አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10/2015 ዓ.ም፡- በበጀት እጥረት ሳብያ የፌደራል እና የክልል የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ በወቅቱ እንደማይከፈላቸው፣ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጭራሽኑ እየተከፈላቸው አለመሆኑን አየገለፁ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ለክልል መንግስታት የደመወዝ ክፍያ ጫና እጅጉን በመበርታቱ ይህንን የሚቃወም ሰልፍ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ከአንድ ወር በፊት አዲስ ስታንዳርድ የሀዲያ ዞን ምስራቅ ባዴዋቾ ወረዳ ሾኔ ከተማ የመንግስት ሰራተኞች የሶስት ወራት ደመወዝ እናዳልተከፈላቸው በመግለጽ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን እና ሰልፉን ለመበተን ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ሶስት ሰዎች ላይ ጥቃት ደርሶ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የወረዳው ነዋሪ ዋቢ በማድረግ መዘገቡ ይታወሳል።
ዋዜማ ሬድዮ ይዞት የወጣው ዘገባ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ደሞዛቸው እስከሶስት ሳምንት ዘግይቶ የተከፈላቸው የክልሉ ተቋማት መኖራቸውን የዞን ሀላፊነት ላይ ያሉ ሰራተኞችን ዋቢ አድርጎ አስታውቋል።
በክልሎች የታየው ምልክት አሁን ደግሞ በፌደራል ተቋማት ብቅ ማለት ጀምሯል። ዋዜማ ሬድዮ ጅማ ዩኒቨርሲቲም በቅርቡ ደሞዝ በአንድ ሳምንት አዘግይቶ መክፈሉን ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። በምክንያትነት የቀረበው ደግሞ የበጀት እጥረት የሚል መሆኑን አመላክቷል።
አዲስ ስታንዳርድ የፌደራል መስሪያ ቤት ከሆኑት መካከል በጳውሎስ ሆስፒታል ሰራተኞች ያገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ደመወዝ የተከፈላቸው ከአስር ቀናት በኋላ ነው። በጳውሎስ ሆስፒታል ከአስር አመት በላይ በነርስነት ያገለገለች የተቋሙ ሰራተኛ የቤት ኪራይ በወቅቱ መክፈል ባለመቻሏ በሆስፒታሉ ለቀናት ለማደር መገደዷን ተናግራለች።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በተለይ ክልሎች ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል ለምን አቃታቸው ተብለው ተጠይቀው ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸው የሰጡት ዋነኛ ምክንያትም አስተዳደራዊ ወጫቸው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ነው የሚለው ዋነኛው ነበር። በክልሎች ያለው የመንግስት ሰራተኛ ቁጥር እጅግ መብዛቱን እና ክልሎቹ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በዚህም ሳቢያ ክልሎቹ ለከፍተኛ በጀት እጥረት ጫና እና ደመወዝ መክፈል እስከ አለመቻል መድረሳቸውን አመላክተዋል።
በመፍትሔነትም የፌደራል መንግስቱ የወሰደው አቅጣጫ ብድር ወስደው እንዲከፍሉ ማድረግ መሆኑን አህመድ ሽዴ ገልጸዋል። ክልሎች የዚህ ብድር ተጠቃሚ የሆኑት ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሆኑን አቶ አህመድ በማብራሪያቸው አስታውቀዋል። ክልሎች ያለባቸው ብድር ወደ ስምንት እና ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ማሻቀቡን በገንዘብ ሚኒስቴር የትሬዠሪ ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ነጠሩ እንደነገሩት ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በዘገባው አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት ሪፖርት በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሱ ሲሆን መንግስት በጦርነት የተጎዳውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግምና ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት እንዲመለስ የሀገር ውስጥ እና የአጋሮችን አቅም ለመጠቀም ዝግጅት ማድረጉን የተመለከተው ሌላኛው ጉዳይ እንደነበር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። የገንዘብ ሚኒስቴር የጦርነትና ግጭት ጉዳት እና የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ሪፖርት አካሂዶ ለመንግስት ማቅረቡን ሚኒስትሩ ተናግረዋል ያለው ዘገባው የደረሰውን ጉዳት በመቀልበስ እና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ እንዲቻል እ.ኤ.አ ከ2023-2028 ድረስ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ አገራዊ የዕቅድ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ብሏል።
በማዕቀፉ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 20 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ በዕቅዱ መመላከቱንም ያብራሩት ሚኒስትሩ ፕሮግራሙን ወደ ስራ ለማስገባት በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በተደረገ የርዳታ ስምምነት 300 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ ስራ መጀመሩንም ማመላከታቸውን ዘገባው አካቷል። አስ