ጥበብ እና ባህል: የአንጋፋው የሙዚቃ አቀናባሪ ዳዊት ይፍሩ የመጀመሪያ አልበም በድጋሚ ተለቀቀ፤ አልበሙ በዛሬው እለት በሸክላ ለሽያጭ ቀርቧል

ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ እና የሙዚቃዊ መስራች ተሸመ ወንድሙ፤ ፎቶ- ሙዚቃዊ ፌስቡክ ገፅ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21/ 2015 ዓ.ም:-ሙዚቃዊ የተሰኘ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኩባንያ የአንጋፋው የኢትዮ ጃዝ አቀናባሪው የዳዊት ይፍሩን የበኩር አልበም ከ45 ዓመታት በኋላ በደጋሚ ከተለቀቀ ከሳምንት በኋላ በዛሬው እለት በሸክላ ለሽያጭ ማቅረቡ ተገለፀ። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለውን ያለፈውን ዘመን ያስታውሳል የተባለው አልበሙ በ1970ዎቹ የተለቀቁ አስራ አንድ በሙዚቃ መሳሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎቹን ማካተቱ ተገልጿል። አልበሙ ከመጋቢት 15 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሙዚቃዊ በዲጂታል የሙዚቃ መተግበሪያዎች ለአድማጭ የቀረበ ሲሆን በዛሬው እለት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ በሸክላ ለሽያጭ መቅረቡ በሙዚቃዊ የማህበራዊ ድረ-ገፅ ተገልጧል።  

በቺክቺካ፣ ትዊስት፣ በኮንጎሊዝ ሩምባ እና ዋልትዝ የሙዚቃ ስልቶች የታጀቡት የሙዚቃ ቅንብሮቹ በወቅቱ በአፍሪካ ቀንድ ይደመጡ የነበሩ ብርቅየ ስራዎችን መለስ ብለን ለመቃኘት ያስችላል። ዳዊት ይፍሩን በዘመኑ ከነበሩ የእሱ ዘመን አቀናባሪዎች ለየት ያደረገው በቅንብሮቹ ላይ የቫዮሊን የሙዚቃ መሳሪያን ማካተቱ ነበር። በእሱ ዘመን ያልተዘወተረውን ቫዮሊን በሙዚቃዎቹ ማካተቱ ትልመኛ አቀናባሪ መሆኑን አሳይቷል ሲል ሚዩዚክ አፍሪካ ዘግቧል።

በሙዚቃ ቅንብሮቹ ላይ የምናገኛቸው ግብአቶች ተደምረው ነው በጠነከረ፣ በተቀየጠ፣ መንፈስን በሚያድስ መልኩ የኢትዮ ጃዝን የፈጠሩት ሲል የሙዚቃዊ ኩባንያ መስራች ተሾመ ወንድሙ ይገልጻል። የአሁኑ የአልበሙ ስብስብ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሙዚቃን በብርሃን መስኮተ ለማሳየት የቻለ ነው ያለው ተሾመ ጥልቅ፣ ውስብስብ እና የካበተውን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባማረ እና በሚገርም መልኩ ተርኮታል ብሏል።

ሙዚቃዊ ኩባንያ የክምችት እና የጥናት ፕሮጀክት የቀድሙ የተወደዱ ስራዎችን እንደገና የማሳተም እና የመልቀቅ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። የዳዊት ይፍሩ ስብስብ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ስራ ሲሆን ዋነኛ አላማው በስራቸው ልክ ከሀራቸው ውጭ አለም አቀፍ ዝናን እና ክብርን ያላገኙ ዘፈኖችን በአለም አቀፍ ገበያው ስራቸውን ማቅረብ እና የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ ማስቻል ነው።

ሁሉም ሀገር የራሱ ኮከቦች እና ተወዳጅ ዘፋኞች አሉት፤ ከነዚህም በበለጠ ጎልቶ የሚወጣም ይኖራል፤ ዳዊት ይፍሩ በዘመኑ ከነበሩት የሙዚቃ ሰዎች ጥቂት ለእኛ እጅግ ጎልተው ከሚወጡ እና ብርቅየ ሰው አንዱ ነው ሲል ተሾመ ወንድሙ ይገልጻል። የዳዊትን ስራዎች በዘመኑ እጅግ ጥቂት ሰዎች ታድመውት ሊሆን እንደሚችል የጠቆመው ተሾመ ለዚህም ዋነኛ ምክንያት በዘመኑ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንደስትሪ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ስለነበር መሆኑን ያስረዳል።

የኢትዮጵያ የሙዚቃ እንደስትሪ በወቅቱ ከጎረቤቶቹ ከኬንያ እና ኡጋንዳ እንኳን እጅግ ያነሰ እንደነበር የሚገልጸው ተሾመ በዚህም ምክንያት እነ ኬንያ እና ኡጋንዳ እንቁ ልጆቻቸውን በአለም አቀፍ ገበያ ሲያቀርቡ እኛ ግን ብርቅየዎቻችንን ለዚህ ደረጃ ማብቃት አልቻልንም ነበር ሲል ቁጭቱን አጋርቷል። በመሆኑም ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን ታላላቅ የሙዚቃ ስራዎች ትንፋሽ እንዲዘሩና እንዲደመጡ እንደሚያስችል ተስፋውን ገልጿል። የአልበሙ መለቀቅ አለም የኢትዮጵያን ድንቅ ስራዎች ለማየት በር ከፋች ይሆናል ሲል ተስፋውን አጋርቷል ሲል ሚዩዚክ አፍሪካ ዘግቧል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.