ዜና፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አንድ የአምቡላንስ ሾፌር ከሚያጏጉዙት በግጭት የቖሰሉ ታካሚዎች ጋር በታጣቂ ሃይሎች መገደላቸውን አወገዘ

የፎቶ ማህደር፡- በአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በህዳር 2013 መጀመሪያ ላይ የተኩስ እሩምታ ተከፍቶበት ጉዳት የደረሰበት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አምቡላንስ።

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ የአምቡላንስ ሾፌር አቶ መንግስት ምንይል ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ/ም በታጣቂ ሃይሎች መገደላቸው ማህበሩ አስታወቀ።  

ማህበሩ ግድያውን ተከትሎ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በባልደረባው ላይ የደረሰውን ጥቃት ያወገዘ ሲሆን አስካሁን ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ አካል አንደሌለ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አባል ለአዲስ ስታንዳርድ  ገልፀዋል።

መግለጫው ሟች አቶ መንግስት ምንይል፤ አድዋ፣ ትግራይ ተሰማርተው በግጭት የተጎዱ ወገኖችን በማገዝ ላይ ከነበሩ ሁለት አምቡላንሶች አንዱን በማሽከርከር ከአድዋ ወደ ወልቃይት ዓዲ ረመፅ ሆስፒታል ቁስለኞችን ለማድረስ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ቁስለኞቹን ጨምሮ በታጣቂ ሃይሎች በተደረገባቸው ጥቃት መገደላቸውን ገልጧል። 

የሁለት ሴት ልጆች አባት የነበረው አቶ መንግስት በምዕራብ ደንቢያ ሰብዓዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበረና በሰብዓዊ ህይወት የማዳን ስራ ወልቃይት አዲ ረመፅ ሆስፒታል ተመድቦ አገልግሎት በመስጠት ላይ አንደነበሩም አክሎ የገለፀው መግለጫው  ስርአተ ቀብሩ  በትውልድ ቀዬው  ምዕራብ በለሳ ጎንድ ተክለሃይማኖት ተፈፅሟል ብሏል፡፡

በመላው ሃገሪትዋ  በሰብዓዊ አገልግሎት የተሰማሩ የቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኞችና በጎ ፈቃደኞችን ሰብዓዊ ተግባራቸውን በገለልተኝነት እና በአለማዳላት መንፈስ በነፃነት ተንቀሳቅሰው መስራት እንዲችሉ፣ እንዲሁም ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ታጣቂ ሃይሎች ከእንደዚህ አይነት ጥቃት እንዲቆጠቡ ማህበሩ ተማፅኗል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት በትግራይ ሽሬ ከተማ በተፈፀመ የአየር ጥቃት አንድ የኢንተርናሽናል ሬስኪዉ ኮሚቴ (IRC) የዕርዳታ ሰራተኛ ሲገደል፣ ሌላ አንድ የድርጅቱ ሰራተኛ መቁሰሉን ድርጅቱ አስታዉቆ ነበር::

ያሁኑ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአምቡላንስ ሾፌር ግድያ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የተገደሉ የእርዳታ ሰራተኞችን ቁጥር ወደ 27 ከፍ ያደርገዋል::

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሰሜን የሃገሪትዋ ክፍል በተቀሰቀሰው ግጭት እና መፈናቀል ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ አገልግሎት አየሰጠ አንዳለ ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.