ዜና፡ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በጸጥታ ኃይሎች በድጋሚ ታሰረች

ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ

በጌታሁን ጸጋዬ @GetahunTsegay12

.አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜ 3፣ 2014 ዓ.ም“ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ትላንት ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 ዓም በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዛ መወሰዷን የስራ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ምስራቅ ተፈራ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገረች።

“ጋዜጠኛ መዓዛ በፖሊሶች የተያዘችው ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በሽሮ ሜዳ አካባቢ አብረን በግብይት ላይ ባለንበት ወቅት ነበር” ስትል ለዜና ክፍላችን አክላለች።

በዕለቱ የነበረውንም ሁኔታ ምስራቅ ለአዲስ ስታንዳርድ ያስረዳች ሲሆን ጋዜጠኛዋ በፖሊሶች ከመያዟ በፊት፤ አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው መታወቂያዋን እንድታሳየው ጠይቋት ነበር” ያለች ሲሆን አክላም መዓዛ “ለምንድን ነው መታወቂያ የማሳይህ?” የሚል ምላሽ እንደሰጠች ተናግራለች። ጥያቄውን ያቀረበው ግለሰብ መታወቂያ ማውጣት ሲጀምር፤ ሁለት የፌደራል ፖሊስ መለዮ የለበሱ የጸጥታ አካላት ወደ እነሱ መምጣታቸውን ምስራቅ ተናግራለች።

የጋዜጠኛዋ የስራ ባልደረባም አክላ “ሁለቱ ፖሊሶች መዓዛን በአቅራቢያቸው ወደ ቆመ ፒክ አፕ መኪና በመውሰድ እንድትሳፈር እንዳደረጓት” ስትል አብራርታለች።

አዲስ ስታንዳርድ መዓዛ ወዴት እንደወሰዷት ታውቅ እንደነበር ምስራቅን የጠየቀች ሲሆን “ወደ ፌደራል ፖሊስ ጣቢያ ነው የምንወስዳት” የሚል ምላሽ ከጸጥታ አካላቱ እንደመለሱላት ተናግራ በዕለቱም ወደተባለው ቦታ ብትሄድም “ሰዓት እላፊ ስለሆነ አሁን መጠየቅ አትችይም” እንደተባለች አስረድታለች።

አዲስ ስታንዳርድ ዛሬ ሃሙስ ጳጉሜ 3 ቀን 2014 ዓ.ም የሮሃ ሚዲያ የስራ ባልደረባ የሆነችው ምስራቅ ተፈራን ስለሁኔታው ያነጋገረች ሲሆን “አሁን የምገኘው ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ጣቢያ ነው። መዓዛን ለማነጋገር እየተጠባበቅን ነው” ስትል ምላሽ ሰጥታለች።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ስታንዳርድ የጋዜጠኛዋን በለቤት አቶ ሮቤል መንገሻን የነጋገረ ሲሆን ትላንት ረቡዕ ሽሮ ሜዳ አካባቢ መታሰሯን ገልፆ “አሁን ፌደራል ፖሊስ በር ላይ ባለቤቴን ለማነጋጋር በመጠባበቅ ላይ ነኝ” ሲል አጠር ያለ ምላሽ ለዜና ክፍላችን ሰጥቷል።

አዲስ ስታንዳርድ የጋዜጠኛዋን እስር አስመልክታ ስትዘግብ እንደነበር ይታወሳል። ጋዜጠኛ መዓዛ እየተገባደደ ባለው 2014 ዓ.ም. ለእስር ስትዳረግ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። መዓዛ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረችው በጥቅምት ወር ላይ ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ነበር። ፖሊስ መዓዛን “ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን በማስተላለፍ” እንደጠረጠራት በወቅቱ ቢገልጽም፤ ጋዜጠኛዋ አንድም ጊዜ ችሎት ፊት ሳትቀርብ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ተፈትታለች።

መዓዛ ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረችው ከሶስት ወራት በፊት ባለፈው ግንቦት ወር ውስጥ ነበር። መዓዛ በዚህኛውም እስር የተጠረጠረችው በተመሳሳይ “ሁከት እና ብጥብጥብ በማነሳሳት ወንጀል” ሲሆን ለ20 ቀናት ገደማ በእስር ላይ ቆይታ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቷ ይታወሳል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.