ዜና: በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ በሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ 20 ሰራተኞች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

በጌታሁን ለገሰ @Birmaduu2

አዲስ አበባ፣ጥር 22/ 2015 ዓ.ም፡– በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን አዲያ በርጋ ወረዳ የሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ 20 ሠራተኞቹ ባልታወቁ ታጣቂዎች መታገታቸውን በጉዳይ በቂ መረጃ ያላቸው አንድ የኩባንያው ባልደረባ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።

ባልደረባው አዲስ ስታንዳርድ በስልክ እንደገጸው ጠለፋው የተፈፀመው ሀሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓም ከቀኑ 10 ሰዓት 30 አካባቢ ሲሆን ሰራተኞቹ የታገቱት ኩባኒያው ውሃ የሚያገኝበትን የተበላሸ የውሃ ፓምፕ ጣቢያ ለማደስ ስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ከሙገር ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

ኩባንያው እስካሁን ድረስ የአጋቾቹን ማንነት እና የታገቱት ሰራተኞቹ የት እና በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳሉ ማወቅ አለመቻሉንና እስካሁን የሰጠው ይፋዊ መግለጫ አለመኖሩን የገለጹት የዓይን ምስክሩ በወቅቱ ህይወቱን ከሳተው አንድ ሰራተኛ በስተቀር በሰራ ላይ የነበሩትን ሰራተኞች እና ሁለት የጸጥታ አባላት አግተዋል።

ይህ እገታ ለሁለተኛ ግዜ የተከናወነ ሲሆን ባለፈው ዓመት በታህሳስ ወር ታጣቂዎች በተመሳሳይ አካባቢ በኩባንያ አውቶቡስ ውስጥ ሲጓዙ የነበሩ 30 የድርጅቱን ሰራተኞች አግተው ነበር።

ታጣቂዎቹ ተጎጂዎችን የለቀቁት ኩባንያው ለእያንዳንዱ ተጎጂ ከ100,000 እስከ 200,000 ብር የሚደርስ ክፍያ በመክፈሉ እንደነበርም የኩባኒያው ባልደረባ ተናግሯል።

እ.ኤ.አ. በ 2010 በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተወካይ ዲፕ ካማራ እና ሁለት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በታጣቂዎች በተመሳሳይ አካባቢ መገደላቸው ይታወቃል። ይህን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት መሰል ድርጊቶችን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተው ወንጀሉን የፈፀሙ ግለሰቦችን ለመያዝ እንደሚሰራ ገልጸው የነበሩ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ለግድያው ተጠያቂ የሆነ አካል የለም። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.