አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16/2014:- ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በሦስት ቀናት ውስጥ በአጠቃላይ 10 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ አካላት መታሰራቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል። በቁጥጥር ስር የዋሉት በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር እና አዲስ አበባ መሆኑን መገናኛ ብዙሀኑ እና ከእስረኞቹ ቤተሰቦች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የተያዘችው መምህርትና ጋዜጠኛ መስከረም አበራ ዛሬ በአዲስ አበባ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀረበች።
ትናንት ሰኞ ግንቦት 15 ቀን በዚሁ ፍርድ ቤት ቀርባ ፖሊስ ተጠርጣሪዋ ላይ ምርመራ ለማድረግ 14 ተጨማሪ ቀን ይሰጠኝ ሲል ችሎት ጠይቆ ነበር። በእለቱም መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኛዋን “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት እንዲሁም በአማራ ክልል እና በፌደራል መንግስት መሀከል ችግር እንዲከሰት በሚዲያ ቅስቀሳ አድርጋለች” በሚል ጥርጣሬ ምርመራ እያደረኩ ነው ሲል ለችሎት ያስረዳ ሲሆን ፖሊስ አክሎም ግብረአበሮቿን ለመያዝ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ደንበኛቸውን በእስር ይዞ ግብረአበሮች ለመያዝ በሚል የጠየቀው አግባብ አይደለም ብለው የተከራከሩ ሲሆን ጥያቄውም ከሚዲያ ነፃነት ጋር የሚጋጭ መሆኑን አስረድተው ደንበኛቸው የምትሰራው ስራ በሚዲያ ሚታወቅ ነው ብለው ሞግተዋል። ደንበኛቸው ወንጀል ሰርታ ቢሆን ኖሮ በአደባባይ ልትንቀሳቀስ እና ቦሌ አየር መንገድ ላይ ልትያዝ እንደማትችል ካብራሩ በኋል የ7ወር ህፃን ጡት ስለምታጠባ እንዲሁም ቋሚ የሆነ የመኖሪያ አድራሻ ስላላት በዋስትና ወጥታ ችሎቷን እንድትከታተል ሲሉ ጠበቆቿ ችሎቱን ጠይቀዋል።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎት መዝገቡን መርምሮ ፖሊስ በጠየቀው 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ግንቦት 16 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል።
ዛሬ በነበረው ችሎት የተከሳሿ ጠበቆች ደንበኛቸው የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጥባት በቀጥታ ወደ ክስ እንድትገባ የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ምክንያቱንም “የተከሰሰችበት ሁከት እና ብጥብጥ በማስነሳት” ስለሆነ ብዙ የማጣራት ስራ እንደሚያስፈልገው አብራርቷል። ስለሆነም ፖሊስ ምርመራውን እንዲያካሂድ 13 የምርመራ ቀናትን የሰጠ ሲሆን ተለዋጭ ቀጠሮው ግንቦት 29 እንዲሆን ወስኗል።
ግንቦት 11 2014 ከሚሰሩበት እስቱዱዩ አምስት የአሻራ ሚዲያ ጋዜጠኞች እና የካሜራ ባለሙያዎች በፀጥታ ሀይሎች ታስረው መወሰዳቸውን አዲስ ስታንዳርድ ማወቅ ችሏል። ቀለሙ ገላጋይ አቅኔ እና ዳንኤል መስፍን የአሻራ ሚዲያ የካሜራ ባለሙያና ኤዲተሮች ሲሆኑ፣ ጋሻየ ንጉሴ ፈረደ፣ ጌትነት ያለው እንዲሁም ሀብታሙ መለሰ ጋዜጠኞች መሆናቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል በገበያ ዩትዩብ ቻናል እና በቀድሞ ‘በሻይ ቡና’ ፕሮግራሙ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ ግንቦት 12 ቀን ረፋድ ላይ የፀጥታ አካላት ወድ መኖሪያ ቤቱ አቅንተው በቤት ውስጥ ባለመኖሩ እህቱን ይዘው ወደ ጣቢያ ውስደዋታል ። ሰለሞን የእህቱን መታሰር በሰማ ጊዜ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄደ ሲሆን እሱን አስረው እህቱን ለቅዋታል። የጋዜጠኛው እህት ትዕግስት ሹምዬ ለሮይተርስ የዜና አውታር እንደተናገረችው አርብ ግንቦት 12 ቀን ከሎሎች ሶስት ተጠርጣሪዎች ጋር በጸጥታ ሃይሎች ከተያዘ በኋላ ፍርድ ቤት እንደቀረበ አስረድታ፣ ፍርድ ቤቱም የ14 ቀን እስራት እንደበየነበት አስረድታለች።
በሌላ በኩል ትዕግስት ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር አጭር ቃለ መጠይቅ ያደረገች ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ሰለሞን በአዲስ አበባ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩን እና ቀጣይ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ግንቦት 22 እንደሆነ ተናግራለች።
አዲስ ስታንዳርድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ከታሰሩት የአሻራ ሚድያ ጋዜጠኞች መካከል የአንደኛውን የቅርብ ጓደኛ ያነጋገረች ሲሆን የጋዜጠኞቹ መታሰር እውነት እንደሆነ አረጋግጠው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም አክለው ተናግረዋል።
ንስር ሚድያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ግንቦት 11/2014 ከቀኑ 10፡45 ላይ የደህንነት ሃይሎች ከአማራ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ባህርዳር የሚገኘውን የንስር ብሮድካስት ቅርንጫፍ ስቱዲዮ በመውረር በስራ ላይ የነበሩ ጋዜጠኞቻችን እና መገልገያ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን ‘በህገወጥ መንገድ ‘ እንደተወሰደባቸው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ ኮሚሽን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በበኩሉ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች “በተቀናጀ መንገድ የሕግ በላይነትን ማስከበር” በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት በወሰዱት እርምጃ ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሊወስድ የሚችላቸውን እርምጃዎች ኢሰመኮ እንደሚገነዘብ ካሳወቀ በኋላ፣ “የዚህ አይነት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን” የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል። “በተለይም የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በስራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ ይገባል፣ እንዲሁም በማናቸውም አይነት ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ወዲያውኑ እንዲያውቁ እንዲደረግና ወደ ፍርድ ቤትም ሊቀርቡ ይገባል” ብለዋል፡፡ አስ