በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3/2015 ዓ.ም፡- በትንትናው እለት በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ሃይል በተቀላቀለበት መልኩ በፈጠሩት ሁከት የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉንና በፈተና አስፈጻሚዎችና በፀጥታ ሃይል ላይ ጉዳት መድረሱን ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ፡፡ ለፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች ከትምህርት ሥርዓት ባፈነገጠ መንገድ “ፈተናውን አንፈተንም” ያሉ 12,787 ተማሪዎች በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው መውጣታቸውን ሚንስቴሩ ገልጿል፡፡
ትምህርት ሚንስቴር የመጀመሪያ ዙር የመልቀቂያ ፈተና መጠናቀቁን ተከትሎ ትናንት ማምሻውን በሰጠው መግለጫ በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መካነ ሰላም ካምፓስ 1700፣ ከደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ 1,226፣ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 2,711 እንዲሁም ከደብረታቦር ዩኒቨርስቲ 7,150 በጠቅላላው 12,787 ተማሪዎች ፈተና ሙሉ በሙሉ ወይም ውስን ፈተናዎችን በመውሰድ ጥለው መውጣታቸውን አስታውቋል፡፡
ፈተናውን ጥለው የወጡት ተማሪዎች ፈተና መፈተን እንዳማይፈልጉ አሳውቀው ግቢ ለቀው የወጡ በመሆኑ በቀጣይ መፈተን የማይችሉ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አሰውቋል፡፡
በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የደረሰውን አደጋ በተመለከተ ከዋና ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ ግቢ ያለው የመተላለፊያ ድልድይ ወድቆ በ 451 ተማሪዎች ላይ የደረሰው አስደንጋጭ አደጋ 232 ቀላል ጉዳት፣ 201 መካከለኛ ጉዳት 13 ከፍተኛ ጉዳት፣ 5 በጣም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እና የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን ገልፆ ጉዳት ለደረሰባቸው ልጆች እና ወላጅ፣ ቤተሰቦች መጽናናት እንደዚሁም ማገገምን ተመኝቷል፡፡
በዚህ ድንገተኛ አደጋ ምክንያት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ መፈተን የሚጠበቅባቸው 14,415 ተፈታኞች የመጀመሪያው ቀን ሁለት ፈተናዎች እንደዚሁም የቴክኖሎጂ ግቢ 7,350 ተፈታኞች የመጀመሪያ ቀን የጠዋት ፈተና ባለመውሰዳቸው፤ ያልተፈተኗቸውን ትምህርቶች በ2ኛው ዙር እንደሚፈተኑ ገልጿል፡፡
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ማክሰኞ እለት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ተማሪዎቹ በጠዋቱ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ወቅት በተወሰኑ “የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን አናከብርም፤ “ካልተኮራረጅን አንፈተንም!” ባሉ ተማሪዎች የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ መስተጓጎሉን ጠቅሶ” ካልተኮራረጅን አንፈተንም!” በሚል እሳቤ ለመበጥበጥ የሞከሩ አካላትን ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል ሲል መግለፁ የታወቃል።
በተመሳሳይ መልኩ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከተመደቡ ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ብዙዎቹ በራሳቸው ፈቃድ ፈተናውን ጥለው መውጣታቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቋል። የደብረማርቆስ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ይትባረክ አወቀ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት “ከምሥራቅ ጎጃም አንዳንድ ወረዳዎች የመጡ ተማሪዎች «ለተፈታኝ ተማሪ የማይመጥን መፈክር በማሰማት በጠዋት የመፈተኛ ግቢያቸውን ጥለው ወጥተዋል።» ተማሪዎቹ ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲወስዱ የተለያዩ አካላት ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካም” ብለዋል።
የመልቀቂያ ፈተናው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደሚሰጥ ከተገለፀ ጀምሮ የቦታ ለውጡ ተፈታኞችን ሀሳብ ውስጥ እንደከተተ አዲስ ስታንዳርድ ተማሪዎችን አነጋግራ ዘግባ ነበር፡፡
ቅድስት (በመጀመሪያ ስሟ ብቻ መጠራት የፈለገች) የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በአዲስ አካባቢ ሄዳ መፈተኗ ለቤተሰቧ ስጋት እንደሆነ ገልፃ ይህ መልቀቂያ ፈተና በተማሪው ህይወት ላይ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ቢፈተኑ በራስ መተማመንናቸው እንደሚጨምር ተናግራለች፡፡
ለአዲስ ስታንዳርድ ሃሳቡን ያካፈለው ሌላው የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ አዲስ ሰመረ ውሳኔው የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት ታስቦ መሆኑ መልካም ሆኖ ሳለ ፈተናዉን ቤተሰብ ጋረ ሆኖ መፈተን የተሻለ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በተለይ ለሴቶች የፈተናውን ወቅት ከቤተሰብ ጋር ሆነው ቢፈተኑ ፈተናው ላይ ትኩረት አድርገው መፈተን የሚችሉት ሲል ገልጧል፡፡
አስማረ ተሰማ እህቱ የሁለተኛ ደረጃ ተፈታኝ ስትሆን በሃገሪቷ ወቅታዊ የፀጥታ ችግር የተነሳ እህቴን ወደ ሌላ ክልል ለመላክ ስጋት ውስጥ ገብቻለው ብለዋል፡፡ የአንዳንድ ክልል የፀጥታ ሁኔታ አስጊ በመሆኑ ተማሪዎቹ ከስጋት ነፃ ሆነው መፈተን ሊከብዳቸው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አክለዋል፡፡
ወላጆቹና ተማሪዎቹ ትምህርት ሚኒስቴር ተግባራዊ የሚደርገው አዲስ አሰራር አላማው የፈተና ስርቆትን ለማስቀረት መሆኑ ተገቢ መሆኑን ገልፀው ወደ ሌላ አከባቢ ማስማራቱ ግን ቢቀር የተሻለ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ማካፈላቸው ይታወሳል፡፡ አስ