ዜና፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተወካዮች ዛንዚባር ውስጥ ድርድር መጀመራቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በታንዛኒያ ዛንዚባር የሚያደርጉት ንግግር መጀመሩን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ማሳወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ቃል አቀባዩ ኑር መሐመድ ሼክ ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኹለቱ ወገኖች ንግግር ወደ ፖለቲካዊ ስምምነት ያመራል ብለው እንደሚጠብቁ መናገራቸው በዘገባው ተካቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጋር በታንዛኒያ ድርድር እንደሚጀመር መግለፃቸውን ተከትሎ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ መንግስት ሶስተኛ አካል ባለበት ድርድር ለማድርግ የቀረቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በመቀበሉ ድርድሩ እንደሚጀመር ማረጋገጡ ይታወቃል፡፡

በዚህም መሰረት በተጀመረው ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክሎ የሚደራደረውን ቡድን የሚመሩት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን መኾናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቻለሁ ሲል የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

በአሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን እና የጦሩ አዛዥ አማካሪ የሆኑት ጂሬኛ ጉደታ እና አብዲ ጣሃ የተባሉ ግለሰብ እንደገኙበት ቢቢሲ ዘግቧል። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ስለተደራዳሪዎቹም ሆነ ንግግሩ ስለ መጀመሩ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

አዲስ ስታንዳርድ ከታማኝ ምንጮች እንደተረዳው በውይይቱ ላይ የኖርዌይ፣ የኬንያ እና የኢጋድ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው። የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ኑር መሀሙድ ሼክ ትላንት ለአዲስ ስታንዳርድ፤ ንግግሩን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልፀው ነበር፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.