ዜና፡ ግሎባል ጥምረት ለጣና ሀይቅ መልሶ ማቋቋም ድርጅት በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን እንቦጭ ለማስወገድ የሚረዳ ማሽን ወደ ኢትዮጵያ ላከ

ምስል ከዚህ በፊት በድርጅቱ የተበረከተ ማሽን ከአዲስ ስታንዳርድ ክምችት 

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

ሃምሌ 13፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦ በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን እንቦጭ ለማስወገድ የሚረዳ የእንቦጭ ማጨጃ ማሽን የመገጣጠም ሂደቱ ተጠናቆ በቂ ፍተሻ ከተደረገለት በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ መላኩን በአሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን የውሃ ባለሙያዎች የተቋቋመው ግሎባል ጥምረት ለጣና ሃይቅ መልሶ ማቋቋም ድርጅት ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው መግለጫ አስታወቀ። ማሽኑ ለአማራ ክልል መንግስት የጣናና ሌሎች ውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ በነጻ የተበረከተ ነው።

ድርጅቱ ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው መግለጫ ማሽኑ ኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ በተከሰተው የፋብሪካዎች መዘጋት ምክንያት መጓተቱን ገልፆ በኢትዮጵያ መርከቦች ድርጅት ትብብር መሰረት በመርከብ ተጭኖ ወደ ጂቡቲ ወደብ ጉዞ የጀመረ ሲሆን በአምስት ሳምንት ውስጥ ኢትዮጵያ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።

ይህ ማሽን ሶስተኛ ማሽን ሲሆን ከዚህ ቀደም ሁለት የእንቦጭ ማጨጃ ማሽኖ ለክልሉ መለገሱ ይታወሳል።

በአጠቃላይ ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ($172,970 ዶላር) ወጭ የተደረገበት ይህ ባለ 80 የፈረስ ጉልበት እንቦጭ ማጨጃ ማሽን በአንዴ 27.5 ኪዩቢክ ሜትር መያዝ የሚችል ሲሆን በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን እንቦጭ ለማስወገድ በሚደረገው ርብርብ ላቅ ያለ ግልጋሎት እንደሚኖረው ይታመናል ተብሏል።

ማሽኑ ወጭው የተሸፈነው ከዚህ ቀደም በዋሽንግተን ዲሲ፤ በዳላስ፤ በችካጎና በእንግሊዝ ሃገር በተደረጉ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ ገንዘባቸውን በለገሱ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን መሆኑን የገለፀው ድርጅቱ ከተመረተበት ካናዳ በመርከብ እስከተጫነበት ወደብ (ባልቲሞር ወደብ) ድረስ ለማጓጓዝና ለወደብ ክፍያ ወጭ በመክፈል ያገዙትን አካላት አመስግኗል።

የኢትዮጵያ መርከቦች ድርጅት ማሽኑን ከአሜሪካ እስከ ጂቡቲ ጭኖ ያለክፍያ በነጻ የጓጓዘ ሲሆን የአማራ ክልላዊ መንግስት ከጂቡቲ እስከ ባህርዳር ያለውን የየብስ ትራንስፖርት እንደሚሽፍን ቃል መግባቱን መግለጫው ያስረዳል።

በሁሉም ሂደት ውስጥ አስተዋፆ ላደረጉና የክልሉ የጣና ሃይቅ ልማት ኤጀንሲ የትብብር ደብዳቤዎችን በመጻፍና ማሽኑ ከጉምሩክ ቀረጥ-ነጻ እንዲገባ የሚያስፈልጉ ዶክሜንቶችን በማዘጋጀትና በማስፈጸም እገዛ በማድረጉ ምስጋናውን አቅርቧል።

ግሎባል ቅንጅት ለጣና ሀይቅ መልሶ ማቋቋም ድርጅት በኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ማህበረሰብ የተመሰረተ አትራፊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን “በጣና ሀይቅ ዙሪያ የአካባቢ እና የውሃ አያያዝ ስራዎችን“ ለመደገፍ የተቃቋቋመ ድርጅት ነው። 

አዲስ ስታንዳርድ ይህ በጎ አድራጊ ተራድዖ ድርጅት በዋሽንግተን ዲሲ “ጤና ለጣና 2018 [GC]” መጋቢት 7 ቀን 2010 ዓ.ም በሚል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር  ለእንቦጭ አረም ማጨጃ ማሽን መግዣ  መሰብሰቡን መዘገቧ ይታወሳል።  

በእለቱም በተከናወነው ፕሮግራም አንጋፋውን ሙዚቀኛ ማህሙድ አህመድን ጨምሮ ከ1,500 በላይ የተሳተፉ ሲሆን በዲሲ የሚገኘው የመድሃኒአለም ቤተ ክርስቲያን ለተባለው ማሽን 70 ሺህ ዶላር ለመለገስ ቃል መግባቱም ተዘግቦ ነበር። 

የኤጀንሲው ሊቀ መንበር ዶክተር ሰለሞን ክብረት በወቅቱ ለአዲስ ስታንዳርድ በላኩት መልዕክት “ኢትዮጵያውያን አብረው ሲሆኑ ታላቅ ነገሮችን መስራት ይችላሉ” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን አክለውም፣“የጣና ሀይቅ በከፍተኛ አደጋ ላይ ሲሆን በሃይቁ ዙሪያ የሚኖሩ ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በእምቦጭ አረም በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዱ ነው” ብለውም ነበር። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.