ዜና፡ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት በሀገር ደረጃ በዘመቻ መሰጠት መጀመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10/2015 ዓ.ም፡- ሀገራዊ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በበናፀማይ ወረዳ ብራይሌ ከተማ በይፋ መጀመሩን የጤና ሚኒስትር አስታወቀ። ዘመቻውን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ፌስቡክ ገጹ ይፋ ያደረገው መረጃ አመላክቷል። ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ዘመቻውን ሲያስጀምሩ ባስተላለፉት መልእክት ባለፉት አመታት መከላከልን መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸዉን አስታውቀው በተለይም የእናቶችና ህፃናትን ጤና ከማሻሻል፣ ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከልና መቆጣጠር ረገድ አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም ዛሬም ድረስ ኮሌራን ጨምሮ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዘመቻው መክፈቻ ስነስረአት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸዉ በዘመቻው እንደ ሀገር እድሜያቸዉ ከአንድ አመት በላይ የሆናቸዉ 1.9 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ክትባቱ ተደራሽ እንደሚደረግ ጠቁመው ለዘመቻዉ መሳካት የጤና ባለሙያዎች በየደረጃዉ ያለዉ አመራርና ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊዉን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተያያዘ ዜና የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አራት ክልሎች መዛመቱን እና በደቡብ ክልል ልዩ ልዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ደግሞ፣ 18 ሰዎችን ለኅልፈት መዳረጋቸውንና 919 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን፣ የክልሉ ጤና ቢሮ ዋቢ በማድረግ ቪኦኤ በዘገባው አስታውቋል።

በክልሉ ለተከታታይ አምስት ቀናት ይሰጣል የተባለውን የኮሌራ ክትባት ዘመቻ፣ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ኦሞ ዞን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ወረርሽኙ በአገር አቀፍ ደረጃ በአራት ክልሎች መከሠቱን እና እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለኾኑ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ዜጎች የኮሌራ ክትባት እንደሚሰጥ ሚኒስትር ዴኤታው ማስታወቃቸውን ዘገባው አስታውቋል።

ከሳምንት በፊት በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በሁለት ቀናት ውስጥ የአራት ሰዎች ህይወት በኮሌራ በሽታ ምክንያት ማለፉን የልዩ ወረዳው ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

በተመሳሳይ ከወራት በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ በኮሌራ ወረርሽኝ ሳቢያ 28 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን እና አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ደግሞ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠዋል ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል። ወረርሽኙ የተከሰተው በኦሮምያ ክልል በባሌ፣ ጉጂ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በሚገኙ 8 ወረዳዎች እና 66 ቀበሌዎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን ሁለት ወረዳዎች መሆኑን የተመድ ሪፖርት ማመላከቱን አካተናል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.