ዜና፡ ድንበር ጥሰው ወደ ክልሉ የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሁለት ሰዎችን ገድለው አንድ ሰው ማቁሰላቸው ተገለፀ

የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት

አዲስ አበባ፣ የካቲት፣2/ 2015 ዓ.ም፡- ከደቡብ ሱዳን በመነሳት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ ክልል የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሁለት ሰዎችን ገድለው አንድ ሰው ማቁሰላቸውን የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት እንዳሉት ታጣቂዎቹ ድንበር ጥሰው በመግባት ጥር 30 ማምሻውን በጎግ ወረዳ በአተቲ ቀበሌ ኡቱዮ መንደር ሁለት ሰዎችን ገድለው አንድ ሰው ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርሱ የአካባቢው ማህበረሰብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመሆን ተገቢውን ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝ አክለው ገልፀዋል፡፡ ኡቶው “ክልሉ በአሁኑ ሰዓት ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻ በመጠቀም ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ስራውን እየሰራ ሲሆን ጥቃት አድራሾች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

ድንበሩ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይም በአኙዋና በኑዌር ዞኖች ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ህብረተሰቡ በንቃት አካባቢውን እንዲጠብቅ አቶ ኡቶው አሳስበዋል።

የሙርሌ ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊትም በተለይም በበጋው ወራት በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው በመግባት የሰው ሕይወት ሲያጠፉ፣ ሕፃናትን አፍነው  ሲወስዱና ንብረት ሲዘርፉ እንደነበር ይታወቃል።

ባሳለፍነው አመት ጥር ወር አጋማሽ ላይ ከደቡብ ሱዳን በመጡ የሙርሌ ታጣቂዎች በክልሉ ኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ ባካንካን ቀበሌ ላይ በከፈቱት ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲሞቱ አምስት ሰዎች ቆስለዋል።

ታጣቂዎቹ ድንበር ጥሰው በጋምቤላ ክልል ዲማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ እና ጎግ ወረዳ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ያለፈ ሲሆን ሌሎች ሁለት ሰዎች ቆስለዋል። በየካቲት ወር ሁለተኛ ሳምንት በተደረገው የድንበር ጥቃት ሶስት ህጻናትም በታጣቂ ቡድኑ ታፍነዋል።

በተመሳሳይ መጋቢት 2014 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት ከ9 ሺህ በላይ የላሬ እና የጂካኦ ወረዳ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግባለች፡፡

በዚያኑ ወር በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መዩኪ እዩ ዴንግ ጋር የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም አምባሳደር ነቢል በኢትዮጵያ ድንበር ላይ የሙርሌ ታጣቂዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሱ ያለውን ተደጋጋሚ ጥቃት እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ “የሙርሌ ጥቃቶች ለዓመታት አሉ እና የችግሩ ተፈጥሮ በመንግስት የተደገፉ ጥቃቶች መሆናቸውን ወይም አለመሆኑን በጥልቀት መመርመር አለበት። ሁለቱ ሀገራት በሰላም አብሮ የመኖርን አስፈላጊነት ዙሪያ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ማስተማር እና ግንዛቤ መፍጠር አለባቸው” ብለዋል። አምባሳደሩ ይህን ያሉት የሙርሌ ታጣቂዎች ከጋምቤላ ክልል 18 ኢትዮጵያውያንን መግደላቸውን፣ ስምንት ህጻናትን አፍነው ከ100 በላይ የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን ተከትሎ ነው።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.