በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
ሐምሌ 15፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡- አል ዐይን ኒውስ የተባለ ዲጂታል ሚዲያ የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ የሆነው ጋዜጠኛ አልዓዛር ተረፈ ትናንት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ፖሊስ የምርመራ ስራዎችን በሰባት ቀን ውስጥ አጠናቆ ለሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃው አቶ መሰረት የኔሁን ለአዲስ ስታንዳርደ ገለፁ፡፡
ጋዜጠኛው ሀምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም የየካ ክ/ከተማ የላምበረትና አካባቢ ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በግል የፌስቡክ ገፁ ላይ “ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ ጽሁፍ ለቋል፣ ዜጎች እየሞቱ ችግኝ ይተከላል የሚል የቅስቀሳ ይዘት ያለው መልእክት አስተላልፏል ይህም በህዝብና መንግስት መሃል መቃቃር ለመፍጠር ታስቦ የተደረገ ነው” በሚል ተጠርጥሮ መያዙን ጠበቃው አቶ መሰረት የኔሁን ገልፀዋል፡፡
አልአዛር በፖሊስ በተያዘ ማግስት ዓርብ ሐምሌ 8 በአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ5 ሺ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ ተወስኖለት ነበር፡፡ መርማሪ ፖሊስ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ይግባኝ የተባለበት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም በማለት ውድቅ ያደረገ ቢሆንም ጉዳዩን ወደ ያዙት የላምበረት አካባቢ ፖሊስ ቢያቀኑም ሊፈቱት አለመቻላቸውን ጠበቃው ለአዲስ ስታንዳርድ አክለው አስረድተዋል፡፡
ጋዜጠኛው ሰኞ ሐምሌ 11 ቀን የፌዴራል የመጀምሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረበ ሲሆን “በሚሰራበት አል ዐይን ሚዲያ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት በሚዲያው በመዘገብ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ቅስቀሳ አድርጓል” በሚል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን በመያዝ ጠርጠሬዋለው ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
ፖሊስ በጋዜጠኛ አልዓዛር ላይ የጀመረውን የምርመራ መዝገብ ባለማቅረቡ ምክንያት በዋስትናው ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠት አለመቻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጾ ነበር፡፡ በመሆኑም መዝገቡን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀጠሮ ይዞ የነበረው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ፖሊስ የሚዲውን ህጋዊነት የሚያረጋግጥና ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብና ሌሎች የምርመራ ስራዎችን በሰባት ቀን ውስጥ አጠናቆ ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብ አዟል፡፡ አስ