አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጎጂዎች ተብሎ የሚቀርብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ መሆኑ በመረጋገጡ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የእርዳታ አቅርቦት ማቋረጡን ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው የኢሜይል መልዕክት አስታወቀ። የምግብ እርዳታ የማቋረጡ ውሳኔ እጅግ አዳጋች እና አስቸጋሪ ቢሆንም ውሳኔውን ለማሳለፍ ተገደናል ሲል ረድኤት ድርጅቱ ቃል አቀባይ በአሜሪካን ኤምባሲ በኩል ባደረሰን መልዕክት ያስታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ የእርዳታ ተደራሺነት አሰራር ስርአት ዙሪያ ተገቢ የሆነ ማሻሻያ እስኪደረግ ድረስ በውሳኔው እንደሚጸና አመላክቷል።
የረድኤት ድርጅቱ የምግብ እርዳታ አቅርቦቱን በፍጥነት ለማስጀመር ተደራሽነቱ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን፣ እንዲሁም በማስረጃ የተደገፈ ሁኖ ሲገኝ እና በገለልተኝነት እንደሚፈጸም ሲያረጋግጥ ብቻ መሆኑን አስታውቋል። የውሳኔው ዋና አላማ የምግብ አቅርቦቱ ተደራሽነት ለተጎጂዎች ብቻ እንዲሆን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጿል።
አዲስ ስታንዳርድ በዛሬው እለት ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባሰረጫው ዘገባ በኢትዮጵያ ከለጋሾች የተገኘ የምግብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ የሚገኘው በተቀናጀ፣ በተደራጀ መንገድ መሁኑ እና ተግባሩ የፌደራል እና የክልል ተቋማትን ያሳተፈ በሰባት ክልሎች የተፈጸመ ነው መባሉን አስታውቋል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ በትግራይ ክልል ተፈጸመ በተባለው ለተረጂዎች የቀረበ የምግብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ ውሏል በሚል ማቋረጣቸው ይታወቃል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ ያዘጋጁት እና ለአዲስ ስታንዳርድ የደረሰው የውስጥ ማስታወሻ እንደሚያሳየው ከሆነ ድርጊቱ የተፈጸመው በትግራይ ብቻ አይደለም፤ ተግባሩ የፌደራል እና የክልል ተቋማትን ያሳተፈ በሰባት ክልሎች የተፈጸመ ነው። የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ ላለፉት ሁለት ወራት ባካሄደው ሰፊ ክትትል እና ምርመራ በኢትዮጵያ በለጋሽ ድርጅቶች የሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላልታለመለት አላማ እየዋለ የሚገኘው በሀገር አቀፍ ደረጃ መሆኑን ማረጋገጡን የውስጥ ማስታወሻው አመላክቷል። ድርጊቱ በተቀናጀ መልኩ በተወሳሰበ የወንጀል መንገድ እንደሚፈጸም የጠቆመው ሰነዱ የምግብ እርዳታው ለተጎጂዎች እንዳይደርስ ድርጊቱ እንቅፋት መሆኑን ማስታወቁን ዘገባችን አካቷል። አስ