አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2 ቀን/ 2014 ዓ.ም፦ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ለጋዜጠኛ መአዛ መሃመድ እና ለጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ በስር ፍርድ ቤት የተፈቀደላቸውን የ10 ሺህ ብር የዋስ መብት ሻረ።
የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን ዋስትና የሰጣቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ፣ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ እንዲሁም ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ ላይ መርማሪ ፖሊስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዋስትና በተሰጠበት እለት ከስአት ይግባኝ አስገብቶ ዳኞች ስላልነበሩ በይደር ለእሮብ ሰኔ 1 ቀን ተይዞ ነበር ።
እሮብ ሰኔ 1 ቀን፣ ጠዋት መርማሪ ፖሊስ እና ተጠርጣሪዎቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ችሎት የተገኙ ሲሆን ፖሊስ ምርመራዬን ሳልጨርስ ዋስትና መሰጠቱ አግባብ አይደለም፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ከወጡ የጀመርኩትን የምርመራ ሂደት ያበላሹብኛል እንዲሁም በህዝብ ላይ የደረሰ ከፍተኛ ጉደት እንዳለ ለፍርድ ቤት አስረድቶ የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ትእዛዝ ተሽሮ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የስር ፍርድ ቤት ትእዛዙን የሰጠው የምርመራ መዝገብን ከተመለከተ በኋላ እንደሆነ አንስተው ተከራክረዋል።ፖሊስ ይቀሩኛል የሚላቸው ስራዎች ተቋም ለተቋም የሚደረግ የደብዳቤ ስራ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናግረው ደንበኞቻቸው ከእስር ቢወጡ ምንም የሚያበላሹት ነገር እንደሌለ እና “በህዝብ ላይ ትልቅ ጉዳት” ደርሷል ሲል ፖሊስ ያነሳው ጉዳይ ነገሩን ለማክበድ እንጂ ምንም የደረሰ ጉዳት አለመሆሩን ጠቅሰው ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤትን ትእዛዝ እንዲያፀና ሲሉ ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የሁለቱን ክርክር መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት በይደር ለዛሬ አሳድሮታል።
በዛሬው ችሎት የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሰጠውን ትእዛዝ በመሻር ለመርማሪ ፖሊስ ከግንቦት 30 ቀን ጀምሮ ታሳቢ የሚሆን ተጨማሪ 8 ይምርመራ ቀናት ሰጥቶ ጉዳዩ በስር ፍርድ ቤት እንዲታይ ትእዛዝ ሰጥቷል።
በተያያዘ “የአልፋ” ዩትዩብ ባለቤትና መስራች ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ዛሬ ጠዋት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ከመርማሪ ፖሊስ ጋር ክርክር አድርጓል።
መርማሪ ፖሊስ ባለፈው በተሰጠው የምርምራ ቀን “ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት” ከአገር ውጪ የሚኖሩ አካላት የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለት እንደነበር መረጃ ሰብስበናል ያለ ሲሆን የሚቀሩ ስራዎች ከተጠርጣሪው እጅ ከተያዙ ኣሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ለምርመራ ልኮ መልስ እየጠበቀ መሆኑን፣ የተጠርጣሪውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ለማወቅ ለተለያዩ ባንኮች ደብዳቤ ልኮ መልስ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሶ ግብረ አበሮቹን ለመያዝ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቃ በበኩሉ ደንበኛቸው ሊጠየቅ የሚገባው በመገናኛ ብዙሀን አዋጅ እንደሆነ ለችሎት እስረድተው በደንበኛቸው ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች ከመንግስት ተቋም የሚመጡ ደብዳቤዎች ስለሆኑ ተጠርጣሪው መረጃ ለያጠፋበት ወይም ሲሰውርበት የሚችልበት ሁኔታ ስለሌለ ስዋስትና እንዲፈቀድላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል።
የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎት ጋዜጠኛ በቃሉ የተጠረጠረበት ወንጀል መታየት ያለበት በብሮድካስት ህግ ወይም በጊዜ ቀጠሮ የሚለውን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።አስ