜ በቁጥጥር ስር ስትውል የጎበዜ እስር ከብዙ ወራት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዋለው ችሎት ፖሊስ ሁለቱንም በሽብርተኝነት ወንጀል መጠርጠራቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ፖሊስ ሁለቱንም ጋዜጠኞች ከህወሓት ከፍተኛ አመራር ጋር በተለያየ መንገድ ግንኙነት እያደረጉ እና ተልዕኮ ተቀብለዋል ሲል ከሷል።
ጎበዜ ሲሳይ
የአማራ ድምጽ የብይነ መረብ ሚዲያ ባለቤትና ምስራች ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጳጉሜ 2፣ 2014 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ተይዞ በድጋሜ መታሰሩ ይታወቃል። በእለቱ ማለዳ 2 ሰዓት ላይ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱና ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሰዎች መያዙን ታናሽ ወንድሙ አቶ ከድር ሲሳይ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
የየኛ ቲቪ የበይነ መረብ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እሁድ ከሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት ወደማይታወቅ ቦታ በጸጥታ ሃይሎች ከተወሰደ በኋላ ግንቦት 1 ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ከእስር ተፈትቶ ነበር።
ጎበዜ ሲሳይ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የዒድ በዓል ዋዜማ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አያት አካባቢ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መወሰዱን ገልጿል። መጀመሪያ መታወቂያቸውን ለማሳየት ፈቃደኛ ያልነበሩና ማንነታቸውን ለመግለጽ ያልወደዱ 7 እና 8 የሚጠጉ ሲቪል ልብስ የለበሱ የጸጥታ ሃይሎች ወደ ቤቱ ገብተው ለምርመራ እንደሚፈለግ ነግረው እንደወሰዱት የተናገረው ጋዜጠኛው፣ “አይኔን ጨፍነው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወዳልታወቀ ቦታ ወሰዱኝ” ብሏል። ከታሰረበት ጊዜ ጀምሮ ፍርድ ቤት እንዳልቀረበም አስረድቷል።
ጋዜጠኛ ጎበዜ የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይል እና ፌዴራል ሃይል በጋር በመሆን ከትግራይ ሃይል ጋር የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ከቀጠለ በኋላ ወደ አማራ ክልል ተጉዞ ነበር። በፌስቡክ ገፁ ላይ ገዥውን የብልጽግና ፓርቲ ተችቷል። ጎበዜ በግል የፌስቡክ ገፁ ላይ “የአማራ ሕዝብ በተለይ ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰነው ህዝብ ጦርነት ሰልችቶኛል ፣ መንግስት በይደር በሚተወው ጦርነት በየአመቱ እያገረሸ ለሞትና ለስደት ዳርጎኛል ። ጦርነት አንፈልግም ዝመቱም አትበሉን የሚል አርሶ አደር አለ።” ሲል ፅፏል፡፡
ዩቲዩብ ላይ ባደረገው ቃለ ምልልስ የአማራ ህዝብ መጪውን የሰላም ቀን እንደሚመኝ በመግለፅ እንዲሁም በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ያሰፈረው ተመሳሳይ ይዘትን በማስተጋባት የሰነዘረው ትችት የመንግስት ደጋፊ በሆኑ አክቲቪስቶች ከፍተኛ ቅሬታ ቀስቅሷል። “አንተን መንግስት አይደለም የሚከስህ ህዝብ ነው:: የኢትዮጵያ ህዝብና መከላክያ ሰራዊት:: በህይውቴ እንደ አንተ አይነት ለቃሉ ይቅርታ <<ቆሻሻ>> ሰው አይቼም ሰምቼም አላውቅም:: እኔ በግሌ እንተን በኢትዮጵያ ስም እፋረድሃለሁኝ!!“ የሚል ትችት አክቲቪስቱ የትዊተር ገፅ ላይ ተለጥፏል፡፡
መአዛ መሃመድ
መአዛ መሃመድ ሂሳዊ አስተያየቷን የምታቀርብበት ሮሃ ሚዲያ የጎበዜን መታሰር ከዘገቡ ሚዲያዎች አንዱ ነው። መአዛ ራሷ ከመታሰሩ ከጥቂት ሰአታት በፊት በትዊተር ገጿ ላይ አዲስ መረጃ ለጥፋለች።
ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በሽሮ ሜዳ አካባቢ አብረው በግብይት ላይ ባሉበት ወቅት በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዛ መወሰዷን የስራ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ምስራቅ ተፈራ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግራ ነበር።
በዕለቱ የነበረውንም ሁኔታ ምስራቅ ለአዲስ ስታንዳርድ ያስረዳች ሲሆን ጋዜጠኛዋ በፖሊሶች ከመያዟ በፊት፤ አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው መታወቂያዋን እንድታሳየው ጠይቋት ነበር” ያለች ሲሆን አክላም መዓዛ “ለምንድን ነው መታወቂያ የማሳይህ?” የሚል ምላሽ እንደሰጠች ተናግራለች። ጥያቄውን ያቀረበው ግለሰብ መታወቂያ ማውጣት ሲጀምር፤ ሁለት የፌደራል ፖሊስ መለዮ የለበሱ የጸጥታ አካላት ወደ እነሱ መምጣታቸውን ምስራቅ ተናግራለች።
ጋዜጠኛ መዓዛ እየተገባደደ ባለው 2014 ዓ.ም. ለእስር ስትዳረግ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። መዓዛ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረችው በጥቅምት ወር ላይ ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ነበር። ፖሊስ መዓዛን “ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን በማስተላለፍ” እንደጠረጠራት በወቅቱ ቢገልጽም፤ ጋዜጠኛዋ አንድም ጊዜ ችሎት ፊት ሳትቀርብ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ተፈትታለች።
መዓዛ ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረችው ከሶስት ወራት በፊት ባለፈው ግንቦት ወር ውስጥ ነበር። መዓዛ በዚህኛውም እስር የተጠረጠረችው በተመሳሳይ “ሁከት እና ብጥብጥብ በማነሳሳት ወንጀል” ሲሆን ለ20 ቀናት ገደማ በእስር ላይ ቆይታ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቷ ይታወሳል።አስ