አዲስ አበባ፡ ሰኔ 22/ 2014 ዓ.ም፡-የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኦንላይን መስጠት እስከሚጀመር ድረስ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጥ መሆንን እና ጥራት ያለው ተማሪ የማያፈሩ እንዲሁም የአካባቢውን ማኅበረሰብ የማይጠቅሙ ዩኒቨርስቲዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ የትምህርተ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ የተወሰነው የፈተና ሰርቆትና ማጭበርበርን ለማስቀረት ታስቦ በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርት በስራና በታታሪነት የሚገኝ መሆኑን አውቀው በርትተው መማርና ማጥናት እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በሆሳዕና ፣ በወራቤና በወልቂጤ ከተሞች የሚገኙ ሁለተኛ ደረጃና ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ዘሬ ሰኔ 22ቀን በጎበኙበት ወቅት ሲሆን በጉብኝታቸው ወቅትም የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትን ጥራትን ለማሻሻል በአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፎች ሌሎችንም የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም ጥራት ያለው ተማሪ ማፍራት የማይችሉ፣ ደረጃውን የጠበቀ ምርምር የማያካሂዱና የአካባቢውን ማኅበረሰብ የማይጠቅሙ ዩኒቨርስቲዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዋቸሞ ፣ ወራቤና ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተመራማሪዎችና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ጋር ትናንት ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረጉት ውይይት ጠቁመዋል።
ዪኒቨርስቲዎች ዓለም አቀፍ ውድድሩን ለመሸከም የሚያስችል ዕውቀት የሚፈራባቸው ቦታዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ሁኔታ ዩኒቨርስቲዎች ጥሩ ዕውቀት ያላቸው ተማሪዎች ማፍራት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ዜጎች እንኳን ማፍራት አልቻሉም ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸዉ የውይይቱ ዓላማ በትምህርት ዘርፉ ያሉ ችግሮችን ምንነት በመለየት ችግሮችን ለመፍታት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ መሆኑን ገልጸዋል።አስ