ዜና፡ በኢትዮጵያ ለተረጂዎች የቀረበ እርዳታ መዘረፉ ሀገራችን ያለችበትን የከፋ የሌብነት፣ ሙስና እና ኢ-ሰብዓዊነት ደረጃ የሚያሳይ ነው ሲል ኢዜማ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መንግስት ለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶች ለተጎጂዎች የሚሰጥን እርዳታ ላልታለመለት አገልግሎት እያዋለው ነው በሚል እርዳታ ማቆማቸውን ተከትሎ መግለጫ አውጥቷል።

መንግሥት ከታረዙ ዜጎች ጉሮሮ የሚነጥቀው ሰብዓዊ እርዳታ ሃገራችን ያለችበትን የከፋ የሌብነት፣ ሙስና እና ኢ-ሰብዓዊነት ደረጃ የሚያሳይ ነው ሲል ያስታወቀው መግለጫው ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ተቋማትን እና መዋቅሮችን በመጠቀም የተረጂዎችን ነጻነት በሚነጥቅ ሁኔታ የፖለቲካ ትርፍ ማስገኛ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው ሲል ኮንኗል፡፡

ኢዜማ በመግለጫው በኢትዮጵያ ለዜጎች መዋል የነበረበትን ፍጆታ ለግል ጥቅም ማዋል፣ በአደባባይ ለሽያጭ ማቅረብ፣ የተጋነነ የተረጂዎችን ቁጥር በማቅረብ በሌሉ ሰዎች ስም እርዳታን መቀበል እና የእርዳታው ተጠቃሚዎችን ከተተመነላቸው ድጋፍ በታች በመስጠት ትርፍን መውሰድ አይነት አሳፋሪ ተግባሮች ሲፈጸሙ ይስተዋላል ሲል አሳስቧል።

ብልፅግና ፓርቲ ከኢሕአዴግ በወረሰው መጥፎ ጠባይ፤ ባለፈው ሃገራዊ ምርጫ የገጠር እና የከተማ ሴፍቲኔት መርኃግብሮችን ለምርጫ ድምፅ መግዣ አድርጎ በስፋት ተጠቅሞበታል ሲል አውስቷል። “ብልፅግናን ካልመረጣችሁ የሴፍቲኔት ድጋፉን እናቋርጣለን” በሚል ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ማስፈራሪያ እንዲሁም ለሴፍቲኔት ፕግራም የተመደቡ በጀቶችን ለምርጫ ቅስቀሳ ጥቅም ላይ የማዋል ተግባራት ሲፈጸሙ እንደነበር የአደባባይ ሀቅ ነው ብሏል።

መንግሥት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ህይወታቸውን ማቆያ የሚሆንን የእርዳታ እህል መዝረፍ እና እንደ ሃገር መከላከያ ያሉ ተቋማትን ስም በሚያጠለሽ ሁኔታ እንዲነሳ ማድረጉ የመንግሥት የሞራል ዝቅጠትን ጥግ ያሳያል ሲል ገልጿል።

ህወሓት ለትግራይ ህዝብ የተሰጡ ዕርዳታዎችን ላልታለመለት አላማ እያዋለ ነው ሲል የኮነነው ኢዜማ እየደረሱበት ያሉ ተቃውሞዎችን ለመከላከል እንዲጠቀምበት፣ በጦርነቱ ለማገዳቸው ታጣቂዎች አሳልፎ በመስጠት የራሱን ፖለቲካዊ ጥቅም እንዲያስጠብቅ ለማድረጉ ዋነኛ ተጠያቂው የፌደራል መንግሥት መኾኑ ሊሰመርበት ይገባል ሲል አሳስቧል።

መንግስት ከእርዳታ ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ብልሹ አሠራሮችን እንዲያጸዳ የጠየቀው ኢዜማ በየትኛውም ደረጃ የሚደረግን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለፖለቲካ ፍጆታ፣ ለምርጫ ቅስቀሳ እና ለገፅታ ግንባታ የመጠቀም አባዜም በአስቸኳይ እንዲያቆም ሲል ጠይቋል።

ዓለምአቀፍ የተራድዖ ድርጅቶችም በመንግስት ብልሹ አሰራር ሳይደናገጡ የእርዳታው ተደራሽነት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የእርዳታ አቅርቦቱ እንዲቀጥል ጠይቋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.