ሰኔ30፣2014 ዓ.ም፣አዲስአበባ፦ ትኩረቱን በዋነኛነት በዜጎች የጸጥታና ደህንነት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች የ2014 ዓ.ም 16ተኛው ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛው መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ በጉባኤው ላይ የምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2015 ዓ.ም ረቂቅ በጀትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን የቀረቡ ሲሆን ጠ/ሚንስቴሩም ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ምክር ቤቱ በተጨማሪም በ2015 ዓ.ም ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ አፅድቋል፡፡
በውያይታቸውም ወቅት የምክር ቤቱ አባላት በንጹሀን ዜጎች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን ‘የጸጥታ አካላት ማስቆም ለምን አልቻሉም?’ የሚል ጥያቄ አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የጸጥታ ሀይሎች በከፍተኛ መስዋእትነት ህግ የማስከበር ስራ እየሰሩ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል። ለአብነትም በደራሼ ብቻ ከ80 በላይ የፖሊስና የአመራር አባላት የህይወት መስዋእትነት መክፈላቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ግድያ አንዳንዶች እንደሚገልጹት “በቸልታ መንግስት ስራውን ስለማይሰራና ሃላፊነቱን ስለማይወጣ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤ መንግስት 24 ሰዓት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፤ በዚህም በጣም በርካታ ህይወት መታደግ ተችሏል፤ ያመለጡ የጠፉብን ዜጎች እንዳሉ እንደተጠበቀ ሆኖ” ብለዋል፡፡
ዜጎች ባልሰሩት ወንጀል ፣ በማያውቁት ጉዳይ በገዛ ሀገራቸው እና ቀያቸው ህይወታቸውን ለማሻሻል ደፋ ቀና ሲሉ ባልተገባ መንገድ ህይወታቸውን የሚቀጥፉ አጥፊ ስብስቦች ያደረሱባቸው ጥቃት በእጅጉ የሚያሳዝን ከመሆኑ ባሻገር ህይወታቸውን ለመታደግ ባለመቻላችን እንደ ሀገር እንደ መንግስት እንደ ህዝብ ጥልቅ ሀዘን ይሰማናል ያሉት ጠ/ሚንስቴሩ “ የንፁሃንን ደም በከንቱ የሚያፈሱ የትኛውም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትም (ሸኔ) ይሁን ሌሎች የጥፋት ኃይሎች መጥፋታቸው የማይቀር ነው፤ ማሸበር ይችሉ ይሆናል እንጂ ከዋና ዓላማችን አያስቀሩንም፡፡ በሚፈጠረው ችግር ሁሉ ህይወታቸውን የሚገብሩ የጸጥታ አካላት እንዳሉ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በየቀኑ የሚሞተው ፖሊስ ልዩ ጥቅም የሚያገኝ አይደለም። እጅግ ዝቅተኛ ደመውዝ የሚከፈለው ከሚከፈለው ክፍያ በተጨማሪ የሚሰማራበት ቦታ ምቹ ባለመሆኑ መሰረተ ልማት በበቂ ባልተስፋፋበት ሁኔታ ጭቃ ውስጥ የሚጓዝ፤ ችግር አጋጥሟል በሚባልበት አካባቢ በእግር እየተጓዘ የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር ጥረት ያደርጋል” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‘ሽብር’ አሁን ባለው ሁኔታ የጠቅላላ የዓለም ሁሉ ፈተና መሆኑን በመጥቀስ ለኢትዮጵያ ተለይቶ የተሰጠ አድርገን ማሰብ የለብንም ብለዋል፡፡ አክለውም “በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው መርዶና መርዶ የሚያስከትሉ ዜናዎች እንሰማለን፤ በዚህ ምክንያት የጸጥታ ተቋማትና መንግስት ይህንን ነገር ለማስቀረት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን የምታውቁት ቢሆንም እስከመቼ ላላችሁት የንጹሃንን ደም በከንቱ የሚያፈሱ የትኛውም ስብስብ ሸኔም ይሁን ሌላ ሃይል በጀመርነው መንገድ ጉዟችንን አጠናክረን የምንቀጥል ከሆነ ይጠፋሉ” በማለት ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል፡፡
“በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሸሽገው አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አመራሮችን የማጥራትና እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
የፀጥታ ችግርን በተመለከተ ባደረጉት ንግግርም “የፀጥታ ችግሮችን ለመከላከል ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ አሰቀምጠን እየሰራን ነው፤ አራት ስትራቴጂዎችን አስቀምጠን እየሰራን ነው፡፡የመጀመሪያው አስቀድሞ መከላከል ነው፤ ሁለተኛው መከታተል ነው፤ ሶስተኛው መጠበቅ ነው፤ አራተኛው ደግሞ መዘጋጀት ነው” ብለዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሸሽገው አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አመራርና ሰራተኞች በመኖራቸው በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ”ምን ይመስላል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ በምላሻቸው “ጠላቶቻችን በመዋቅር ውስጥ ሰው ይገዛሉ፤ ይሄንን ለማጥራት እየሰራን ነው፤ እስካሁንም ብዙዎችን አጽድተናል፤ ሚዲያዎችና ባንዳዎችም ግልጽ ጠላቶቻችን ሆነው አሉ፤ እነዚህንም አቅማችን በፈቀደ መጠን እንከላከላለን። በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሸሽገው አገር ለማፍረስ የሚሰሩ አመራሮችን የማጥራትና እርምጃ የመውሰድ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል” በማለት መልሰዋል።
