ዜና፦የሚድያ ሠራተኞች እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሕግአ ግባብ ውጪ ያሉበት ቦታሳይገለጽ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ኢሰመኮ ጠየቀ

ጋዜጠኛያየሰው ሽመልስ እና ጋዜጠኛ አበበ ባዩ በደህንነት ሰዎች ከታሰሩ በኋላ ፍርድ ቤት አልቀረቡም።

አዲስ አበባ ሰኔ 30፣2014 ዓም፦የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬሰኔ 30 ቀን ባወጣው መግለጫ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ የተያዙ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ እንዲገልጹና ተዓማኒ ክስ የማይቀርብ ከሆነ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ እንዲያደርጉ አሳሰበ።

ኢሰመኮ በመግለጫው ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ ክልል፣ እንዲሁም ለበርካታ ወራት በኦሮሚያ ክልል የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የሚድያ ሠራተኞችን በተመለከተ እና በተለይም በአማራ ክልል “የሕግ የበላይነትን ለማስከበር” በሚል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የታሰሩ ሰዎችን አስመልክቶ የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ለተራዘመ የቅድመ ክስ እስር ከመዳረግ፣ ጋዜጠኞችን በሥራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር፣ ኢመደበኛ በሆኑ ማቆያዎች ከማሰር ሊታቀቡ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ማሳሰቡን ያወሳ ሰሆን በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ ክልል ጋዜጠኞች ምስግና ስዩም፣ ተሾመ ጠማለው፣ ኃይለሚካኤል ገሰሰ እና ሃበን ሐለፎምን ጨምሮ 15 የሚዲያ ሠራተኞች ከተገባደደው የግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ተይዘው እንደሚገኙ ተናግሯል።

በማናቸውም ጊዜ ቢሆን የተያዙና በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝ የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ ሊሆን እንደሚገባ እና በክልልም ሆነ በፌዴራል የፀጥታ አካላት የተያዙ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ የማሳወቅ፣ የሕግ አማካሪ እና የቤተሰብ ጥየቃን መብት የማክበር እንዲሁም በአፋጣኝ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብቶችን ሊያከብሩ ይገባል

ኢሰመኮ

ኮሚሽኑ አያይዞም   የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 (ሚዲያ አዋጅ) ዋቢ አድርጎ በመጥቀስ በአዋጁ መሰረት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑን ከዚህ በፊት ሲያስታውስ መቆየቱን አንስቶ በሚድያ ሠራተኞች ላይ የተጀመሩ የሕግ ሂደቶች በዚሁ መሰረት እንዲተገበሩ ጥሪ ማቅረቡንም ጨምሮ ገልጿል።

“በማናቸውም ጊዜ ቢሆን የተያዙና በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝ የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ ሊሆን እንደሚገባ እና በክልልም ሆነ በፌዴራል የፀጥታ አካላት የተያዙ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ የማሳወቅ፣ የሕግ አማካሪ እና የቤተሰብ ጥየቃን መብት የማክበር እንዲሁም በአፋጣኝ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብቶችን ሊያከብሩ ይገባል” ሲል ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫ አሳስቧል። 

በአዲስ አበባ ከተማ ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተይዘው የቆዩ የሚድያ ሠራተኞች መካከል በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው ተከብሮ የተለቀቁ መሆኑን ኮሚሽኑ እንደተመለከተም ተናግሯል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው አያይዞም በአማራ ክልል ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይም የሚገኙበት ቦታ ሳይገለጽ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ በአብዛኛው ኢመደበኛ በሆኑ እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው በራቀ ቦታ ለብዙ ሳምንታት ተይዘው የቆዩ በርካታ ሰዎች በባሕር ዳር ወደሚገኙ ማቆያ ቦታዎች መዛወራቸውን፣ እንዲሁም በእነዚሁ ቦታዎች ከቆዩ ሰዎች መካከል ይገኙ የነበሩ የሚድያ ሠራተኞች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ሲገመግም መቆየቱን አክሎ ገልጿል።

ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የአሻራ ሚድያ እና የንስር ሚድያ ሠራተኞች በዋስ እንዲለቀቁ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መወሰኑን ኢሰመኮ አውስቶ፣ የሚድያ ሠራተኞችን የፍርድ ቤት ሂደት መከታተል ጨምሮ ሁሉንም በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ጉዳይ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ተናግሯል። 

ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው የተወሰኑ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተጠበቀላቸውን ተጠርጣሪዎች “በዋስትና ውሳኔው ላይ ይግባኝ ተጠይቋል ወይም ለሌላ የወንጀል ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ አስፈልጓል” በሚል ምክንያት  የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን በመጣስና ታሳሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማቆየት ሕገወጥ እስር እየተፈጸመ መሆኑን አስምሮበታል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት፣ እንዲሁም ጋዜጠኛ አበበ ባዩ ከሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት የሲቪል ልብስ በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ከተወሰዱ በኋላ ያሉበት ቦታ ያለመገለጹን ኮሚሽኑ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስበው መሆኑን በመግለጫው ያነሳ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚድያ ጽሑፎቹ የሚታወቀው በላይ በቀለ ከሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተመሳሳይ መልኩ የሲቪል ልብስ በለበሱ የፀጥታ አካላት ከተወሰደ በኋላ ያለበት ቦታ ሳይገለጽ ተይዞ ከቆየ በኋላ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. መለቀቁን አያይዞ ገልጿል። እንዲሁም የሚድያ ሠራተኛ  ወግደረስ ጤናው በባሕር ዳር ከሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተይዞ የሚገኝ መሆኑን እና ፍርድ ቤት መቅረቡ እንደታወቀም አክሎ ኮሚሽኑ ተናግራል።

እነዚህን እስሮች በተመለከተ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “የዘፈቀደ፣ ሕገ ወጥ እና በተለይም ተጠርጣሪዎች የሚገኙበትን ቦታ ሳያሳውቁ የሚደረጉ እስሮች ሰዎችን ለከፍተኛ ስጋት፣ ቤተሰቦችን ለጭንቀት ዳርጓል። በመንግሥት የፀጥታ አካላት እውቅናና ሆነ ተብሎ ሰዎችን ከሕግ እይታ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሊሆን የሚችል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ነው፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በዋስ እንዲፈቱ መብታቸው የተጠበቀላቸውን ተጠርጣሪዎች ከሕግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር ማቆየት የሕግ የበላይነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚሸረሽር ነው” ብለዋል።

ስለሆነም ኮሚሽኑ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ አካላት በአፋጣኝ የተያዙ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ እንዲገልጹና ተዓማኒ ክስ የማይቀርብ ከሆነ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ አሳስቧል።

አዲስ ስታንዳርድ በተከታታይ ባወጣችው እትሟ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ባህር ዳር አንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የታሰሩ እነደነበሩ መግለጿ የሚታወስ ሲሆን ከታሰሩት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ ሂደታቸውን የሚከታተሉ እንደነበሩ እና እንዳሉ፣ የዋስ መብት ተፈቅዶላቸው ከህግ አግባብ ውጪ የተከለከሉ እንደነበሩም ስትዘግብ ቆይታለች። በተጨማሪም የጸጥታ ሃይሎች ‘ለጥያቄ ትፈለጋለህ/ ትፈለጊያለሽ’ በሚል በተለያዩ ጊዚያት መሰል ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች ‘ወደማይታወቅ’ ቦታ ወስደው ሲያስሩ እንደቆዩም አዲስ ስታንዳርድ ስትዘግብ እንደነበር ይታወሳል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.