ዜና: ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከእስር ተፈታ

በማህሌት ፋሲል 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2 ፣ 2014 –  የየኛ ቴሌቪዥን የበይነ መረብ ጋዜጠኛ የሆነው ጎበዜ ሲሳይ እሁድ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት  ወደማይታወቅ ቦታ በጸጥታ ሃይሎች ከተወሰደ በኋላ ትናንት ማታ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ከእስር ተፈታ።

ጎበዜ ሲሳይ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም የዒድ በዓል ዋዜማ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አያት አካባቢ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መወሰዱን  ገልጿል። መጀመሪያ መታወቂያቸውን ለማሳየት ፈቃደኛ ያልነበሩና ማንነታቸውን ለመግለጽ ያልወደዱ 7 እና 8 የሚጠጉ ሲቪል ልብስ የለበሱ  የጸጥታ ሃይሎች  ወደ ቤቱ ገብተው ለምርመራ እንደሚፈለግ ነግረው እንደወሰዱት የተናገረው ጋዜጠኛው፣ “አይኔን ጨፍነው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወዳልታወቀ ቦታ ወሰዱኝ” ብሏል። ከታሰረበት ጊዜ ጀምሮ ፍርድ ቤት እንዳልቀረበም አስረድቷል።

አዲስ ስታንዳርድ ጎበዜን በእስር ላይ በነበረበት ወቅት  የጸጥታ ሃይሎቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምን እንደነበሩ ጠይቃለች። “አብዛኞቹ ጥያቄዎች መሠረተ ቢስ ውንጀላዎች ነበሩ” ሲል ጎበዜ የተናገረ ሲሆን የጸጥታ ሃይሎቹ “ጽንፈኛ አማራ” እንዲሁም “ኦሮሞ ጠል” ነህ እያሉ ይናገሩት እንደነበር አብራርቷል።

በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን በከሚሴ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች ጨምሮ ‘በተለያዩ ግጭቶች’ ተሳትፎ ነበረህ በሚል የተወነጀለ መሆኑን ገልጾ የጸጥታ ሃይሎቹ ግን ክሱን በተጨባጭ ማስረጃ ሊያቀርቡ እንዳልቻሉ አክሎ ተናግሯል። ጎበዜ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገረው ሌላው የጸጥታ ሃይሉ ‘የፋኖ ቡድን ደጋፊ ነህ’ የሚል ውንጀላም ሲያቀርቡበት እንደነበር ተናግሯል።

ጎበዜ አስረው የወሰዱት የአዲስ አበባ ፖሲስ ወይም የፌደራል ፖሊስ እንዳልሆኑ የተናገር ሲሆን፣ “አይኔን ስለሸፈኑኝ እና እነማን እንደሆኑ ስላልገለጹ፣ መታወቂያቸውን ስላላሳዩኝ በትክክል እነማን እንደሆኑ ማወቅ አልቻልኩም” ብሏል። አዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኛውን አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ገጥሞት እንደሆነ የጠየቀ ሲሆን ምንም አይነት አካላዊ ጥቃት ወይም ስቃይ እንዳልደረሰበት ተናግሯል። ነገር  ግን የስነ ልቦና ጉዳቱ ከፍተኛ እንደነበር ገልጿል። 

“ከተያዝኩበት ጊዜ ጀምሮ  በተደጋጋሚ የጸጥታ ሃይሎች ከታሰርኩበት ክፍል  ወደ ምርመራ ይዘውኝ ሲሄዱ አይኔን ይጨፍኑኝ ነበር። ከሳምንት በላይ ታስሬ ስቆይ  መርማሪዎቹ እነማን እንደሆኑ በትክክል ማወቅም ሆነ ማየት   አልቻልኩም” ሲል አስረድቷል። በተጨማሪም የጸጥታ ሃይሎቹ ዓይኑ እንደተሸፈነ ከታሰረበት አጓጉዘው ለምን እንደታሰረ እና ለምን እንደተለቀቀ በቂ መረጃ ሳይነግሩት ትናንትና ማታ  ከቤቱ ደጃፍ ላይ ጥለውት እንደሄዱ ገልጿል።

የሰብአዊ መብት እና የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾች ጎበዜ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ማማዕከል ባወጣው መግለጫ መንግስት ተገቢውን የህግ ሂደት እንዲከተል ጠይቋል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋዜጠኞች እና የሚዲያ አካላት ያለ አግባብ መታሰር እንዳሳሰበው ገልጿል። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድንም የጎበዜ መታሰር እንዳሳሰበው እና በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.