አዲስ አበባ መጋቢት 27፣ 2014 – በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቅምቢቢት ወረዳ 280 ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ‘በማይታወቅ ሁኔታ’ በአማራ ክልል መንግስት አስተዳደር ስር መግባቱን የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መግለጫ አስታውቋል። በተጨማሪም የአማራ ልዩ ሃይል በወረዳው መሰማራቱ የአካባቢውን አርሶ አደሮች በነፃነት እንዳይዘዋወሩ እያደረጋቸው መሆኑንም መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል።
የኮሙዩኒኬሽን ቢሮው ለሦስት አስርት አመታት የዘለቀው የመሬት ወረራ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ህይወት አደጋ ላይ መጣሉን ገልፆ አካባቢው ባለፉት አመታት በአማራ ክልል አስተዳደር ስር እንደገባ ገልጿል።
መግለጫው በ1977 የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ከ22 አባወራዎች 280 ሄክታር መሬት በመያዝ ለምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) ቢሮ ለመክፈትና ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘመናዊ የበግ እርባታን ለማስተዋወቅ ቃል በመግባት መሬቱን መያዙን አስታውሷል።
በቅምቢቢት ወረዳ የሲንቄ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ፍቃዱ ረጋሳ በወቅቱ ማህበረሰቡ የስራ እድል፣ የምርምርና ልማት ተጠቃሚነት እና ለልጆቻቸው የወደፊት ጥሩ እድል ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
የፍቃዱ በእርሻ ስራ የሚያስተዳድራቸው ስምንት ቤተሰብ አባላት አሉት። ከአባቱ ከአራት ሄክታር በላይ መሬት መወሰዱን ገልጾ፣ በቀራቸው መሬት ላይ ለቤተሰቡ የሚሆን በቂ ምግብ ማምረት እንዳልቻለ ያስረዳል። ፍቃዱ የልጆቹ የትምህርት ክፍያን ለመሸፈን የጉልበት ስራ እየሰራም ይገኛል።
በመግለጫው የምርምር ማዕከሉ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የገባውን ቃል ሳይፈጽም ሥራውን ማቆሙን ገልጾ “ተቋሙ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሥራውን ሲያቆም ፣ መሬቱን ለአካባቢው አርሶ አደሮች ሳይሆን ለሠራተኞቹ አሳልፎ እንደተሰጠና “በአሁን ሰዓት መሬቱ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር እንደሚገኝ” አሳውቋል።
ከዚያም መሬቱ ለወተት ማምረቻ ድርጅት መሰጠቱን አቶ ፍቃዱ አስታውሰዋል። ከአመታት በኋላ መሬቱ በአማራ ክልል መተዳደር ስር ገብቷል ሲል የሚናገረው ፍቃዱ “መሬታችን እንዴት በሌላ ክልል ስር እንደገባ አናውቅም። ለኦሮሚያ ክልል መንግስት ያቀረብነው ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ ሆኑል” ብሏል፡፡
በተቋሙ መሬታቸው የተወሰደባቸው ሌላው አርሶ አደር ወርቁ ዳዲ በበኩላቸው “ተወካዮቻችንን ወደ መንግስት መስሪያ ቤቶች ስንልክ ቆይተናል ነገርግን አንዳቸውም ለጉዳያችንን ትኩረት አልሰጡም” በማለት ገልጿል።
የመንግስት አካላቱ መሬታችን በህገ ወጥ መንገድ መነጠቅ እንደሌለበት ነግረው ቢያጽናኑንም ፍትህ ግን ሊሰጡን በፍጹም አይሞክሩም” ብለዋል። በመቀጠልም “በቅርብ ጊዜ ይህ አካባቢ የአማራ ክልል እንደሆነ እና ከአማራ ክልል የተሰጠ መታወቂያ ከሌለን ስራ እንደማናገኝ ተነግሮናል። አሁን መሬቱ ለአማራ ልዩ ሃይል ወታደራዊ ካምፕ ሆኖ እያገለገለ ነው፣ መንቀሳቀስ ስጋት ሆኖብናል ብሏል።
ነዋሪዎቹ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት በተቋሙ መሬታቸውን በህገ ወጥ መንገድ ከተወሰደባቸው 22 አባወራዎች መካከል ጥቂቶቹ ወደ ሌላ አካባቢ የተሰደዱ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በድህነት ውስጥ ይገኛሉ።
የቅምቢቢት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ ነጋሽ የአካባቢው አርሶ አደሮች የሰጡትን አስተያየት በማረጋገጥ ለአካባቢው አርሶ አደሮች አጋርነታቸውን ገልጸዋል። አመራሩ ከዞን እስከ ፌዴራል ባሉ የመንግስት መዋቅሮች የፍትህ ጥያቄውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ህብረተሰቡም እንዲታገስ አሳስበዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ተጨማሪ መረጃ የቅምቢቢት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ ነጋሽ እና የወረዳው የመሬት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ቶለሳ ሁንዴን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።አስ