አክለውም “እነዚህ ሃይሎች” የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የኢትዮጵያን ለውጥ ለማደናቀፍ ከአሸባሪዎችና ከባንዳዎች ጋር እየሰሩ ስለመሆኑ አንስተዋል። እነዚህ ሃይሎች ኢትዮጵያን በጋራ የማኖርና የማጽናት ስራ እየጎዱት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ህልውና እና ለህዝብ ሰላም ሲል የመከላከያ፣የደህንነት እንዲሁም የፖሊስ መዋቅሩን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በቅርቡ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት በመወሰናቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህወሃት ላይ የሽብርተኝነት ፍረጃውን ሳያነሳ ከሽብር ቡድን ጋር በሰላም አማራጩ ለመወያየት መወሰኑ ወንጀል አይሆንም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሁልጊዜም ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።
“ለሰላምም ይሁን ለጦርነት የምንወስነው በብሄራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅሟን በሰላማዊ መንገድ ማስጠበቅ ካልተቻለ የህይወት ዋጋ ከፍለን በመስዋዕትነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን፡፡ መንግስት በሰላማዊ አማራጭ ተወያይቶ መፍትሔ ለማምጣት መወሰኑ ክፋት የለውም ” ብለዋል። አክለውም መንግስት ስለሰላማዊ አማራጩ ሌሎችን የመብትም ሆነ ሂደቱን በብቸኝነት የመከታተል ሙሉ ስልጣን እንዳለው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
በተጨመሪም ምክር ቤቱ የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት የ786 ነጥብ 6 ረቂቅ በጀትን በአራት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል። በዚህም መሰረት ከ786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ውስጥ 218 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲሆን 345 ነጥብ 1 ቢሊዮኑ ለመደበኛ ወጪ፤ 209 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ ደግሞ ለክልል መንግስታት ድጋፍ እንደሚከፋፈል ተገልጿል። ለ2015 በጀት አመት ከሚመደበው የፌዴራል መንግስት በጀት 59 በመቶ ለድህነት ቅነሳ ይውላልም ነው የተባለው። እንደ ሀገር ያጋጠመውን የገንዘብ ግሽበት በተመለከተ አጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቱን መፈተሽ ይገባል ነው ያሉት። ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። የዘንድሮው በጀትም ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር በ16 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ከቀረበው የበጀት ረቂቅ ለመረዳት ተችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ደህንነትና ሰላምን ማስጠበቅ፣ መልሶ ማቋቋምና ሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ ማድረግ፣ የዋጋ ንረት ማረጋጋት፣ ሀብትን በቁጠባ መጠቀም፣ በብድር መቀነስ፣ የበጀት ጉድለት መቀነስ የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ ዜና በትናንትናው እለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አስመልክቶ ተወያይቶ የውሳኔ ሀሳብ አስተላልፏል፡፡
በኦሮሚያ፣ በጋምቤሳ፣ በደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ በአማራ፣ በአፋር እና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በንጹሐን ዜጎቻችን ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ እንዲሁም ፀጥታና ደህንነት ለማሳጠበቅ በተንቀሳቀሱ የፀጥታ አካላት ላይ ለደረሰው ሕይወት መጥፋት አስመልክቶ የኢትዮጵያፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተዋይቷል፡፡ (የትግራይ ክልል አልተጠቀሰም)
በዚህም መሰረት ፓርላማው “በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች” የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ እና በፓርላማ ከፍተኛ አመራር የሚሰየም “ልዩ ኮሚቴ” በማቋቋም ጉዳዩን መርምሮ ፓርላማው እና የኢትዮጵያ ህዝብ “በቂ መረጃ” እንዲኖራቸው ለማስቻል እንዲሁም በቀጣዮቹ እርምጃዎች ላይ ምክረ ሀሳብ ለመስጠት ጭምር ፋይዳ ያለውን ባለ ስድስት ነጥብ ውሳኔ አስተላልፈፏል፡፡
1ኛ፦ በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲደረግ፤
2ኛ፦ በአገራችን በየትኛውም ክልልና አካባቢ በሲቪል ዜጎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ያስከተሉ እና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦች በሕግ- እንዲጠየቁ እንዲደረግ፤
3ኛ፦ በየደረጃው ያለው አመራር አካል፣ የፀጥታ አካል እና የፍትህ ተቋም የሕዝቡን ደህንነትና ሠላም በጥብቅ እንዲያስከብር፤ አጥፊዎች ለሕግ ተጠያቂነት እንዲቀርቡ እንዲደረግ፤
4ኛ፦ከመንደራቸው እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በአስቸኳይ እንዲሰራ፤
5ኛ፦ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከየትኛውም ጊዜ በላይ በወንድማማችነት፣ በአብሮነት እና በአንድነት እንዲቆሙ፤
6ኛ፡ በምክር ቤቱ የበላይ አመራር የሚሰየሙ ስብጥሩ ሁሉንም ብዝሀነቶች ታሳቢ ያደረገ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን በማጣራት ምክር ቤቱ እና ለሕዝቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ለማስቻል፤ እንዲሁም ለቀጣይ እርምጃዎች የሚረዳ ምክረ-ሀሳብ እንዲቀርብ፤ ተወስኗል፡፡አስ