ዜና: 26 ሚሊሻዎች በታጣቂዎች መገደላቸው ተሰማ

አዲስ አበባ መጋቢት 22፣ 2014:- ከአማራ ክልል ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ታጣቂዎች እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በፈንታሌ ወረዳ በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ የሚሊሻ አዛዡን ኮማደር አብዲሳ ኢፋን ጨምሮ በበርካታ ታጣቂዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱ ተገለጸ። ግጭቱን ተከትሎ ከሁለቱም ወረዳዎች እርስ በእርስ የሚጣረሱ  መግለጫዎች ተሰጥተዋል።

የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦሰት እንደተናገሩት አሞራቤት ቀበሌ ልዩ ቦታዉ አዉራ ጎዳና ተብሎ በሚጠራ መንደር የተደራጀና የታጠቀ ሃይል በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በከፈተው ጥቃትና ባደረሰው ጥቃት የሰዉ ህይወት ሲያልፍ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ከኦሮሚያ ክልል መሆናቸውን እና ወደ ቀበሌው የገቡት በአጎራባች ፈንታሌ ወረዳ በኩል መሆኑን አቶ ታደሰ ጨምረው ተናግረዋል። ጥቃቱ የተፈፀመው መጋቢት 20, 2014 ዓ.ም. ከቀኑ በሰባት ሰዓት ላይ ሲሆን የተጎዱ ሰዎች በአቅራቢያው ወደሚገኙ ሆስፒታሎች እና የቀሩት ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ተወስደዋል። አቶ ታደሰ አክለዉም ሴቶችና ህጻናት ወዲያውኑ ከአካባቢው እንዲወጡ መደረጉን እና ብዙ ሰዎች ወደ ጫካ መሰደዳቸውን አስረድተዋል። የሸሹት ሰዎች ሁኔታ እንደማይታወቅም ገልጸዋል።

የፋንታሌ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ በትላንትናው እለት በሰጠው መግለጫ  በአካባቢው የሚገኙ ታጣቂዎች ቆርኬ በሚባል ቦታ ስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ‘ፅንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች’ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል። የአካባቢው ሚሊሻ አዛዥ ሻምበል አብዲሳ ኢፋ እና ሌሎች በርካታ አባላትም መገደላቸውን በመግለጫው ጨምረው አስታውቋል። የፈንታሌ ወረዳ አስተዳደር የወረዳውን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትን ለህግ እንደሚያቀርብ ያስታወቀ ሲሆን  በወረዳው የበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱንም አስታውሰው የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የምንጃር ሸንኮር ወረዳ አስተዳዳሪ ቀደም ሲል ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል። “የዚህ ጥቃት መንስኤ ግልጽ ባይሆንም ማንነታቸው ባልታወቁ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ሆን ተብሎ ነዋሪዎችን ለማፈናቀል የተነሱ እንደሆኑ መገመት ይቻላል” ብለዋል። በእለቱም የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው  በመግባቱ ግጭቱ ከምሽቱ 12 ሰዐት በኋል እንደተረጋጋ አቶ ታደሰ ተናግረዋል። 

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ በበኩላቸው በአሞራቤት ቀበሌ በኩል  ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸውን ለክልሉ ሚዲያ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ ለጸጥታ ሃይሎች እንዳሳወቁት የፌደራል ፖሊስ ሊያናግራቸው ሲሞክሩ ታጣቂዎቹ ተኩስ ከፍተዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ ለጠፋው ህይወት ማዘኑን ገልፆ ጥቃቱ ላይ ከነበሩት የአካባቢው ሚሊሻዎች በተጨማሪ የፌደራል ፖሊስ አባላትን ህይወት ቀጥፏል ብሏል። የክልሉ መንግስት ጥቃቱን ያደረሰው በምንጃር ሸንኮር ወረዳ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች ናቸው ሲልም አሳውቀዋል ።

የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ ‘ፀረ-ሰላም ቡድኖች’ ሲል በጠራው ቡድን ላይ የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ እንዳይሰራጭ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።  መግለጫው  ‘በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎችን በተሳሳተ መንገድ እንዳይገልጹ አስጠንቅቋል። በሸንኮራ ወረዳ በጠፋው የሰው ህይወት ማዘኑን የገለፀው የክልሉ መንግስት መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርቧል።

ቀደም ሲል የምንጃር ሸንኮር ወረዳ አስተዳዳሪ ከሰጡት መግለጫ በተቃራኒ የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ጥቃቱን የፈፀሙት በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ በህገ-ወጥ መንገድ የታጠቀ አክራሪ ቡድን ነው ብለዋል።.ግጭቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክሩ ከነበሩ ከ26 ሰዎች መካከል 2 የፌደራል ፖሊስ አባላት እና አንድ ሹፌር መሞታቸውን  ተናግረዋል።

አቶ አባቡ ጥቃቱ የተፈፀመው በኦሮሚያ ክልል ግዛት ውስጥ ነው በማለት ተናግረዋል። እርሳቸው የሰጡት መግለጫ ከኦሮሚያ ክልል  ወደ ቀበሌው በመጡ ታጣቂዎች ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል ከሚለው ከምንጃር ወረዳ አስተዳዳሪው  መግለጫ ጋር የሚቃረን ነው። የምንጃር ሸንኮር ወረዳ አስተዳዳሪ ከቪኦኤ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ታጣቂዎቹ የፌደራል ፖሊስ አባልን ገድለዋል ሲሉ መናገራቸው የታወቃል።

የፌደራል መንግስት ስለጉዳዩ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ተጨማሪ አስተያየት አልሰጡም። አዲስ ስታንዳርድ የሁለቱን ክልሎች የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ  ሙከራ አልተሳካም።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.