ዜና፡ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/ 2015 ዓ.ም፡- የፌደራል የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወይም ሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በቅርቡ ተቋቋሞ ጠቅላይ ሚንስቴሩ ይፋ ያደረጉት  የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ።

ብሔራዊ ኮሚቴ ስራውን በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ የሰጠ ሲሆን  በመግለጫው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በተጨማሪ በብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ የስራ ሃላፊዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የተሰጣቸውን ሀላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም ከግለሰቦች እና ከድርጅቶች ላይ ገንዘብ እና ንብረት ወስደዋል በሚል ተጠቁሞ ነው፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባም የአርሶ አደር ልጆች ያልሆኑ ልጆችን በማስመሰል፣ የልማት ተነሽ ሳይሆኑ በሀሰት ሙስና የሰሩ ግለሰቦች መለየታቸው ተመላክቷል፡፡

175 ሺህ ካሬ ቦታና የኮንዶሚንየም ቤት ምዝበራ የፈፀሙ እንዲሁም በፍትህ ዘርፉ ስልጣናቸውን በመጠቀም ከግለሰቦችና ከንግድ ተቋማት ጋር ሲሰሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል ተብሏል።

ብሄራዊ ኮሚቴው በተቋቋመ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከህብረተሰቡ ከ250 በላይ ጥቆማዎች መሰብሰባቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ ህብረተሰቡ ሙሰኞችን በማጋለጡ ረገድ ጥቆማውን አጠናክሮ አንዲቀጥልም ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።

መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህዳር 08/2015 ዓ.ም አስታወቀው ነበር፡፡

ኮሚቴ ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ እነርሱም፡- አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ፣ አቶ ተክለ ወልድ አጥና፣ አቶ ሰሎሞን ሶቃ፣ አቶ ደበሌ ቃበታ፣ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና አቶ አብዱሃሚድ መሃመድ ናቸው፡፡

በወቅቱ መንግሥት በጥናት በደረሰባቸው የመንግሥት ሹመኞች፣ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ አቀባባዮችና ጉቦ ሰጪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፆ ነገር ግን ሙስና በባሕሪው በረቀቀ መንገድ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አንዳንድ ጊዜም በሕጋዊነት ሽፋን የሚካሄድ በመሆኑ በመንግሥት ጥናት የተደረሰባቸው አካላትን ብቻ ለሕግ በማቅረብ የሚፈታ አይደለም ብሏል፡፡ አክሎም ሙስናን ከሥር ከመሠረቱ ለመንቀል እንዲቻል ከሕግና ከአሠራር ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ የሙስና ተዋንያን ሁሉ ሙስናን እርም እንዲሉ የሚያደርግ ርምጃ ያስፈልጋል ሲል መግለፁ ይታወሳል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.