አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23/2014 ዓ.ም፡- የደሴ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ የከተማዋ ሰላምና ደህንነት ላይ ከመከረ በኋላ የተለያዩ ክልከላዎች እና ገደቦችን አስቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የወልድያ ከተማ አስተዳደርም የከተማዋን አካባቢ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ከነሐሴ 22፣ 2014 ዓ.ም ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ አስቀምጧል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ከነሀሴ 22/2014 ዓ.ም ጀምሮ የትኛውም የከተማዋ ነዋሪ ከምሽቱ 2:00 /ሁለት/ ሰዓት ጀምሮ በተናጠልም ሆነ በጋራ መንቀሳቀስ እንደመይቻል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በከተማ ደረጃ እውቅና ያላቸው የታክሲ አሽከርካሪዎች እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ብቻ ህዝቡን እንዲያገለግሉ ተወስኗል፡፡ ነገር ግን በሁሉም የከተማችን አካባቢዎች የሚገኙ የሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) እስከ ምሽቱ 1:00 ሰዓት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን በከተማ ደረጃ የስምሪት ፍቃድ የሌለው ባጃጅ መንቀሳቀስም ሆነ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ( የፀጥታ መኪኖችና አምቡላንሶች ) የሚሰጡት አገልግሎት በሰዓት እላፊ ሳይገደቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም ወደ ደሴ ከተማ በማንኛውም ምክንያት የገቡ እንግዶች ከምሽቱ 1:00 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንዲሁም የምግብ ቤቶች፣ የምሽት መጠጥ ቤቶች/ግሮሰሪዎች/ ከምሽቱ 1፡ዐዐ ሰዓት ጀምሮ በማንኛውም ምክንያት አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ከተፈቀደላቸው የከተማችን የፀጥታ ሃይሎች ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑም ምክር ቤቱ አክሎ አስታውቋል፡፡
በመፈናቀልም ሆነ በሌላ ማንኛውም ምክንያት ወደ ደሴ ከተማ የገቡ ተፈናቃዮች የከተማውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል የፀጥታ ሀይሉ ለጋራ ደህንነት ለሚተገብራቸው የፍተሻና የቅድመ-ጥንቃቄ ስራወች ተባባሪ የመሆን ግዴታ አለበት ተብሏል፡፡ በተጨማሪም አልጋ ቤት፣ የመኖሪያ ቤት ወይም መደብ ቤት አከራዮች የየትኛውንም ተከራይ ማንነትን የሚገልፅ መረጃ ለፀጥታ ተቋማት የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ የ”ጠላትን” ሀሳብና እንቅስቃሴ በመደገፍ አሉባልታና ወሬ በማናፈስ በህብረተሰቡ መካከል ሽብር የሚነዛ በህግ እንዲጠየቅ ተወስኗል ነው የተባለው፡፡
“በከተማው ውስጥ የሚስተዋሉ ፀጉረ- ልውጦችን እና ሰርጎ ገብን በመከታተል በፍጥነት ለፀጥታ ሃይሉ በመጠቆም እና በማስያዝ ማህበረሰባችን የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተወስኗል፡፡ ማህበረሰቡ ወይም የከተማችን ነዋሪወችን ለተጨማሪ ችግር ለመዳረግ በማንኛውም ምርት ላይ የዋጋ ጭማሬ የሚያደርጉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ያለው ምክር ቤቱ መላ የከተማችን ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች አካባቢያችሁን ከመጠበቅ አንፃር ሌላ አደረጃጀት ሳያስፈልግ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመሆን የምያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ እና ከፀጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት ሀላፊነታቸውን እንድትወጡ” ሲል አሳስቧል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤቱ የከተማዋን የፀጥታ ሃይሎች ከምንጊዜውም በላይ በመቀናጀትና በመደራጀት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት እንዲወጡ አሳስቦ በተጣለው የሰአት ገደብ መሠረት ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ተላልፎ የተገኘ አካል ላይ እርምጃ ይወሰዳል ሲል አስጠንቅቋል።በተመሳሳይ መልኩ የወልድያ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን አካባቢ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ከነሐሴ 22፣ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን ከተመደበው የጸጥታ ኃይል በስተቀር ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ እንዲሁም ለጸጥታ ስራ ስምሪት ከተሰጠው ተሽከርካሪ ውጭ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ መንቀሳቀስ የማይችል መሆኑን አስታውቋል። አስ