አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18/2015 ዓ.ም፡- በሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች መካከል ተደርሷል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት በከፊል ተከብሯል፣ ወይም በከፊል ተጥሷል የሚሉ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎች ተበራክተዋል።
በጦርነቱ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎቿ ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል። የአለም ጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው አምስት መቶ እየተጠጋ ይገኛል። ባለፉት ቀናት ደግሞ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ መኖሪያቸውን ለቀው ለስደት እየተዳረጉ ሱዳናውያን ቁጥር እጅጉን እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። በካርቱም እና በሌሎች ሱዳን ከተሞች ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ከአሳሳቢነት በላይ መሆኑን የሚወጡ መረጃዎች እያመላከቱ ይገኛል።
የሱዳኑ ግጭት ዳፋ በሀገሪቱ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ደርሷል። የቢቢሲ የአማርኛ ድረገጽ እንዳስነበበው ቢያንስ ስምንት ኢትዮጵያውያን እንደተገደሉ በካርቱም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መስማቱን ገልጿል። ከሟቾች በተጨማሪ አራት ኢትዮጵያውያን ጉዳት እንደደረሰባቸው በኤምባሲው የዲያስፖራ ክፍል የዜጎች ጉዳይ ክትትል ባልደረባ የሆኑት ነጂብ አብደላ ለቢቢሲ መናገራቸውን አካቷል። ኢትዮጵያውያኑ ሞት እና ጉዳት የደረሰባቸው በተባራሪ ጥይት ወይም በፍንዳታ ምክንያት በሚፈጠር ፍንጣሪዎች መሆኑን መናገራቸውንም ዘገባው አስታውቋል።
በሱዳን ካርቱም ብቻ 24ሺ የሚሆኑ በእርግዝና ላይ ያሉ ልጆቻቸውን በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት በሰላም ለመገላገል በህክምና ተቋማት ሲከታተሉ የነበሩ እናቶች መኖራቸው ደግሞ የቀውሱ አሳሳቢነት ማሳያ ሁኗል ሲል ቢቢሲ በዘገባው ጠቁሟል።
የተባበሩት መንግስታት የስረደተኞች ጉዳይ በጀኔቫ የሱዳንን ቀውስ አስመልክቶ ያሰራጨው ዘገባ እንደሚያመላክተው ድርጅቱ የስደተኞች ማዕበል ሊፈጠር ይችላል በሚል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። 270ሺ ሱዳናውያን ለስደት ሊዳረጉ ይችላሉ ሲል መላምቱን አስቀምጧል። በሱዳን ተጠልለው የሚገኙ ከአንድ ሚሊየን በላይ ስደተኞች መኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን ከሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን በላይ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሏትም የተመድ መረጃ ያመላክታል። ወደ ደቡብ ሱዳን የተሰደዱ እና ቁጥራቸው አስር ሺ እንደሚደርስ የተገለጸ ሲሆን ወደ ግብጽ የተሰደዱ ሱዳናውያን ቢኖሩም ምን ያክል ናቸው የሚለው አልተገለጸም። በቀጣይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን አጎራባች ሀገራት በተለይም ኤርትራ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ሊቢያ የሱዳን ስደተኞችን ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ መላምቱን አስቀምጧል።
ሁለቱም ተቀናቃኝ ሀይሎች ወደ ዋና ድርድር ለመቀመጥ ምንም አይነት ዝግጁነት እንደማይታይባቸው በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መልዕክተኛ ቮልከር ፐርዘስ ትላንት ለተካሄደው እና በሱዳን ላይ በመከረው የፀጥታው ምክርቤት የምክክር መድረክ ላይ ባቀረቡት ንግግር አስታውቀዋል። ሁለቱም ሀይሎች ማሸነፍ ይቻላል የሚል ግምት ወስደው እየተዋጉ እንደሚገኙ አብራርተዋል፤ ይህም ሁለቱም የሚተገብሩት የተሳሳተ ቀመር ነው ብለዋል።
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዩ ጉተሬዝ በሱዳን ያለው ቀውስ ልብ ሰባሪ ነው ሲሉ ገልጸው ቀውሱ ወደ ቀጠናው ሀገራት ሊዛመት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ሱዳን በሰባት ሀገራት ተዋሰናለች፤ እነዚህም ሀገራት ግጭት ላይ አልያም እርስ በርስ ጦርነትን ባለፈው አስር አመት ያስተናገዱ ናቸው፤ በሱዳን ያለው ቀውስ በዚያው ላያበቃ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።
የቀድሞ የሱዳን ፕሬዝዳን አልበሺር ታስረውበታል ተብሎ የሚታመንበት እስር ቤት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን በርካታ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። አልበሺር ጥቃቱን ተከትሎ እንዲያመልጡ ተደርገዋል ሲሉ መረጃ ያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉ ሁሉ ጥቃቱ ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሲባል ተዛውረዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። አልበሺር የተወሰዱት ወደ ወታደራዊ ሆስፒታል ነው ሲልም ጠቁሟል።
(መረጃዎቹ ከቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ሮይተርስ፣ ዲደብልዩ እና ጋርድያን የተጠናቀሩ ናቸው)