አዲስ አበባ፣ሀምሌ 4 / 2014 ዓ.ም – በኮንሶ ዞን በዝናብ እጥረት ምክንያት 190 ሺህ ህዝብ በላይ ለረሃብ የተጋለጡ መሆኑንና ወቅቱን ባልጠበቀ የዝናብ ሁኔታ የተነሳ ከ24ሺ ሄክታር በላይ በዘር የተሸፈነ መሬት ምርቱ በመጥፋቱ ህብረተሰቡ ለከፋ ችግር መጋለጡን የኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
ዞኑ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ባለፈው ሳምንት በምግብ እጥረትና ሳቢያ 13 ህፃናት መሞታቸውን የዞኑ ዋና የመንግሥት ተጠሪ ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡
የኮንሶ ዞን ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ ጫሬ እንደገለፁት በቀጣይ ስድስት ወራት በዞኑ ውስጥ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከ 190 ሺ በላይ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 122 ሺህ 735 በዝናብ እጥረት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሲሆኑ፣ 68,087 የሚሆኑት ደግሞ በግጭት ምክኒያት ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁ መሆናቸውን አመልከተዋል። በምግብ እጥረት የተነሳ ክፉኛ የተጎዱ 244 ህፃናት የፅኑ ህሙማን ክፍል ገብተው በህክምና ላይ ሲሆኑ በዞኑ ሶስት ወረዳ ውስጥ በምግብ እጥረት ክፉኛ ታመው ወደ ጤና ጣቢያዎች የሚወሰዱ ህፃናት ቁጥር መጨመሩንም አቶ ተስፋዬ አክለው ገልፀዋል፡፡
በያዝነው አመት ሚያዝያ ወር አዲስ ስታንዳርድ ባወጣችው ሪፖርት በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን ተቀስቅሶ የነበረው የእርስ በርስ ግጭት ለነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት እንደነበር መዘገቧ ይታወሳል።
በኮንሶ ዞን የምርት ዘመን በአራቱ ዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች ከተዘራዉ 96,157.3 ሄክታር መሬት 24,202 ሄክታር ምርት በድርቅ በመጥፋቱና የመኸር እርሻ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ምክንያት በመሆኑ ህብረተሰቡን ለረሃብ መዳረጉን የኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ ዘርፉ ላቀው ገልፀዋል፡፡
በያዝነው አመት ሚያዝያ ወር አዲስ ስታንዳርድ ባወጣችው ሪፖርት በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን ተቀስቅሶ የነበረው የእርስ በርስ ግጭት ለነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት እንደነበር መዘገቧ ይታወሳል። በወቅቱ አዲስ ስታንዳርድ የተባበሩት መንግስታትን ሪፖርት ዋቢ አድርጋ በግጭቱ በዞኑ ከሚገኙ 10 ቀበሌዎች ወደ 37,000 የሚጠጉ የተፈናቀሉ እንደነበሩ እና ከነዚህም ውስጥ 19,000 የሚጠጉ ሴቶችና ልጃገረዶች መሆናቸውን አክላ ዘግባ ነበር።
ይህ የተመድ ዘገባም በተጠቀሰው ወር በኮንሶ እና ዳርሼ ማህበረሰብ መካከል በተነሳው የእርስ በርስ ግጭት በሰገን ዙሪያ ወረዳ ብቻ ከ32000 በላይ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ የገለፀ ሲሆን ከ3,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከካራት ዙሪያ ወረዳ ፉጩጫ ቀበሌ እንደሆኑ፣ ከ1,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቦርቃራ እና ማታራጊዛባ ቀበሌዎች እንደተፈናቀሉ አክሎ ተናግሮ ነበር። ሪፖርቱ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በሰገን ዙሪያ እና ካራት ዙሪያ ወረዳዎች ከሚገኙት ማህበረሰብ ጋር እንደሚቆዩ ገልፆ የነበረ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በዞኑ በሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙም አስታውቆ ነበር። የክልሉ ባለስልጣናት ለተጎጂው ህዝብ 50 ሜትሪክ ቶን ምግብን ድጋፍ ማድረጉን ጋልጾ እንደነበር እና ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ መናገሩም ይታወሳል።
በኮንሶ ዞን ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የሚጥለው ዝናብ ወቅቱን የጠበቀ ባለመሆኑ እንዲሁም በተከታታይ በነበሩ ግጭቶች የተነሳ ለከፋ ረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ በመኸሩ ወቅት በዞኑ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚረዱት ተጠቃሚዎችን ሳይጨምር በድርቅና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተራቡ እና በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ከ126,800 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የፌዴራልና የክልል መንግስት የምግብ ግብዓት ድጋፍ እንዲያደርግ የተጠየቀ ሲሆን የተደረገው የህፃናት አልሚ ምግብና ሌሎች ግብዓት እርዳታ ከተጠቀሱት ተጎጂዎች መካከል ለ34,386 ተጎጆዎች ብቻ ምላሽ በመስጠቱ በበልጉ የምግብ ዋስትና ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ጫና እንደፈጠረ ከኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት ያወጣው መረጃ የመላክታል፡፡
በዝናብ መዛባትና የተዘራዉ ሰብል ሳይደርስ መጥፋቱን ተከትሎ ተዘርቶ ከበቀለ በኋላ በዝናብ መጥፋት ምክንያት የጤፍ፣በቆሎ፣ማሽላ፣ቦሎቄ፣ማሾ፣ሰሊጥና ሱፍ በድምሩ 30,565.8 ሄክታር ሰብል መውደሙን የኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ የተዘሩት ቋሚ ሰብሎች የምርት ጉዳቱ ሽፋን 33.8% መውደሙን አስታውቀው፤ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ በዜጎች ላይ ከዚህ በበለጠ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ እንደሚከሰት ተጠቁሟል፡
የዝናብ ማነሱ የፈጠረው ችግር የምርት ማነስ ብቻም ሳይሆን በተፋሰሶችና በተከለሉ የግጦሽ መሬት የእንስሳት መኖ በመድረቁ እንሰሳት ለረሃብ መዳረጋቸውን አቶ ዘርፉ ላቀው አስረድተዋል፡፡
ዞኑ በምግብ እጥረት፣ በግጭት እና በኑሮ ውድነት እየተፈተነ መሆኑን ያነሱት አቶ ተስፋዬ፣ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች 20 ትምህርት ቤቶች በመቃጠላቸው የተነሳ 10 ሺህ 430 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ከአሁኑ ጥገና ካልተደረገላቸው በ2015 ዓ.ም ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው እንደሚቆዩ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
የደቡብ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምኣ በኮንሶ ዞን በተለያየ ወቅት በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ለተፈናቀሉ እንዲሁም ሰብላቸው በዝናብ እጥረት ምክንያት ለተጎዳባቸው ሰዎች የምግብ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን ለቢቢሲ የገለፁ ቢሆንም ነዋሪዎቹ ግን የመንግስት እርዳታ በመጠባበቅ ላይ ነን ብለዋል፡፡ የዞኑ ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው የሴፍቲኔት እርዳታው እየቀረበ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ያስረዳሉ።
ከቅርብ ሳምንታት ጀምሮ በኮንሶ እና አሌ ልዩ ወረዳ አጎራባች አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት በተለያዩ ቦታዎች የህብረተሰቡ ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የአሌ ልዩ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ገልፆም እንደነበር የሚታወስ ነው። አስ