ዜና ትንተና፡ የደቡብ ክልል ባለስልጣናት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይፋዊ ውሳኔ ወይም ህዝበ ውሳኔ ሳይሰጥ “የማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ክልልን ስለመመስረት ተወያየ

አዲስ አበባ፣ህዳር 22/2015 .ም፡ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የጉራጌ ዞንን በማጠቃለል በቅርቡ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ”  በሚል ለሚደራጅው  አዲስ ክልል አመሰራረት  እቅድ ላይ ህዳር 20  ቀን 2015 ዓ.ም በቡታጅራ ከተማ ውይይት አድጉ።

በክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የተመራው ውይይት በክልሉ የሚገኙ  ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ከምባታ ጥምባሮ እና ሀላባ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳ ያለ ህዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል እንዲደራጁ ለማድረግ ያለመ ነው። 

ነገር ግን እስካሁን ድረስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስካሁን ከላይ የተጠቀሱት ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ‘የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል’ በሚል እንዲደራጁ ይፋዊ አቅጣጫ አልሰጠም።

የፌደሬሽ ምክር ቤቱ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የሚገኙ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች በጋራ ”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የመመስረት ጥያቄ በማቅረባቸው በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ውጤቱ ለምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ቦርዱ የማደራጀት ጥያቄው ላይ ውሣኔ አስተላልፎ ነበር፡፡

ምርጫ ቦርድም የፌደሬሽ ምክር ቤቱ ጥያቄን ተቀብሎ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔውን እንደሚያደራጅ ነሐሴ 18/ 2014 ዓ.ም መግለፁ ይታወቃል፡፡

በተቃራኒው ግን ሀዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ-ጠንባሮ፣ ጉራጌ እና የስልጤ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተዳደር እንዲቀጥሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወስኗል።

የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ አስመልክቶ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔ መሠረት ያለ ህዝበ ዉሳኔ በቀጥታ በአዲስ መልክ ለሚደራጀዉ የ’ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል’ አደረጃጀት እየተሰራ  መሆኑን አቶ ርስቱ ይርዳው ጠቁመዋል ብሏል።

 የአደረጃጀት ሥራዉን የሚያስተባብር የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተዋቅሮ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለፁት አቶ ርስቱ አዳዲስ ክልሎችን የማደራጀቱ ተግባር የአብሮነትንና የህዝቦችን ትስስር በሚያጠናክር አግባብ እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡምጥሪ አስተላልፈዋል።

በዚህም መሰረት ያለ ህዝበ ውሳኔ ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮና ሀላባ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ‘በአንድ ክልል ተደራጅተው ‘ ‘ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል’ በሚባል ክልል ስር እንደ አዲስ ይደራጃሉ ተብሏል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በመድረኩ ተገኝተው የየደረጃው አመራሮች ስራውን ስኬታማ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

ዳራ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ በርካታ ዞኖችና የአካባቢው ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም  በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አስተዳደር ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ክልላዊ መንግሥትን ለማቋቋም ውሳኔ ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡   ውሳኔው በክልሉ ውስጥ የሚመሰረቱትን ክልላዊ መንግሥትን ቁጥር የሲዳማ እና የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ጨምሮ ወደ አራት ከፍ ያደርገዋል።

በምክር ቤቶች በዞን ደረጃ ጥያቄ ውስጥ የገቡት ፡- ኮንሶ፣ ጌዴኦ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና ወላይታ፣ ሀዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጥምባሮ እና ስልጤ ዞኖች ሲሆኑ እንዲሁም  በልዩ ወረዳዎች ደረጃ ያሉ ደግሞ ምክር ቤት፡ አማሮ፣ አሌ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደራሼ እና የም ልዩ ወረዳዎች ነበሩ።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ሚዲያዎች የጉራጌ ዞን ዝርዝሩ ውስጥ ተካቷል ብለው የዘገቡትን በማስተባበል የዞኑ ምክር ቤት ወደሌሎች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር አንድ ላይ በመሆን በአዲስ ክልላዊ መንግስታት  አመመስረት አልተወያየም በማለት ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል።

ይልቁንም የዞኑ አስተዳደር በህዳር 17፣ 2011 ዓ.ም ያቀረበውን የክልልነት ጥያቄ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ እየጠበቀ ነው ብሏል።

ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. የደቡብ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ አቶ ክፍሉ ዋና የ16 ዞኖችን እና ልዩ ወረዳዎችን ስም ዝርዝር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤው አቅርበው ለተጨማሪ ሁለት ክልሎች ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በዚህም መሰረት ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ እና ወላይታ ዞኖች ሲሆኑ አምስቱ ልዩ ወረዳዎች ደግሞ፡- አሌ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ ደራሼ  የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ጥያቄውን ካፀደቀ በኋላ አንድ ክልል ይመሰርታሉ። በተመሳሳይ አራት ዞኖች ሀዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጠምባሮ እና ስልጤ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል ይደራጃሉ የሚል ነበር። 

አቶ ክፍሉ  የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ለጥያቄው  “በሕገ መንግሥቱ ላይ የተመሠረተ” ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም  በሰጠው ምላሽም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩት የ6 ዞኖችና የ5 ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል የእንደራጅ አቤቱታን ተቀብሎ ከመረመረ በኃላ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ እንዲቀጥሉ ውሳኔ አስተላልፏል።

ምርጫ ቦርድ በ6ቱ ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የካቲት 06 ጥር 29 2015 ዓ.ም  ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን ማሳወቁ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ከአራቱን ዞኖች ማለትም ሀዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጥምባሮ እና ስልጤ ዞኖች ጋር በጋራ  በመሆን አዲስ ክልል ለመመስረት የሚደረገውን ሙከራ መቃወሙን ቀጥሏል።

የዞኑ ምክር ቤት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፕሬዘዳንት እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ነሀሴ 13 ባካሄደው ስብሰባ የጉራጌ ዞንን በደቡብ ክልል ስር ከሚገኙ ሌሎች 4 ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ጋር በማዳመር የጋራ ክልል ለመመስረት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብን ከአጠቃላይ 97 የምክር ቤቱ አባላት 52 የምክር ቤት አባላቱ በመቃወም ውድቅ አድርገውታል።

ከዞኑ ምክር ቤት ስብሰባ ቀደም ብሎ በክላስተር የመደራጀት ውሳኔውን በመቃወመም በወልቂጤ ከተማና በሌሎች ወረዳዎች ስራ የማቆም አድማ ማድረጋቸው አድረገው ነበር፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የዞኑ አመራሮች እና  የመምሪያ ኃላፊዎች ላይ እስራት የተፈፀመ ሲሆን ከእንዚህ መካከል የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ምነወር  ሀያቱ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ ማሪያም፣ አቶ አበበ አመርጋ የዞኑ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ይገኙበታል፡፡

ትናንት ህዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራር የጉራጌ ዞንን ወደ ክላስተር በማካተት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን እንዲቀላቀል የተወሰነው ውሳኔ የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሙሉ የጉራጌ ዞንን ላልተወሰነ ጊዜ በኮማንድ ፖስት ስር ካዋለ በኋላ ነው፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.