አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23/ 2015 ዓ.ም – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በአዲስ መልክ በተዋቀረው የሸገር ከተማ ህገወጥ ቤቶች ፈረሳ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫውም የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የመኖሪያ ቤት እንዲፈርስ መደረጉን ደርሸበታል ብሏል። የከተማው አስተዳደር ቤቶቹን ከማፍረሱ በፊት በቂ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን እና ከነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን በዚህም ንብረቶቻቸውን በታዘዙት መሠረት ቀድመው ያነሱ ሰዎች ያሉ መሆኑን የገለጹ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ አለመደረጉን ማወቅ ተችሏል ሲል መግለጫው አመላክቷል። ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በርካታ ሰዎች ቤታቸው እንደሚፈርስ አስቀድሞ ያልተነገራቸው መሆኑን እና አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በድንገት መጥቶ እንዳፈረሰባቸው መናገራቸውንም አስታውቋል።
መንግሥት የሚወስዳቸው ማናችውም እርምጃዎች ከአድሎ የጸዱ መሆን እንደሚገባቸው ሁሉም ህጎች አስቀምጠዋል ያለው የኢሰመኮ መግለጫ ክትትል እና ምርመራ ባደረገባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ አድሏዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንዳሉ ለመመልከት መቻሉን ጠቁሟል። መግለጫው በአብነትም በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ቄስ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተያይዘው ከተሰሩ ቤቶች ውስጥ ሁለት ቤቶችን በማስቀረት ሌሎች ቤቶች እንዲፈርሱ መፈረጋቸውን አስቀምጧል። ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች አድሎው ብሔር ተኮር እንደሆነ እምነት እንዳላቸው መግለጻቸውን ያካተተው ኢሰመኮ የመንግሥት ኃላፊዎች ግን ይህ እንዳልሆነ መናገራቸውን አመላክቷል።
በአንዳንድ ቦታዎች የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳቱ ሂደት ለሁከት፣ እንግልት፣ ለአካልና ሥነ ልቦና ጉዳት እና ለእስር ምክንያት መሆኑን የጠቆመው መግለጫው በአንዳድ አካባቢዎች ቤታቸው እንዳይፈርስባቸው የተቃወሙ፣ መንገድ የዘጉ፣ ጩኸት ያሰሙ ሰዎች በጸጥታ አስከባሪዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ መደብደባቸውን፣ የተወሰነ መጠን የአካል ጉዳት መድረሱን፣ በቤተሰብና ሕፃናት ልጆች ላይ የሥነ ልቦና ጉዳት መድረሱን እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ለተለያየ የጊዜ መጠን እስር መዳረጋቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ከሰው ህይወት መጥፋት ጋር በተያያዘ በጸጥታ ሀይሎች እና ቤት ፈረሳ በተከናወነባቸው አከባቢ በሚገኙ ነዋሪዎች መካከል በተነሳ ሁከት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን የተመለከተ መረጃ እንደደረሰው ያመላከት መግለጫው አለማረጋገጡን ዝና ክትትል እያደረገበት እንደሚገኝ አስታውቋል።
ቤት የማፍረስ እርምጃው በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውስ መዳረጉን፣ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ለማቋረጥ መገደዳቸውን፤ በርካታ ቤተሰቦች የእለት ተእለት ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን፤ በርካታ ቤተሰቦች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሄድ መገደዳቸውን፤ ከፊሎቹም መንገድ ላይ ወድቀዋል ወይም በተለያዩ የሀገር ውስጥ መጠለያ ጣቢያ በመሰብሰብ የመንግሥት እርዳታ ለመጠባበቅ መገደዳቸውን የኢሰመኮ መግለጫ አመላክቷል።
በቤት የማፍረስና በግዳጅ ማንሳት እርምጃ ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች እንደሚገባ በምክረ ሀሳብነት አስቀምጧል።