በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9/2015 ዓ.ም፡- በሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች መካከል የተነሳው ግጭት ከተጀመረ ሁለት ወራትን ደፍኗል። ግጭቱ ሁለት ሚሊየን ሱዳናውያን እንዲፈናቀሉ ከማድረጉ በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሂወታቸውን አጥተዋል።
በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መከላከያ ሀይል እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል መካከል ካርቱምን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ውጊያ መካሄድ የጀመረው ልክ የዛሬ ሁለት ወር መሆኑ ይታወሳል።
ባለፉት ሁለት ወራት ሁለቱን ጀነራሎች ለማሸማገል በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ በተለይም በሪያድ በአሜሪካን መንግስት እና በሳዑዲ አረብያ መንግስት አማካኝነት ተሞክሮ የነበረው ተጠቃሽ ነው። የተወሰነ እፎይታ ለሱዳናውያን የሰጡ በከፊል እየተተገበሩ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተደርገዋል።
ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም በጂቡቲ በተካሄደው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ የሱዳንን ግጭት ለማሸማገል አራት ሀገራት ያሉት አሸማጋይ ቡድን ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በአሸማጋይነት የተመረጡ የኢጋድ አባል ሀገራት ሲሆኑ ቡድኑን የምትመራው ኬንያ መሆኗም ተጠቁሟል።
የኬንያው ፕሬዳንት ሩቶ ሁለቱን የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ፊት ለፊት አገናኝተው ለማሸማገል ቃል መግባታቸውን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ በዘገባው አስታውቆም ነበር። ሁለቱንም ጀነራሎች ከኢጋድ አባል ሀገራት መካከል በአንዱ ዋና ከተማ ተገናኝተው እንዲወያዩ ለማስቻል እንደሚሰራ የኬንያው ፕሬዝዳን ሩቶ ጽህፈት ቤት ይፋ ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁን ዘግበን ነበር።
ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መለስ አለም በኢጋድ አባል ሀገራተ መሪዎች የሚካሄደው የሱዳን ሀይሎችን የማደራደር ሂደትን አዲስ አበባ እንደምታስተናግድ አስታውቀዋል። ሁለቱን ሀይሎች የማደራደሩ ስራ በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።
የሱዳን መንግስት በኢጋድ የድርድር ሂደት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳት ላይ መሆኑን በርካታ ዘገባዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ። በኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሱዳን ሀይሎችን ለማደራደር በቀረበው ሀሳብ ላይ ምንም አይነት ገለጻ አልተደረገልንም ሲል የሱዳን መንግስት ቅሬታ ማንሳቱን የኬንያው ኔሽን ጋዜጣ በዘገባው አስታውቋል። የአደራዳሪነት ሚና ሲጫወቱ የነበሩት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ተነስተው የኬንያው ዊሊያም ሩቶ መተካታቸውንም እንደማይቀበለው የሱዳን መንግስት ማስታወቁን ዘገባዎቹ አመላክተዋል።
በጂቡቲ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ በርካታ አንቀጾች እንዲሰረዙ በሱዳን መንግስ ተወካዮች በኩል ጥያቄ ቢቀርብም ተቀባይነት አላገኙም ሲል የሱዳን መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩል ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዘገባዎቹ አካተዋል። በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ሀይል በበኩሉ የኢጋድ ጥረት በሳዑዲ አረብያ እና በአሜሪካ መንግስት የድርድር ማዕቀፍ በኩል እንዲካተት መጠየቁን ዘገባዎቹ አስታውቀዋል።
በኢጋድ በኩል የሚደረገውን የሽምግልና ጥረት የኬንያው ፕሬዝዳንት ሩቶ እንዲመሩት መደረጉን የሱዳን መንግስት ተቃውሟል መባሉን የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማስተባበላቸውን የኬንያ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። በጉዳዩ ዙሪያ ከሱዳን መንግስት በኩል የቀረበልን ምንም አይነት መደበኛ ግንኙነት የለም ማለቱንም አካተዋል።
ኢጋድ በበኩሉ በያዘው አቋም መጽናቱን እና ምንም አይነት የተቀየረ ነገር የለም ማለቱን መገናኛ ብዙሃኑ አስታውቀዋል። የኬንያው ኔሽን ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ አራቱ የኢጋድ አባላት ሀገራተ መሪዎች የተመረጡት በጉባኤው ነው ሊነሱም ሆነ ሊቀየሩ የሚችሉት በኢጋድ ጉባኤ ነው መባሉን ጠቁሟል።
የሱዳን የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ ካሚስ አብዱላህ አባካር መገደልን በርካታ የቀጠናው መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተውታል። አስተዳዳሪው የተገደሉት ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል የሚል አስተያየት ከሰጡ በኋላ መሆኑም ተገልጿል። የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥና ጀኔራል ቡርሃን፣ ለግድያው ባላንጣቸውን ጀኔራል ደጋሎ የሚመሩትን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ተጠያቂ ያደረገ ሲኾን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ ግን በግድያው እጁ እንደሌለበት ገልጾ ግድያውን አውግዟል። አስ