ዜና፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በተፈጠረው ድርቅ ማህበረሰቡ ከድርቁ ተጽዕኖ ማምለጥ አለመቻሉን ገለፀ



ምስል- የአለም የምግብ ፕሮግራም

ሐምሌ 19/ 2014 ዓ.ም፣አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ዘንድሮ በተከሰተው ድርቅ ከዚህ በፊት ከነበሩት አደጋዎች በተለየ መልኩ  ከ 2 እስከ 4 የዝናብ ወቅቶች ያልዘነበበት እንዲሁም ሰፊ ቦታዎችን ያካለለ በመሆኑ ማኅበረሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ ተሻሉ ቦታዎች ተዘዋውሮ ከድርቁ ተጽዕኖ ማምለጥ አለመቻሉ ጠቅሶ ለተጎዱ ሰዎች እና አካባቢዎች የሚሰጠው ትኩረት እና ምላሽ አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳሰበ፡፡

ኮምሽኑ ይህን ያለው በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ እና ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ከየካቲት 14 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች በመዘዋወር የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል በማድረግ ባዘጋጀውን በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው ሪፖርት  ነው። 

በኦሮሚያ ክልል፣ ቦረና ዞን፣ በያቤሎ፣ ተልተሌ፣ ድቡሉቅ፣ ድሬ እና ሞያሌ ወረዳዎች በሚገኙ 11 ቀበሌዎች፤ እንዲሁም በሶማሌ ክልል፣ ሸበሌ፣ ጀረር እና ፋፈን ዞኖች፣ በጎዴ እና አዳድሌ፣ ደጋሃቡር እና ቢርቆድ እና ቀብሪ በያህ ወረዳዎች በሚገኙ 6 ቀበሌዎች በመዘዋወር፣ ተጎጂዎችን እና የተለያዩ አካላትን  አነጋግሪያለው ፣ አካላዊ ምልከታ አድርጊያለው ያለው ኮሚሽኑ በድርቁ ጉዳት ሳቢያ በተለይ በቂ ውኃና ምግብ ባለመኖሩ ሰዎች ለተለያዩ የጤና እክሎች መዳረጋቸውን፣ በምግብ እጥረት ምክንያት ሰውነታቸው መክሳቱን፣ ሆዳቸውና እግራቸው አብጦ በዚህም ታመው የተኙ ሰዎች መኖራቸውንና የጤና ግልጋሎት መስጫ ተቋማት በአካልም በኢኮኖሚም ተደራሽ አለመሆናቸውንም አረጋግጫለው ብሏል፡፡

በማከልም  “ የጤና ግልጋሎቶችን ለራሳቸው ማግኘት ለማይችሉ የድርቁ ተጎጂዎች የጤና ግልጋሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ውስን ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ተጋላጭ የሕብረተሰቡ ክፍሎች በተለይም አረጋውያን እና ሕፃናት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል። በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በተፈናቃይ ካምፖች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተግባራት አለመከናወኑ እና የተፈናቃዮችን ጤና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል እንደ ወረርሽኝ የመሰለ በሽታ ተጋላጭነት ነበር፡፡ ይህም የድርቅ ተጎጂዎችን የጤና መብት ከማረጋገጥ አንጻር ክፍተት እንዳለ ያመላክታል” ብሏል፡፡

የክትትል ሪፖርቱ በኦሮሚያም ሆነ በሶማሌ ክልል በቅድመ ማስጠንቀቅ እና በዝግጁነት ረገድ የተሰበሰቡት መረጃዎች አግባብነት ባላቸው የብሔራዊ የአደጋ ክስተት ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲና ስትራቴጂ እና በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን  የድርቁን አደጋ ቅነሳ፣ ቅድመ-ማስጠንቀቂያና ዝግጅት እንዲሁም የማሳወቅ ሥራዎች በይፋ አለመሠራታቸው ለድርቁ አደጋ ምላሽ የዘገየ እንዲሆን ምክንያት መሆኑን አስረድቷል፡፡

ሪፖርቱ የውኃ መብትን በተመለከተ ለክትትሉ በተመረጡ ቦታዎች የድርቁ ተጽዕኖ መሰማት የጀመረው የመጠጥና የንጽሕና ውኃ ምንጮች መቀነስ እና መድረቅን ባስከተለ የውኃ እጥረት የተነሳ መሆኑን እና ለዚህ ሁኔታ የሚሰጠው ምላሽ እንደየ አካባቢው የተለያየ ሲሆን የመጨረሻው አማራጭ ግን ውኃን በተሽከርካሪ ማከፋፈል አስታውሶ፣ ክትትሉ በተደረገበት ወቅት ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመሰረተ ልማት አለመኖር፣ በነዳጅ እጥረት፣ በውኃ ዋጋ መናር ወይም በውኃ አቅርቦት ውስንነት ምክንያት ውኃ ተደራሽ የማይሆንላቸው በርከት ያሉ ሰዎች እንደነበሩ ያሳያል፡፡

ኢሰመኮ የፌዴራል፣ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች መንግሥታት በአፋጣኝ  በመረጃና በምዝገባ ሥርዓት የታገዘ፣ አሳታፊ የሆነ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት የተዘረጋለት እንዲሁም ከፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ምላሽ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና ክትትል ማድረግ አለባቸው ባሏል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በድርቁ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ድጋፍ ፈላጊዎች ባሉበት ቦታ እርዳታ እንዲያገኙ እንዲያደርግ፣ እርዳታ የሚገኝበትን ቦታ እና ሁኔታ እንዲያሳውቅ እና ያለ በቂ መረጃ ለሚፈናቀሉ ሰዎች አፋጣኝ እርዳታ ለማድረግ የሚያስችል የመጠባበቂያ እርዳታ ዝግጁ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ይህንኑ አስመልክተው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር  ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ መንግሥት በተለይም የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሕጉ በሚያዘው መሰረት የድርቁን አደጋ በይፋ በማሳወቅ በአደጋ ክስተት ስጋት ሥራ አመራር ሥራ እገዛ ከሚያደርጉ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሀገሮች ጋር ሀገሪቱ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲኖር የማድረግ ግዴታ እንዳለበት አስታውሰዋል።

በተጨማሪም “እስካሁን በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት በድርቁ ለተጎዱ ሰዎች እና አካባቢዎች የተሰጡ ምላሾች አበረታች ቢሆኑም፣ ተጎጂዎች አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እና ድርቁም ከሁለቱ ክልሎች በተጨማሪ ወደሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው፤ እንዲሁም በተለያዩ ግዜያት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚያገረሹ ግጭቶች ምክንያት በድርቁ ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለተደራራቢ ጉዳት እየዳረገ ነው። ስለሆነም በድርቁ ለተጎዱና አዋሳኝ አካባቢዎች የሚሰጠው ትኩረት ሊቀንስ አይገባም”  ሲሉ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.